«ማኅበረ ቅዱሳን ለሁሉም ግልጽ አሠራር አለው» ክፍል ሁለት
ስምዐ ጽድቅ፦ አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳን የተወሰነ ብሔር ስብስብ ነው የሚል አስተያየት አላቸው፤ ማኅበሩ ለዚህ ዓይነት አስተያየት የሚሰጠው መልስ ምንድነው?
ስምዐ ጽድቅ፡- የለቲካ አቋምን በተመለከተስ?
ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ- ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የእኛ ማኅበር ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ እንደ ተቋም የሚሰጠውም አገልግሎት ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ለየትኛውም የፖለቲካ ዓይነትና አደረጃጀት የሚያግዝ /የሚሠራ/ እንዲሆን መቼም ቢሆን ፍላጐቱ የለንም፡፡ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ አምስት እንደተቀመጠው «ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖረውም» ይላል፡፡ የዚህን አንቀጽ ይዘት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማኅበሩ ያሉ የተወሰኑ አካላት በሓላፊነት ላይ እያሉ የማንኛውም የፖለቲካ አባል እንዳይሆኑ በ1998 ዓ.ም የሥራ አመራር ጉባኤያችን ወስኗል፡፡ በውሳኔውም መሠረት የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የማኅበሩ መደበኛ መምህራን፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ጽ/ቤት አባላት፣ የኦዲትና ኤንስፔክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ የማዕከላት ሰብሳቢዎች በሓላፊነት ላይ ያሉ መደበኛ አገልጋዮች የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይሆኑም፡፡
ይህ ማለት ግን ለፖለቲከኞች በማኅበሩ የማገልገል ዕድል አይኖራቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለፖለቲካ ዓላማቸው ማኅበሩን መጠቀም ግን አይችሉም፡፡ ስለዚህ የትኛውንም የማኅበሩን አባል በግሉ የ«ሀ» ወይም የ«ለ» ፓርቲ ደጋፊ፣ አባል ወይም አመራር እንዲሆን ወይም እዳይሆን ምንም ዓይነት ተቋማዊ ተጽዕኖ በማኅበሩ የሚፈጠርበት ዕድል የለም፡፡ ይህ ግን ሀገርን በመገንባት ረገድ ለአጠቃላዩ ማኅበረሰብ ትርጉም ያለው ልማታዊ ተግባራትን የማከናውን ዓላማና እንቅስቃሴ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ያላት የሀገራዊ ልማት ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣይነት እንዲኖረው ክርስቲያን ምሁራንና ወጣቶች ባላቸው አቅም ሁሉ ይሳተፋሉ፡፡ የልማት ተሳትፎአቸው ለሀገርና ለትውልድ እንዲጠቅም፣ ቤተክርስቲያንም ያላትን ድርሻ እድትወጣ በማሰብ ነው፡፡ ብዙዎቹ ልማታዊ ተግባሮቻችን ደግሞ በቀጥታ የቤተክርስቲያናችንን ጥቅም የሚያስጠብቁ በመሆናቸው እንቅስቃሴያችን ለሌላ ትርጉም በሚጋለጥ መልኩ የሚደረግ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡
በእርግጥ እንደተባለው በሀገር ውስጥም በውጪም በፖለቲካ ወገንተኝነት ማኅበሩን ለማማት የሚፈለጉ ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን የሚሰጡት አስተያየቶች የተዘበራረቁ መሆናቸው በራሳቸው መሠረት የሌላቸው አስተያየቶች መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በሀገር ውስጥ ያለው ማኅበሩ የ«ሀ» ፖርቲ ደጋፊ ነው ሲል በውጪ ሀገር ያሉ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የ«ለ» ፖርቲ ደጋፊ ነው እያሉ ተጨባጭነት የሌለውና ምናልባትም የማኅበራችን አባላት በሆኑ የአንዳንድ ግለሰቦች ተሳትፎን መነሻ አድርጐ የሚሰጥ ሚዛናዊ ያልሆነ ድምዳሜ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ማኅበራችን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተመርኩዞ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ከሚቋቋመው መንግሥት ጋር መሥራት ሃይማኖታዊም ሕገ መንግሥታዊም ግዴታው ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ማኅበሩ እንደተቋም የትኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ /Ideology/ በመደገፍ ወይም በመቃውም ከፖርቲዎች ጋር ግንኙነት ስለሌለው /ስለማይኖረው/ ለማንም ስጋት ወይም ዕድል ልንሆን አንችልም፡፡ በዚህ ደረጃ ፈርጆን የሚነሣ አካል ካለ ግን ለመፈረጅ ያበቁትን የመረጃ ምንጮች እንዲመረምር በዚሁ አጋጣሚ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበሩ አክራሪ ነው ስለሚባለውስ?
ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፡- እኛ «አክራሪ» የሚለውን ቃል በጥንቃቄ ነው የምንመረምረው? አክራሪ ማለት የሃይማኖቱን ሕግ አክብሮ የሚኖር ተግቶ የሚጾም፣ የሚጸልይ በሃይማኖቱ ላይ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ፣ ታሪኩን፣ ቤተክርስቲያኑን የሚወድ፣ ለሃይማኖቱ የሚቀና የማይዋሽ ወይም ወደ ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ራሱንም የሃይማኖት ወገኑን ሁሉ ለማድረስ የሚተጋ ከሆነ የማኅበራችንን አባላት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰዎች ምናልባት በልማድ በዚህ ብያኔ ለመጥራት ፈልገው ከሆነ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ የሚመላለሱትን ክርስቲያኖች «አክራሪ» ተብ ለው ከሚጠሩ አጥባቂ፣ ዐቃቤ ሃይማኖት ቢባሉ የተሻለ ነው፡፡
በሌላ በኩል ግን «አክራሪ» የሚለው የሚያሰቃይ፣ የሚገድል፣ የሚያስገድድ፣ የሚሳደብ፣ የሌላውን ሳይነኩ የራሳቸውን አምልኮ እየፈጸሙ ያሉትን የሚረብሸ፣.. ወዘተ ለማለት የተቀመጠ ብያኔ ከሆነ በወንጌል የሚያምኑ፤ አምነውም የሚያስተምሩ ክርስቲያኖች ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ከላዩ የተጠቀሱት ተግባራት ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ጋር ተጣጥመው አይሔዱም፡፡ ማኅበራችንም ስብከተ ወጌልን በመላው ሀገሪቱ እና ዓለማት የማስፋፋት ዓላማ ይዞ የሚሠራ በመሆኑ ለፍቅርና ለመከባበር ትልቅ ቦታ አለው፡፡
ምናልባት በማስጨነቅ ወይም በማስገደድ ሃይማኖታችንን ለማስጣል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ቅሬታችንን መግለጻችንና በሃይማኖታችን ላይ በኅትመት ወይም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አማካኝነት የሚሰጡ አስተያየትና ጥያቄዎች ሲኖሩ መልስና የአጸፋ አስተያየቶችን መስጠታችን በዚህ ደረጃ አስ ፈርጆን ከሆነ ሚዛናዊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እነዚህን የምናደርገው በሃይማኖታችን ላይ ጥያቄ ያነሣውን ወይም አስተያየት የሰጠውን አካል ለመተቸት ወይም ለመሳደብ ተፈልጐ ሳይሆን እነዚህ አካላት ካሠራጯቸው መልእክቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ሐሳብ እንዳይበረዝ፣ ሃይማኖታችን መልስና አስተያየት የሌለው መስሎ ለምእመናን እንዳይታሰብ ለመጠበቅ የሚደረጉና ለጠየቁን መልስ እንድንሰጥ በሃይማኖታችንም የታዘዘውን መንፈሳዊ ተግባር ለመፈጸም ነው፡፡
መከራ የደረሰባቸውና የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ሲኖሩ ቅሬታችንን መግለጻችን ተገቢ ይመስ ለኛል፡፡ ምክንያቱም ለሀገር ሰላምም የሚበጀው ችግሮች መኖራቸውን ጠቁሞ ሕዝብም መንግሥትም መፍትሔ እየሰጣቸው ሲሔዱ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ስሜታዊ በሆነ መልክና ከጀርባው ሌላ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴን በክርስቲያኖች ስም ማካሔድን በጽኑ የምንቃወመው ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያን ያለውን ተቆርቋሪነት ከግምት አስገብቶ የተለያዩ አካላት በስሜት የሚያካሒዷቸው ግልጽና ሥውር እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አካላት እንደሚኖሩ እናምናለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓውደ ምሕረት ቆሞ ያለ ሕግና ሥርዓት የሚያስተ ምሩ መምህራንን ሁሉ የማኅበረ ቅዱሳን መምህራን ናቸው የሚሉም እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን በጭፍን የሚሰጡ እነዚህን የሚመስሉ አስተያየቶች ተገቢ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት ማኅበሩ ያሰማራቸው መሆን አለመሆኑን ማጣራትም ወይም ሆኖም ከተገኘ ማኅበሩ ባለው አሠራር ርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብ የተሻለ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓይነት አቋም ላይ ያለን ማኅበር አክራሪ የሚሉት አካላት ካሉ ያን ለማለት መነሻ ያደረጓቸውን ጭብጦች ማጤን ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ጋር ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፤ ማኅበሩም ለመምሪያው ለመታዘዝ ፈቃደኛ አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም አሉ፡፡ እርስዎ እንደ ሰብሳቢ ምን ይላሉ?
ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ቤተክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱም ደንብና መመሪያዎች እንዲጠበቁ በጸኑ የሚሠራ ማኅበር ነው፡፡ ይህ ዋነኛ አጀንዳ ያለው አካል የማደራጃ መምሪያውን አሠራር ጠብቆ አይንቀሳቀስም ከተባለ ራዶክስ /መጣረስ/ ይፈጥራል፡፡ ማኅበሩ በመምሪያው የአሠራር ሥርዓት ላይ ችግር የመፍጠር ፍላጐትም ሥልጣንም የለውም ነገር ግን መምሪያውን ከሚመሩት ግለሰብ ዓላማና አቅም ላይ ግን ጥያቄ አለው፡፡ መከሩ ብዙ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት በሆኑበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ለአገልግሎት የተሰማሩ ማኅበራት እና ሰንበት ት/ቤቶችን በመምራት ረገድ የሚከተሉት የራሳቸው ፖሊሲ እንደተመሪ /ባለድርሻ/ ምቹ አይደለም፡፡ ማኅበሩ ላይ አሉ የሚሏቸውን ችግሮች በውይይትና በክርስቲያናዊ የምክክር ሥርዓት ከመፈጸም ይልቅ በግልጽና በስውር የማኅበሩን ስም ማጥፋትን ሥራዬ ብለው ይዘዋል፡፡ የተለያዩ አካላትም በማኅበሩ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ያላ ሠለሰ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ማኅበሩ ችግር አለበት፤ ለመምሪያውም አይታዘዝም… ወዘተ የሚለውን የራሳቸውን ሓሳብ መነሻ አድርገው የሚጽፏቸውን ደብዳቤዎች ምስክር እያደረጉ መናፍቃን ደግሞ በመጻሕፍት አሳትመው ሲሰድቡን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን እያየን ማኅበረ ቅዱሳንን ከሚጠሉ መናፍቃን ጋር እርሳቸው ተመጋግበው እየሠሩ ነው ላለማለት ዋስትና አይሰጥም፡፡ የማኅበሩ አሠራር ችግር አለበት ብለው ቢያስቡ እንኳን ከሠሯቸው በጐ ተግባራት፣ የወጣት ምሁራን ክርስቲያኖች እንቅስቃሴን አስፈላጊነትና አሁን ቤተክርስቲያን ከአጽራረ ቤተ ክርስተያን በኩል እየደረሰበት ካለው ፈተና አንጻር በስብከተ ወንጌል ረገድ ያለውን ርምጃ በመመልከት ችግሮቹን ከሚመለከታቸው ከተለያዩ አካላት ጋር ተግባብቶ በመፍታት ግልጽ አሠራር ማስፈን ይገባቸው ነበር፡፡ ያንን አላደረጉም፡፡ ስለዚህ በአንዳንድ ማኅበሩ የአሠራር ችግሮች እንዳሉበት ለመምሪያውም እንደማይታዘዝ አድርጐ በማናፈስ ሺሕዎች የተሰለፉለትን ቤተክርስቲያን የመጠበቅ ተልእኮ ማነቆ እንዲያጋጥመው እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰቡ ተልእኮ ላይ ማኅበሩ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ሆኗል፡፡ ማኅበሩ ለ17 ዓመታት ከተለያዩ መምሪያ ሓላፊዎች ጋር በምክክር ሠርቷል፡፡ ውጤትም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ እኛ ጥያቄያችን ዛሬ እርሳቸው ያገኙት አዲስ ነገር ምንድነው የሚል ነው፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- የመምሪያው ዋነኛ ጥያቄ የማኅበሩን ገንዘብና ንብረት ኦዲት በመደረጉ ጉዳይ ነው፡፡ ማኅበሩ በዚህ ላይ ያለው አቋም ምን ስልሆነ ነው ችግሮች የተፈጠሩት?
ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ- ማኅበራችን ለአገልግሎት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ገንዘብ በሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ካሉ ከማኅበሩ አባላት የሚያገኘው በማኅበሩ የውስጥ ኦዲተሮች የሚሠሩት ሪፖርት ተአማኒነት ስላለውና የሚታዩ ውጤታማ ክንውኖችን መሠረት አድርጐ ነው፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ የማይታመንና ግልጽነት የጎደለው ከሆነና ሥራችንም በጎና ውጤታማ ባይሆን ለቀጣዩ ተግባሮቻችን የሚሆን የገንዘብ መዋጮን መሰብሰብ ባልቻልን ነበር፡፡ ስለዚህ አባላቱ መዝናናት ሳያምራቸው በመጠን እየኖሩ ለቤተ ክርስቲያን ከሚከፈሉት ዓሥራት በኩራት ተጨማሪ ለማኅበሩ አገልግሎት የሚሰጡትን ገንዘብ፣ ጊዜና ንብረት በአግባቡ መያዝ የእያንዳንዱ አባል ሓላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ ለዚህ ዋስትና የሚሰጠው ደግሞ የኦዲት ሥራው ነው፡፡ ስለዚህ የኦዲት ሥራን ለማኅበራችን ደኅንነት እንደ አንድ ግብ የምናስብ ነን፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ «ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፋችሁ ተጠንቀቁ» ያለውን ቃሉን ሁሌ እናስባለን፡፡ ስለዚህ በየጊዜው የኦዲት ሥራዎች የውስጥ ኦዲተሮቻችን ይደረጋሉ፡፡ ያንን አለማድረጋችን ከማደራጃ መምሪያው ይልቅ የሚጐዳው ማኅበሩን ስለሆነ ስለነገሩን ሳይሆን ስለሚያስፈልገን መቼም ቢሆን እናደርገዋለን፡፡ ማኅበሩ በጠቅላላ ጉባኤው የቤተክርስቲያን መምሪያ ሓላፊዎች ባሉበት የሂሳብ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ሆነ የሚመለከተው አካል የሂሳብ ሪፖርቱ አላረካኝም በውጪ ኦዲተር ይቀርብ ብሎን አያውቅም፡፡ ጥያቄው ከቀረበ ምንግዜም ማድረግ ይቻላል፡፡
አሁን ግን የተሻለ አደረጃጀትና ሰፊ አገልግሎት በሀገር ውስጥና በውጪም መስጠት ስንጀምር መምሪያው በማኅበሩ አገልግሎት የማይደሰቱ ግለሰቦች እና አካላት ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ መገኘቱ በእጅጉ ያሳስበናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የመመሪያ ሓላፊው የእኛን ስም ለማጥፋት በመ ጠመዳቸውና ጊዜያቸውን ለዚያ እየሠው በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰ/ት/ቤቶች ከመምሪያው የሚፈልጉትን ያህል ድጋፍ ለማግኘታቸው ከፍተኛ ጥርጣሬ አለን፡፡ ከሁሉ በላይ ሊያሰጨንቀን የሚገባ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንጂ ሌላ አልነበርም በእኛ በኩል ግን የሚጠበቅብንን በማድረግ መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ሁሌም እንሻለን፡፡ ችግራችንም ከመዋቅሩ /ከመምሪያው/ ጋር ሳይሆን ከመምሪያው ሓላፊ ጋር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡