‹እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ› ዘዳ 30፥19
በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
አምላካችን እግዚአብሔር በሥልጣኑ ገደብ የሌለበት ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ነው፡፡ ከሥልጣኑ ማምለጥ የሚችልም የለም፤ ሁሉ በእርሱ መግቦት፣ ጥበቃና እይታ ሥር ነው፡፡ በምድር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ሥልጣናቸው በድንበር፤ በጊዜ፤ በሕግ የተገደበ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በቦታና በጊዜ የተገደበ ሥልጣናቸውን ያለገደብ ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ ሥልጣናቸውና ኃይላቸው የፈቀደላቸውን ያህል ኅብረተሰቡን እንደ ሰም አቅልጠው፤ እንደገል ቀጥቅጠው በግርፋት፣ በቅጣት፣ እየተጠቀሙ ልክ ሊያስገቡት ያም ባይሆን ሊያዳክሙት መሞከራቸው የምድራዊ ገዢዎች ጠባይ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስና በታሪክ የምንረዳው ሀቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ገደብ የሌለው ሥልጣኑን በራሱ መግቦት ቸርነት፣ ምሕረት ገድቦ ሁሉን የሚያኖር አምላክ ነው፡፡
የሰው ልጅን ታሪክ ስንመረምርም ይህን እውነት መረዳት እንችላለን፡፡ አዳም የእግዚአብሔርን ሥልጣን (አምላክነትን) ሽቶ በዲያብሎስ ምክር ሕገ እግዚአብሔርን በጣሰ ጊዜ እግዚአብሔር ‹ሥልጣኔን ልትጋፋ አሰብህን? ብሎ በአዳም የፈረደበትን ፍርድ በራሱ ላይ አድርጎ ለመቀበል የፈጠረውን ሥጋ ተዋሕዶ በመከራው፣ በሞቱ አድኖታል፡፡ ይህም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በግድ ሳይሆን በነፃነት የሚገዛ አምላክ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከአዳምም በኋላ የሰው ልጆች እርሱን ከማምለክ ወደኋላ ሲሉና ለፍቅር አገዛዙ ሊመለስ የማይገባ ያለመታዘዝና የአመጽ አጸፋን ሲመልሱ የነጻነት እርምጃውን አልተወም። ሰውን ሁሉ እርሱን ወደ ማምለክና ለእርሱ ብቻ መገዛት የሚችልበት ችሎታ ሲኖረው ‹እሳትና ውኃን አቀረብኩልህ ወደ ወደድኸው እጅህን ስደድ› የሚል የነፃነት ጥሪን ከማቅረብ በቀር ምንም አላደረገም፡፡ ዛሬም ድረስ “እግዚአብሔር የለም” እስከማለት፤ በእርሱ ላይ እስከማፌዝና እስከመዘበት የሚደርሱ ብዙዎችን እየተመለከተ ዝም ማለቱ ማንም ሰው በፍላጎቱ ብቻ እርሱን እንዲመርጥ ስለሚፈልግ ነው፡፡ ‹ወደ እኔ ኑ! ወደ እኔ ቅረቡ› እያለ መጣራቱን ወደንና መርጠን በፈቃደኝነት ወደ እርሱ እንድንሄድ፤ ነፃነታችን ላለመንፈግ እንጂ እኛን ወደ እርሱ ማቅረብ ተስኖት የሚያደርገው የልምምጥ ጥሪ አይደለም፡፡ ይህን ሁኔታም አሁን ከምንረዳው በላይ በእግዚአብሔር ፊት በሞት እጅ ተይዘን በምንቀርብበት ጊዜ በይበልጥ የምንረዳው ነው፡፡
አንባብያን ሆይ! እግዚአብሔር አባታችን አዳምን በገነት ሳለ ዕፀ በለስን እንዳይበላ መከልከሉ ከሞላ ዛፍና ፍሬ አንዲት ዕፅ ተበልታ እርሱ የሚጎድልበት ሆኖ ነው? ወይስ ዲያቢሎስ ለሔዋን እንደነገራት አምላክ እንዳይሆን ነው? እንዲህ እንዳንል ደግሞ አዳም ዕፅዋን ሲበላ እንኳን አምላክነት ሊጨመርለት የነበረው ፀጋ ተገፍፎ ዕርቃኑን ቀርቶአል፡፡ ታዲያ ለእግዚአብሔር አንዲት ቅጠል ምን ልትረባው ነው አትብላ ብሎ የከለከለው? በንባብና በትምህርት ከምንደርስባቸው በርካታ ምክንያቶች በተጨማሪ የአዳም ነጻ ፈቃድ እንዲታወቅ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለአዳም ያለውን ፍቅር በመፍጠር፤ ሁሉን በመስጠት ከገለጠ አዳም ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅርስ በምን መለካት ይቻላል? አዳም ለእግዚአብሔር ሊሰጠው የሚችለው እግዚአብሔር ከሰጠው ነገር ሌላ አዲስ ነገር ምን አለ? ምንም የለም! አዳም ለአምላኩ ያለውን ፍቅር የሚገልጠው በምንም ቁስ አይደለም የመታዘዝና ያለመታዘዝ ነጻ ፈቃዱን ለእግዚአብሔር በመስጠት (በመታዘዝ) ብቻ ነበር፡፡ ዕፀ በለስም የዚህ ነጻ ፈቃድ መመዘኛ ነበረች፡፡ አዳም ግን ነጻ ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ አልፈቀደም። በነጻነት ከሚገዛው ፈጣሪ ይልቅ ረግጦ የሚገዛውን የዲያብሎስን አገዛዝ መረጠ፡፡
አንዳንዶች ‹ፈጣሪ የሰው ልጅ ኃጢአተኛ እንደሚሆነ እያወቀ፤ እያየ ለምን ኃጢአት እንዳይሠራ አላደረገውም? ይላሉ፡፡ ይሁንና እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ነጻ ፈቃድ የማይነካ የነጻነት ገዢ ነው፡፡ ደግሞም ሰው በበጎው መንገድ ብቻ እንዲሔድ ቢያስገድደው ኖሮ ‹ነጻነቴን ተነፈግሁ› ባለ ነበር፡፡ እንኳን ዕድሜያችንን ሙሉ በመንፈሳዊው አኗኗር ለመኖር በዕለተ ሰንበት በቤተ ክርስቲያን መጥተን ሥርዓተ ቅዳሴ እስከሚጠናቀቅ ለመታገስ ፈቃደኛ ያልሆንን ብዙዎች ነን፡፡
ወደ ሲኦል ወይንም ወደ ገነት መግባታችን የነጻነት አገዛዙ አካል ነው፡፡ አንዳንዴ ‹እግዚአብሔር እንዴት ሰው ወደ ሲኦል እንዲገባ ያደርጋል? ለምን ይጨክናል?› ብለን ባላወቅነው ልንፈርድ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር በምድር ሳለን ‹ይህን ብትፈጽሙና ብታደርጉ ገነትን ትወርሳላችሁ፤ ይህንን ብታደርጉ ደግሞ ሲኦል ትገባላችሁ ብሎ ሁለት አማራጮችን ሰጥቶናል፡፡ የምንመርጠው መንገድ የምንወርሰው ርስት ምን እንደሆነ ይወስነዋል፡፡ እግዚአብሔር ሁሉም ሰው ቢድን (ወደ ገነት ቢገባ) የሚወድ አምላክ መሆኑን ራሱ በቃሉ ተናግሯል፡፡ ይሁንና በምድር ሳሉ ሲኦል ለመግባት የሚያበቃቸውን መንገድ የመረጡ ሰዎችን ግን ከምርጫቸው ለይቶ ወደ ገነት መውሰድን የነጻነት አገዛዙ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህም ማንንም ማስገደድ የማይወድ አምላክ የሰው ልጅ በተሰጠው ነጻ ፈቃድ በምድር ሳለ የመረጠውን ርስት እንዲወርስ ያደርገዋል፡፡
የዚህ ጽሑፍ መሪ ጥቅስ የሆነው ቃልም ከላይ ለጠቀስነው ሀሳብ ምሳሌ የሚሆን የነጻነት ጥሪ ነው፡፡ ‹በፊታችሁ ሕይወትና ሞትን፤ በረከትና መርገምን እንዳስቀመጥኩ እኔ ዛሬ ሰማይና ምድርን ባንተ ላይ አስመሰክራለሁ፡፡ እንግዲህ ‹አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ› ዘዳ 30፥19
እግዚአብሔር ሕይወት የተባለች ሃይማኖትንና ምግባርን በእርስዋ ከሚገኘው በረከት ጋር፤ ሞት የተባለች ኃጢአትንና ርኩሰትን በእርስዋ ከሚመጣው መርገም ጋር በፊታችን አስቀምጧል፡፡ የምንወደውን የምንመርጥበት ነጻ ፈቃድ አለንና፡፡
የዚህ ምርጫ ታዛቢዎች ሰማይና ምድር ናቸው፡፡ ሰማይና ምድር ደግሞ በየትኛውም ዘዴ የማይታለሉና ንቁ ታዛቢዎች ናቸው፡፡ ወደ ሞት መንገድ እየሄድን የመረጥኩት ሕይወትን ነው ብሎ ማታለል አይቻልም፤ ሰማይና ምድር ይመለከታሉና፡፡ ኃጢአትን አብዝተን እየፈጸምን በመላ ሰውነታችን ርኩሰትን እየመረጥን የመረጥኩት ሕይወት ነው ብንል ከሰማይና ከምድር ዕይታ ውጪ የሰራነው ኃጢአት ስለሌለ እግዚአብሔር እነርሱን ምስክር ያደርግብናል፡፡ ብሎም በምድር በሰው ልጆች በሰማይ በመላእክት ያስመሰክርብናል፡፡ መላእክቱም ጠባቂዎቻችን ፤ የሰው ልጆችም አብረውን የሚኖሩ ናቸውና ሥራችንና ምርጫችን ምን እንደሆነ ለመታዘብ አይቸገሩም። እግዚአብሔር ታዛቢዎች አቁሞ ምረጡ ሲለን ምንም ነጻ ፈቃዳችንን ባይነካም፤ ብንሰማውም ባንሰማውን እንደ አባትነቱ የቱን ብንመርጥ እንደሚሻለን ይመክረናል ‹እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ› በማለት፡፡
ሕይወትን ምረጡ ሲል ወደ ሞት የምትወስደውን የኃጢአት መንገድ ትታችሁ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የምትወስደውን የሃይማኖትና የጽድቅን መንገድ ተከተሉ ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ቤት መራቅና ዓለማዊ ተድላ ደስታን ብቻ ማሳደድ ሕይወትን አለመፈለግ ነው፡፡ ወደዚህች ቅድስት ስፍራ የሚመጣ ሁሉ ሕይወት የሆነ አምላክን ከእርሱም የሚገኘውን መንፈሳዊ ስጦታ ሁሉ ያገኛል፡፡ እግዚአብሔር ሕይወትን ምረጡ ማለቱ በሌላው ምርጫችን የሚደርስብንን ክፉ ነገር ሁሉ እንዳናይ በማሰብ ነው፡፡
ውድ አንባብያን! ቀጣዩን አንቀፅ ከማንበባችን በፊት እስቲ ቆም ብለን ‹ባለፈው የሕይወት ዘመናችን መርጠን የነበረው መንገድ የሕይወት ነው? ወይስ የሞት?› በማለት ራሳችንን እንጠይቅ የብዙዎቻችን ሕሊና የሚነግረን ምርጫችን የጥፋት መንገድ እንደነበረ ነው፡፡ ከነፍሳችን ይልቅ ለሥጋችን፤ ከሕይወታችን ይልቅ ለሞታችን፤ከልማታችን ይልቅ ለጥፋታችን ስንደክም መኖራችን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የደጋግ ቅዱሳን አባቶች መፍለቂያ የሃይማኖትና የምግባር መነኻሪያ በነበረችው ቅድስት ሀገራችን ያለአንዳች እፍረትና ፍርሃት ተከፍሎ የሚያልቅ፤ የማይመስል የኃጢአት ዕዳ ሲከማች እንደዋዛ መታየቱ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ቢል የብዙ ኢትዮጵያውያን እጅ ግን ወደ ሌላ አቅጣጫ መዘርጋቱን የሚያመለክት ነው፡፡ ለመንፈሳዊ አገልግሎትና ለሥራ ዳተኛ የሆነ ሁሉ ለዝሙትና ለዳንኪራ ያለስስት ገንዘቡን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን ሲሰጥ በመንፈሳዊ ዓይን ለሚመለከተው ሰው እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡
ክርስቲያኖች፣ በዚህ ዲያብሎስና የዓለም ጠባይ ሰውን ሁሉ ከሃይማኖትና ከምግባር ለማውጣት፤ የተቀደሰ ኢትዮጵያዊ ባሕሉን፤ ማንነቱንና ሥርዓቱን ለማጥፋት ታጥቀው በተነሱበት ጊዜ ‹ሕይወት ምረጡ› የሚለው አዋጅ እጅግ ተገቢ አይደለም ትላላችሁ? ስለዚህ ነው ፈጣሪ እያንዳንዱ ክርስቲያን ‹ወደ ሌላው ሰው በደል መጠቆምና ማመካኘት ትተህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ› በሚለው ቃል ራስን ለመመርመር ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ሕይወትን የሚመርጡ ሁሉ የሚገቡባት በር ናት፡፡ ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያን ስላሉ ሰዎች መጥፎ ወሬን ቢሰሙ እንኳን እንደ ተራ እንቅፋት ቆጥረው በጽናት መቀጠል ለክርስቲያኖች ይገባቸዋል፡፡ ያለፉት የኃጢአትና የርኩሰት ዓመታት በንስሐ በማጠብ ወደ ሥጋ ወደሙ መቅረብ ፤ ሕይወትን መምረጥ ፤ብሎም በሕይወት መኖር ነው፡፡
የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብሎ ይህንን የሕይወትና የሞት ምርጫ ለመምረጥ ልዩ መሥፈርት የለውም ክርስቲያንነት ብቻ በቂ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም መንፈሳዊውን መንገድ መርጠን መኖር ጀምረን በድክመታችን ያቋረጥነው ሰዎችም አሁን ዳግመኛ ሕይወትን መርጠን በሕይወት ከመኖር አንከለከልም፡፡ አውራጣታችንን ይዞ ቀለም እየቀባ ‹እናንተ ከዚህ በፊት መርጣችኋል ድጋሚ መምረጥ አትችሉም!..›የሚል ከልካይ በቤተ ክርስቲያን የለም፡፡ ዲያብሎስ ግን «ጠፍቼ ጠፍቼ እመለሳለሁ?» እንድንል ወደ ኋላ ሊስበን ይሞክራልና ሕይወትን በመምረጥ የክርስቶስን መንገድ በመያዝ እናሳፍረው፡፡
የእግዚአብሔር ሁሉን የመቀበል፣ ይቅር የማለት ባህርይ የእኛን ድኅነት ከመሻቱ ነውና የተዘረጋልንን የምሕረት እጅ ቸል ብንል እንቀጣለን። ነገሩም እንዲህ ያለውን መዳን ቸል ብንል የሚብስ ቅጣት የሚገጥመን አይመስላችሁም? እንዳለው ነው። እርሱ ይቅር ማለት ሳይታክተውና እኛ ይቅር መባልና ይቅር በለኝ ማለትን ልንጠላ አይገባንም።
እግዚአብሔር መጪውን ጊዜ የንስሐ፤ የስምምነት፣ የፍቅርና መደማመጥ የሞላበት የአገልግሎትና የመንፈሳዊነት ዘመን ያድርግልን! አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር