የቅድስት ምንባብ 3(ሐዋ.10÷17-30 )
ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር፡፡
ተጣርተውም፡- ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው÷ “እነሆ÷ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፡፡ ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና፡፡” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና÷ “እነሆ÷ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው፡፡ እነርሱም÷ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት፡፡ እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ፡፡ በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት፡፡ ጴጥሮስም÷ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው፡፡ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው÷”ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ፡፡ አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡”