የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ 397 ደቀ መዛሙርትን አስመረቀ


በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቀን በማታና በርቀት ትምህርት ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርት እሑድ ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት አስመረቀ፡፡

theology1

ኮሌጁ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሆኖ ከተቋቋመበት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ ለቅድስት ቤተክስቲያንና ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱ ደቀመዛሙርትን አሰልጥኖ ማውጣቱን የኮሌጁ ምክትል ዲን ዶክተር አባ ኃይለማርያም መለስ ለመካነድራችን ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዶክተር አባ ኃይለማርያም በዚሁ መግለጫቸው፡-“የዘንድሮውን የምርቃት መርሐ ግብር ልዩ ከሚያደርጉት ነጥቦች አንዱ ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ መልኩ በቁጥር ከፍ ያሉ ሴት ተማሪዎች መመረቃቸው እና አብዛኛዎቹም የመአረግ ተመራቂዎች መሆናቸው ነው፡፡” ብለዋል፡፡

theologyከመንፈሳዊ ኮሌጁ የሬጅስትራር ጽ/ቤት ባገኘነው መረጃ በዚህ ዓመት በድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ (P.G.D) 16፣ በዲግሪ 95፣በዲፕሎማ 72፣ በግእዝ ቋንቋ 14፣ እንዲሁም 200 ተማሪዎች በሰርተፍኬት መርሐ ግብር ተመርቀዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ዓመት በደቀ መዝሙር ኢያሱ ጥጋቡ የተመዘገበው 3.98 ነጥብ በኮሌጁ ታሪክ እስከአሁን ከተመዘገቡት ከፍተኛው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡