የዐቢይ ጾም ስብከት (ክፍል 3)
የካቲት 24/2004 ዓ.ም.
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር ከእናቱ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ከአሥራ ሁለት ሐዋርያቱ ጋር በዶኪማስ ቤት ሠርግ ተጠርቶ ነበር፡፡ በዚያም ወይን ጠጅ አልቆባቸው አፍረውና ተሸማቀው የነበሩትን ጋባዦች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ውኃውን የወይን ጠጅ አድርጎ በመቀየር ከዕፍረት አድኗቸዋል፤ ክብሩን በመጀመሪያ ተአምሩ ገልጧል፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አምነዋል፤ዮሐ 2፥1-11፡፡
ጌታችን ከዚህ በኋላ የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ስለ ነበር የሔደው ወደ ኢየሩሳሌም ነበር፡፡ በዚያ የተመለከተው ነገር ግን በዶኪማስ ሠርግ ቤት ውስጥ ከተመለከተው የአክብሮት ጥሪና መስተንግዶ ጋር ሲነጻጸር ፍጹም ተቃራኒ ነበር፡፡ ጌታ ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ በኋላ በቀጥታ ያቀናው ወደ ቤተ መቅደስ ነው፡፡
በእኛ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እኛ ከአንዱ ከተማ ተነሥተን ወደ ሌላው ከተማ ስንደርስ ወይም ገና ካለንበት ከተማ ከመነሣታችን በፊት ቅድሚያ ሰጥተን የምናጣራው ወይም የምንጠይቀው ጉዳይ በከተማይቱ ውስጥ ስላለው የተሻለ መኝታ፣ ጥራት ስላለው ምግብና መጠጥ እንዲሁም ተመራጭ ስለ ሆነው ገላ መታጠቢያ ቤት ነው እንጂ በከማይቱ ውስጥ ስላሉት የተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት፣ በዚያ ስለሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም ስለሚገጥሙአቸው የዲያብሎስ ውጊያዎች አይደለም፡፡ ስለሆነም እኛ ከአንድ ከተማ ተነሥተን ወደ ሌላ ከተማ ስንደርስ አስቀድመን ልንጠይቃቸው ስለሚገቡን አንገብጋቢ ጉዳዮች እንድንጠይቅና ወደዚያ ከተማ እንድንደርስ ያበቃንን አምላክ እናመሰግን ዘንድ በመጀመሪያ መሔድ የሚገባን ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሆኑን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያስተምረን ወደ ቤተ መቅደስ ሔዷል፡፡
የአይሁድ የፋሲካ በዓል አይሁድ በኀጢአታቸው ምክንያት በግብጽ ምድር ለ430 ዓመታት በባርነት በግፍ ሲገዙ ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ እነርሱን በነቢዩ በሙሴ አማካይነት በኀይልና በተለያዩ ተአምራት በማውጣት ይህን የዘላለም መታሰቢያ እንዲሆናቸው አድርጎ የሰጣቸው ታላቅ የመሻገር በዓል ነው፤ ዘጸ 12፡፡ አይሁድ ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር በዓል ሊከበር በቀረበበት አጭር ጊዜ ውስጥ ስለ በዓሉ አከባበር እና ሊከናወኑ በሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ላይ ባተሌ መሆን ሲገባቸው ለምስጋና፣ ለጸሎት፣ ለተመስጦ፣ ለስግደት፣ መባ ለማቅረብና ለሥርየት በታነጸው ቤተ መቅደስ ውስጥ በሬዎች፣ በጎችና ርግቦች በማስገባትና ከሕዝቡ ጋር ሲነጋገዱበትና ጥቁር ገበያ አድርገው ገንዘብ ሲለዋወጡበት ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ ያገኛቸው፡፡ ሊያደርጉ የማይገባቸውን ነገር ሊያደርጉ በማይገባቸው ቦታ ላይ ሲያደርጉ ነው ያገኛቸው፡፡ ምስጋና፣ ጸሎት፣ ተመስጦ፣ ስግደት፣ መባ ማቅረብና ሥርየት ማግኘት ከዋጋ ውጣ ውረድ፣ ከቀንስ አትቀንስ ክርክር፣ ከጫጫታ፣ ከንጥቂያ፣ ከስድብና ከድብድብ ጋር ምንም ዓይነት መስማማት የለውም፡፡ የቤተ መቅደስን ንጽሕና መጠበቅና ቤተ መቅደስን በከብቶች አዛባና ሽንት ማቆሸሽ ፍጹም የማይገናኙ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ጸሎትና ምስጋና በዋጋ ክርክርና በሁካታ መተካቱ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ እኩይ ተግባር ነው፡፡
ዛሬም እንዲሁ ነው፡፡ አንዳንዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡ በኋላ ስለ ንግድና ስለ ገንዘብ ልውውጥ እንዲሁም ገንዘብ ስለሚገኝበት ሁኔታ መከራከራቸውና መንጫጫታቸው ከአይሁድ ክርክርና ጫጫታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ዛሬ ምስጋና ለማቅረብ፣ ጾም ለመያዝ፣ ስግደት ለመስገድ፣ በተመስጦ ለመቆየት፣ መባ ለማቅረብና ኀጢአትን ለንስሓ አባት በመናዘዝ ሥርየት ለማግኘት ክርስቲያን ተብለው የተጠሩ አማኞች እግዚአብሔርን ለማገልገል ይህን ያህል ገንዘብ ክፈሉን፣ የላመና የጣመ ምግብና መጠጥ አቅርቡልን፣ የተደላደለ መኝታ አንጥፉልን፤ድምፃችንን እጅግ አጉልታችሁ አሰሙልን፤ይህን ካላደረጋችሁልን ወይም ይህን ካልከፈላችሁን አናገለግልም እያሉ ሲታበዩ ማየትና መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ አልፎ ተርፎ በቤተ መቅደስና በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነገር ቀንስ-አትቀንስ ሁካታና ጫጫታ ለመደራደር መሞከር ከአይሁድ ተግባር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ የኢየሱስ ክርስቶስን የቁጣ ጅራፍ የሚያስነሣ ተግባር ነው፤በማይገባው ቦታ ላይ የሚፈጸም የማይገባ ተግባር ነውና፡፡
ባቀረበው ምስጋና፣ ባደረሰው ጸሎት፣ በሰገደው ስግደት፣ በጾመው ጾም፣ በያዘው ንስሓና በሰጠው መባ ተባርኮ፣ ተቀድሶና ሥርየት አግኝቶ በደስታ ወደ ቤቱ መመለስ የሚገባው ምእመን ገንዘብ የሚገኝበትን ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የገንዘብ መድረክ ስለሚገኝበት ሁኔታ ወይም የእግዚአብሔርን ቤት የንግድና የኑፋቄ ቤት ለማድረግ በመሞከር ተከራክሮና ተንጫጭቶ፤ተጣልቶና ተኮራርፎ መለያይት የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ አይሁድ በቤቱ ውስጥ ለፈጸሙት እኩይ ተግባር በንስሓ ተመልሰው ጌታን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ጭራሽ ለደረሰባቸው ቅጣት እርሱን ምልክት መጠየቃቸው አሳዛኝም አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን በጥምቀት ልጅነትን፣ በሜሮን መታተምን፣ በንስሓ ሥርየትን፣ በእምነት መንግሥተ ሰማያትን ያሰጠችና የምታሰጥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የንግድ ቤት ለማድረግ ሞክረው ያልተሳካላቸው ሰዎች ከጥፋት በፊት ይቅርታ እንዲጠይቁ ታሳስባለች፡፡
ይህ ስለሆነ ነው የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቁጣ በእነዚህ ሰዎች ላይ እጅግ የነደደው፡፡ ከዚህ በኋላ ጅራፍ አበጅቶ ይሻሻጡና ይለዋወጡ የነበሩትን ሰዎችና የሚሸጡትን በሬዎች፣ በጎችና ርግቦች እየገረፈ ከቤቱ ካስወጣ በኋላ የለዋጮችን ገበታዎች ገለባብጦባቸዋል፤ የሚለዋወጡባቸውን ገንዘቦችም በታትኖባቸዋል፡፡ ይህን ከማድረጉ በፊት ግን «የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት፡፡» በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቶአቸዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በከፍተኛ ቅንዓት ይህን ሁሉ ነገር ሲያከናውን አብረውት የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ያሰላስሉና ያስቡ የነበረው አባታቸው ቅዱስ ዳዊት ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅንዓት በትንቢት መነጽር የተመለከተው ትንቢት መፈጸሙን ነበር፡- «. . . ቤትህ ቅንዓት ይበላኛል፤» (መዝ 68፡9) የሚለው፡፡ ከዚህ በኋላ እነዚህ እኩያን አይሁድ ያደረገውን ነገር በምን ሥልጣን እንደሚያደርግ ይህን ለማድረጉም ምን ዐይነት ምልክት ሊሰጣቸው እንደሚችል ሲጠይቁት «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስት ቀንም አፈርሰዋለሁ . . .» (ዮሐ 2፡19) በማለት ለእነርሱ ያልገባቸውን ነገር ስለ ገዛ ራሱ ሞትና ስለ ትንሣኤው በቤተ መቅደሱ መስሎ ነግሯቸዋል፡፡ ይህን አባባሉንም አብረውት የነበሩት ሐዋርያቱ ጌታ ከሙታን መካከል ከተነሣ በኋላ በመጽሐፍ የተጻፈውንና ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገውን ነገር በማሰብ በእርሱ አምነዋል፡፡ አይሁድ ግን ያደረጉት ክፉ ሥራ ሳያንሳቸው ለምልክት ጥየቃ ተመልሰው ወደ እርሱ በመምጣታቸው ለጥፋት ተዳርገዋል፡፡
አንድም ቤተ መቅደስ ተብሎ የተጠራው ይህ የእኛ ሰውነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሁኔታ በመልእክቱ መላልሶና አስረግጦ ገልጦታል፡- «የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ያውም እናንተ ናችሁ፡፡» 1ኛ ቆሮ. 3፥16-17፤1ኛ ቆሮ. 6፥19-20፡፡ ሰው የራሱ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚኖረውና ሊኖር የሚገባው ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚኖረውም እኛን በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ወይም በዋጋ ስለ ገዛንና መልሶ የራሱ ስላደረገን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ በላይ እኛን በመልኩና በምሳሌው የፈጠረን በእኛ ውስጥ ስለሚያድርና እኛን ቤተ መቅደሱ ስላደረገን ነው፡፡ ይህ በመሆኑም እኛም ይህን አክበሮ፣ ባርኮና ቀድሶ የሰጠንን ቤተ መቅደስ ያለ ምንም ዕድፈትና ቆሻሻ በቅድስናና በንጽሕና ልንጠብቀው ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይሁድ እንዳደረጉት በከብቶች አዛባና ሽንት ሊቆሽሽ አይገባውም፡፡ አዛባና ሽንት የተባለው ኀጢአትና በደል ነው፡፡ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖት ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት. . . ወዘተ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይኸውም እኛን የሚያቆሽሽ አዛባ ነው፡፡
እግዚአብሔር ደግሞ በቆሸሸ ቤት ውስጥ አይኖርም፡፡ የምንኖርበት ምድራዊ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ሲቆሽሽ ደስ እንደማይለን ሁሉ እኛም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ (ራሳችንን) ስናቆሽሽ እግዚአብሔርን እንደማናስደስተው በማወቅ በንስሓ ልናጸዳው ይገባናል፡፡ እኛ ይህን ሰውነታችንን ወይም ይህን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በተለያዩ የኀጢአት ዐይነቶች የምናፈርሰው ከሆነ እግዚአብሔር ደግሞ አፍራሾቹን እኛን ያፈርሰናል፡፡ ዛሬ ብዙዎች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ወይም ሰውነታቸውን በተለያዩ ክፉ ቅጠሎች ማለትም በትንምባሆ፣ በሺሻና በጫት እያፈረሱት ነው፡፡ ከልክ ባለፈ መጠጥና በዝሙትም እያፈረሱት ነው፡፡ በሀሜትና በአሉባልታም እያፈረሱት ነው፡፡ በሐሰትና በስርቆትም እያፈረሱት ነው፡፡ እጅግ ብዙ የሚታገሥ እግዚአብሔር ደግሞ በንስሓ ካልተመለሱ እነርሱን አንድ ቀን ያፈርሳቸዋል፡፡ እርሱ ዛሬ ለአይሁድ ያነሳውን የገመድ ጅራፍ በእኛ ላይ በድጋሚ ለማንሣት ድጋሚ ይወለድ ዘንድ አይመጣም፤ በፍርድ ቀን በእሳት ጅራፍ ለመግረፍ እንጂ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ብዙዎች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስን በተለያየ ምክንያት ሲያፈርሱ ለሚመለከት ሰው መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ «ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?» (1ኛ ቆሮ 6፡19) በማለት በጻፈው የተግሣፅ ቃል ላይ በተመስጦ እንዲቆይ ያደርገውና በሰዎች አለማወቅ እንዲያዝንም ሆነ እንዲያለቅስ ያደርገዋል፡፡ «አታውቁምን?» የሚለው ቃል የእኛን አለማወቅ ያጎላብኛል፡፡ ይኸው ሐዋርያ «አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤. . .» (1ኛ ቆሮ 2፡8) በማለት ተናግሯል፡፡ ይህ ኀይለ ቃል ለአይሁድ ብቻ የተነገረ የሚመስለን ከሆነ ዛሬም እኛ አላወቅንም ማለት ነው፡፡ እነርሱ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ብዙዎቻችን ግን ኀጢአት በሠራን ቁጥር በሥራችን ብዙ ጊዜ መላልሰን እየሰቀልነው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ብዛት ያላቸው የኀጢአት ሥራዎችን ሲሠሩ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነ ሰውነታቸው እየሰቀሉትና እያፈረሱት መሆናቸውን በትክክል ቢያውቁ ኖሮ ከዚህ ክፉ ሥራቸው በታቀቡ ነበር፡፡ ባለማወቃቸው ግን የራሳቸውን፣ የሌሎችንና የእግዚአብሔርን አብያተ መቅደሰ እያፈረሱ ነው፤ በማፍረሳቸውም እግዚአብሔር እነርሱን እያፈረሳቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የምንታነጽ እንጂ የምንፈርስ ከመሆን ያድነን፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን፡፡
ይቆየን፡፡
በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡