ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ

ጥቅምት ፲፩፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

የአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ተጋድሎ በጽኑ መሠረት ላይ በመገንባቱ የመከራ ዝናብ ቢዘንብ፣ የሥቃይ ጎርፍ ቢጎርፍ፣ የችግር ነፋስ ቢነፍስ አይወድቅም፡፡ (ማቴ.፯፥፳፭) ይህም የሆነው እነርሱን በመንፈሳዊ ሕይወት የተተከለ፣ በተጋድሎ ያሳደገ፣ ገቢረ ተአምራት ወመንክራት በማድረግ እንዲያብቡ ያደረገና ለፍሬ ክብር ያበቃ የክብር ባለቤት አምላካችንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ነው፡፡

በየዓመቱ ጥቅምት ፲፪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዕረፍቱንና የምስክርነቱን መታሰቢያ በዓል የምታከብርለት ቅዱስ ማቴዎስም በዚህ ጽኑ ተጋድሎ ያለፈና በአምላካችንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበለትን ጥሪ ተከትሎ ፈፅሞ ለክብር የበቃ ሐዋርያና ወንጌላዊ ነው፡፡

ሐዋርያና ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ የተወለደው በናዝሬት ከተማ ሲሆን ከ፲፪ቱ የእስራኤል ነገድ ከይሳኮር ነገድ የተገኘ ነው፡፡ አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡ ለአገልግሎት ከመጠራቱ በፊት የቀድሞ ስሙ ሌዊ ይባል ነበረ፤ በኋላ ግን ማቴዎስ ተብሏል፡፡ ማቴዎስ ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ “ጸጋ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ስጦታ)” ማለት ነው፡፡ ስሙን የቀየረውና አስቀድሞ በእስራኤላውያን ዘንድ እጅግ ከተጠላው የቀራጭነት (ግብር ሰብሳቢነት) ሙያው የጠራው አምላካችንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ማቴ. ፱፥ ፱ -፲፫፣ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪)

“ተከተለኝ” የምትልን አንዲት የአምላካችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ሰምቶ ሁሉንም ነገር ትቶ ለጊዜው በእግር በፍጻሜው ግን በግብር ተከትሎታል፡፡ (ማቴ.፱፥፱) በአንዲት ቃል ሁሉንም ነገር ትቶ እውነተኛውን አምላክና የዓለም መድኃኒት በመከተል ብዙ አሕዛብን አሳምኗል፤ ወደ ክርስትናም ለውጧል፡፡
በወንጌል እንደተጻፈው ቅዱስ ማቴዎስ ጌታ “ተከተለኝ” ካለው በኋላ በቤቱ ታላቅ ምሳ አዘጋጅቶ ምሳውን ጌታችንና ደቀ መዛሙርቱ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ተመግበውለታል (ሉቃ. ፭፥፳፰)፡፡ በዚህም ትእምርተ ምናኔን በተግባር አስተምሯል፡፡ ለዚህም ነው አባቶች ቅዱስ ማቴዎስን “በቁሙ ተዝካሩን አውጥቶ አምላካችንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተለ ሐዋርያ” የሚሉት፡፡
ሕግን ጠንቅቀን እናውቃለን ለሚሉ አይሁድ ፍጹም አይሁዳዊ የሆነ የሕግ መምህር ቅዱስ ማቴዎስ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅሶች በማንሣት አዲሲቷ የፍቅር ሕግ ሕገ ወንጌል ከሕገ ኦሪት እንደምትበልጥ አሳይቷል፡፡ ይህም ኦሪታዊ ይዘቱ የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን በሐዲስ ኪዳን የመጻሕፍት ቅደም ተከተል ከእርሱ አስቀድሞ ከተጻፈው ከቅዱስ ማርቆስ ወንጌል እንዲቀድምና በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን መካከል ድልድይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ለሙሴ ሕግን የሰጠና ነቢያትንም ለትንቢት ያስነሣ እርሱ ራሱ አምላካችንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ባለ ማስተዋልና ላለማመንም በዳተኝነት በመጓዝ ብዙ የሕግ እና የትእዛዝ ጥያቄዎችን ለአምላካችንና ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚያቀርቡት ጸሐፍት፣ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን እጅግ ጥበብ ከተሞላባቸው የጌታችን መልሶች ጋር የጻፈልን ሐዋርያና ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ ነው፡፡

ለአብነትም በማቴዎስ ወንጌል ላያ የተጻፈውን ይህን ቃል እንመልከት፡- ‹‹በዚያን ቀን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እንዲህም ብለው ጠየቁት ፤ “መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ፡፡ ሰባት ወንድሞች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፤ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፣ እስከ ሰባተኛው ድረስ ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች፡፡ ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች፡፡››

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ፡፡ በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔወ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም፡፡ ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁም የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም›› የሚል የተሰበሰበውን ሕዝብ ሁሉ እጅግ ያስገረመ መልስ መልሶላቸዋል፡፡

ጥያቄያቸው ግን በዚህ አላበቃም፤ ሌላም የሕግ ጥያቄ አቀረቡ፡- ‹‹አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው “መምህር ሆይ፥ ከሕግ የትኛዋ ትእዛዝ ታላቅ ናት” ብሎ ጠየቀው፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፡፡ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡ ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፤ እርሷም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለዋ ናት፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል›› በማለትና እራሳቸውንም መልሶ ጥያቄ በመጠየቅ ከዚያች ዕለት ጀምሮ ወደ ፊትም ጥያቄ ለመጠየቅ የሚያስችል ድፍረት እስኪያጡ የሰጣቸውን መልሶች የጻፈልን ሐዋርያና ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ ነው፡፡ (ማቴ.፳፪፥፳፫-፵፮)

በመጽሐፈ ስንክሳር ጥቅምት ፲፪ ቀን ተመዝግቦ ደግሞ እንደምናኘው ጌታችን ወንጌልን እንዲሰብክ ባዘዘው መሠረት በብዙ አገሮች ውስጥ አስተምሮ ብዙዎችን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መልሷል። ታሪኩም እንዲህ ይነበባል፤ “ተጒዞም ወደ ከተማው መግቢያ ደጅ በደረሰ ጊዜ አንድ ወጣት ብላቴና አገኘ፤ ወደ ከተማው ለመግባት እንዴት እንደሚችል ጠየቀው፤ ወጣቱ ብላቴናም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ አንተ ግን ራስህንና ጽሕምህን ካልተላጨህ በእጅህም ዘንባባ ካልያዝክ መግባት አትችልም። ይህም ነገር ለሐዋርያ ማቴዎስ አስጨንቆት ሲያዝን አስቀድሞ ያነጋገረው ያ ወጣት ብላቴና ዳግመኛ በስሙ ጠራው። ሐዋርያውም ወዴት ታውቀኛለህ አለው፤ እርሱም እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ፤ አሁንም እንደ ነገርኩህ አድርግ፤ እኔም ከአንተ ጋር አለሁ፤ ከአንተም አልርቅም አለው።

ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዘው አድርጎ ወደ ካህናት አገር ገባ፤ ለአማልክት ካህናት አለቃቸው ከሆነ ከአርሚስ ጋር ተገናኘ፤ ከእርሱም ጋር ስለ አማልክቶቻቸው ተነጋገረና ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው እንዲህም አላቸው። ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉ ሌላውን እንዴት ያድናሉ፤ በዚያንም ጊዜ ከአርሚስ ጋር ብዙዎች ሰዎች አምነው አጠመቃቸው፤ ከሰማይም ማዕድ አውርዶ መገባቸው።

የሀገሩም ንጉሥ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከአርሚስ ጋር ሐዋርያውን ወደ እሳት ጨመረው፤ ጌታችንም አዳናቸው። ከዚህም በኋላ በሚአሠቃያቸው ነገር ሲያስብ እነሆ ልጁ እንደ ሞተ ነገሩት፤ እጅግም አዘነ። ሐዋርያ ማቴዎስም ልጅህን እንዲያስነሡት ወደ አማልክትህ ለምን አትለምንም አለው፤ ንጉሡም የሞተ ማንሣት እንዴት አማልክት ይችላሉ ብሎ መለሰ። ቅዱስ ማቴዎስም ብታምንስ የእኛ አምላክ ልጅህን ማሥነሣት ይችላል አለው። ንጉሡም ልጄ ከተነሣ እኔ አምናለሁ አለ፤ በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ክብር ይገባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና የንጉሡን ልጅ ከሞት አስነሣው።

ንጉሡም ክብር ይግባውና በጌታችን አመነ፤ የአገር ሰዎች ሁሉም አመኑ፤ የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው፤ ካህናትንም ሾመላቸው፤ ከዚህም በኋላ ወደ ሌሎች አገሮች ሂዶ ወንጌልን አስተማረ። ከዚህም አስቀድሞ በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስን ሁል ጊዜ በየበዓላቸው ወደ እነርሱ ሲመጣ አየው፤ ከእርሱም ጋር መቶ አርባ ሽህ ሕፃናት አሉ፤ መላእክትም ሁሉ በዙሪያው ቁመው ያመሰግኑታል።

በብሔረ ብፁዓን ስለ ሚኖሩ ወገኖችም ድንቅ ስለሆነ ሥራቸው ሁሉ ከሐዋርያው በኋላ ወደርሳቸው የገባ ዘሲማስ ቀሲስ ምስክር ሆነ። ከዚህም በኋላ የሐዋርያው የተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቀርብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ፤ ብዙዎችንም አሳመነ፤ አገረ ገዢውም ይዞ ከወህኒ ቤት ጨመረው። በዚያም አንድ እጅግ የሚያዝን እሥረኛ አይቶ ስለኀዘኑ ጠየቀው፤ እርሱም ብዙ የሆነ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሠጠመበት ነገረው፤ ሐዋርያ ማቴዎስም ወደ ዕገሌ ባሕር ዳርቻ ሂድ፤ ወርቅን የተመላ ከረጢትንም ታገኛለህ፤ ያንንም ወርቅ ወስደህ ለጌታህ ስጥ አለው።

ስለዚህም ድንቅ ተአምር ብዙዎች ክብር ይግባውና በጌታችን አመኑ። መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፤ ቅዱስ ማቴዎስንም ራሱን እንዲቆርጡ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉ አዘዘ። ከከተማውም አውጥተው ቈረጡት፤ ምእመናንም በሥውር መጥተው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩት።”

የሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት አይለየን፤ አሜን!

ምንጭ ፡-
• ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፤
• የመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ፤
• መጽሐፈ ስንክሳር፣
• ገድለ ሐዋርያት፡፡