ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልም
ምእመናን ይህን ወቅታዊ የለውጥ ሒደት ከግምት አስገብተው ቤተክርስቲያናቸውን ከመጠበቅ አንፃር ዛሬ ይዛ እንድትገኘ ከሚፈልጉአቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የአመራርና አስተዳደራዊ አቅምን የማጠናከር ተግባርን ነው፡፡
የአመራርና አስተዳደር አቅም ማለት ደግሞ የአሠራር፣ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል አቅምን ይመለከታል፡፡ ያለን አሠራር ከነቀፋ የሚያድነን፣ ለመተማማት ሰበብ የማይፈጥር /ግልጽ/ ያጠፋ የሚቀጣበት፣ ያለማ የሚከብርበት /ተጠያቂነት የሰፈነበት/ እንዲሆን ነባራዊ ሁኔታው ያስገድዳል፡፡ ለዚህም ከሕገ ቤተክርስቲያኑ ጋር የማይጋጭ፣ በየደረጃው ያሉ የሥራ ክፍሎችን እርምጃ የሚያፋጥን ደንብና መመሪያ አዘጋጅቶ ማጽደቅ ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ያለንን መዋቅርና አደረጃጀት እንድንፈትሽ ይጠይቃል፡፡ አካባቢያዊ ለውጦችን ከግምት አስገብቶ በዘመናዊው የአስተዳደር ዘይቤ የሚመራ የሰው ኃይል በየደረጃው መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ግፊቶች የተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ያመጡት አይደለም፡፡ የአጠቃላዩ የለውጥ ግስጋሴ ያስከተላቸው ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በየጊዜው ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ጋር በማስተያየት፣ ነባር፣ ጠቃሚና መንፈሳዊ የሆኑ፤ መቼም መች የሚያስፈልጉንን ኦርቶዶክሳዊ መገለጫዎቻችንን ከመጠበቅ ጋር እያጣጣሙ ማካሔድ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ በፍጥነት ተግባራዊ እንድናደርግ ያስገደደንም ከላይ የጠቀስናቸው ተጨባጭ እውነታዎች ናቸው፡፡ ለዚህ እውነታ ደግሞ ማድረግ ያለብንን እንድናደርግ ያስፈልጋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስም እነዚህን የምእመናንን ትኩረቶች ተረድቶ በቅርቡ የአመራርና አስተዳደራዊ አቅምን ለመገንባት ወይም የተሻሉ ጠቃሚ ለውጦችን ለማምጣት ያሳየው ፍላጎትና ጅምር እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው፡፡ «ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ» ያለውን የሐዋርያውን ምክር ሰምቶ እነዚህን ጅምር እንቅስቃሴዎች መደገፍ ደግሞ የክርስ ቲያኖች ሁሉ ድርሻ ነው፡፡
ሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለሺሕ ዘመናት ብዙ ውጣ ውረዶችን እያለፈች ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ጭምር እንደብርሃን የሚታዩ በጎ ተግባራትን ስትፈጽም የኖረችው ቤተክርስቲያን ባለአደራዎች እንደሆኑ እናምናለን፡፡ አባቶች ይህንን ተረደተው በስውርም ይሁን በግልጽ፣ በግልም ይሁን በቡድን የሚፈጸሙ ጣልቃ ገብነቶችን ተቋቁመው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለጊዜያችን የሚያስፈልገውን የአመራርና የአስተዳደር ዓይነትና ደረጃ በቤተክርስቲያን ማስፈን አለባቸው የሚል እምነት አለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የተጠሩለትን ሕይወትና ዓላማ ከመረዳት ጀምሮ እውነትን ለማገልገልና ለዚያም መከራ አስከመቀበል ለመትጋት ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ለሚገባና እውነት ለሆነው ነገር መከራን መቀበል የሚገባ ነውና፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው አሉ ብሎ ያስቀመጣቸውን በአመራሩና በአሰተዳደሩ የታዩ ችግሮችን ካልፈታና መፍታት የሚያስችሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው አሠራሮችን ለመዘርጋት ቁረጠኝነት ካጣ ቤተክርሰቲያን በሒደት ሊገጥማት የሚችለው ፈተና ማኅበረ ቅዱሳንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው በቤተ ክርስቲያኒቱ ተንሰራፍተዋል ያላቸውን የአሠራር ችግሮች ግልጽ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱ በሁለት ተገቢ ባልሆኑ የአካሔድ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳትወድቅ ማኀበራችን ስጋት አለው፡፡ አንደኛው ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው ግልጽ ያደረገው የውስጥ አሠራር ችግር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እነዚህን የአሠራር ችግሮች አጋኖ በማራገብ ቤተክርስቲያኒቱን በቅጥረኛነት ለማጥፋት የሚካሔደው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከዚህ አጣብቂኝ ሌላ በሚኖሩ ኋላቀርና ብልሹ አሠራሮች በመመረር ምእመናን የተለያየ አደረጃጀት ፈጥረው በራሳቸው ማስተዋል በመንቀሳቀስ ለቤተክርስቲያን መከፋፈል ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የያዝነውን ደካማ አሠራር የጠሉ በመንፈስ ያል ጠነከሩ ምእመናን ይሰናከላሉ፡፡ ሥራዎቻችንን ከሚሠሩበት መሥሪያ ቤት፣ ካላቸው ድርጅት ተሞክሮ፣ ከሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት ዕድገትና ግስጋሴ ጋር የሚያስተያዩት ደግሞ የአመራርና የአስተዳደር ዘይቤያችንን በመናቅ ይለዩናል፡፡ ከዚያም አልፎ የቤተክርስቲያኒቱ ቅርስ፣ ሀብትና አስተዳደር በአጽራረ ቤተክርስቲያን እጅ እስከ መያዝ ሊደርስ ይችላልና፡፡ ቤተክርስቲያን የማትሸነፍ ቢሆንም የብዙ ምእመናን ሕይወት መፈተኑ የማይቀር ይሆናል፡፡
በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶች ለዚህ ትውልድ የደረሰችው ቤተክርስቲያን ወሳኝ ባላደራነታቸውን ተረድተው ከቀደሙት አባቶቻቸው ቆጥረው ሰፍረው የተረከቡትን የቤተክርስቲያኒቱን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት ለተተኪው ትውልድ በአግባቡ ማስረከብ ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ኦርቶዶክሳዊና ዘመናዊ አስተዳደርን የማስፈን ሐላፊነታቸውን በሰከነና አሳማኝ በሆነ አካሔድ እንደሚፈጽሙ እምነታችን ነው፡፡ ይህንንም ስንል ያንን በማድረግ ሒደት የሚኖሩ የተለያዩ አስተያየቶችም አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ አደርጎ ከማሳየት ይልቅ በየጊዜው ከሚኖሩ ለውጦች ጋር እየተፈተሹ የሚተገበሩ የአካሔድ ዓይነቶች ተደረገው መወሰድ እንዳለባቸው ከመጠቆም ጋር ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ሕገ ማኅበሩን አጽድቆ የሥራ ፈቃድ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህን ተፈላጊ የአሠራር ማሻሻያዎች ለማምጣትና ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሰጠው ሓላፊነት ካለ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር