የትንሣኤ የማሕሌት ምንባብ 3 (ሉቃ.24፥1-13)

ከሳምንቱም በመጀመሪያዪቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ ያቺንም ድንጋይ ከመቃብሩ ላይ ተንከባልላ አገኙአት፡፡ ገብተውም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም ስለዚህም ነገር የሚሉትን አጥተው ሲያደንቁ ሁለት ሰዎች ከፊታቸው ቆመው ታዩአቸው፤ ልብሳቸውም ያብረቀርቅ ነበር፡፡ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀረቀሩ፡፡ እነርሱም እንዲህ አሉአቸው፥ “ሕያዉን ከሙታን ጋር ለምን ትሹታላችሁ? በዚህ የለም፤ ተነሥቶአል፡፡ በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንዲህ ሲል የተናገረውን ዐስቡ፡- የሰው ልጅ በኀጢአተኞች ሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይሰቅሉታል፤ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፡፡” ቃሉንም ዐስቡ፡፡ ከመቃብርም ተመልሰው ለዐሥራ አንዱና ለቀሩት ባልጀሮቻቸውም ይህን ለሐዋርያት ነገሩአቸው፡፡ ይህም ነገር በፊታቸው እንደ ተረት መሰላቸውና አላመኑአቸውም፡፡ ጴጥሮስም ተነሣ፤ ወደ መቃብርም ፈጥኖ ሄደ፤ ዝቅ ብሎም በተመለከተ ጊዜ በፍታውን ለብቻው ተቀምጦ አየ፤ የሆነውንም እያደነቀ ተመለሰ፡፡
በዚያም ቀን ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደምትርቀው ኤማሁስ ወደምትባለው መንደር ሄዱ፡፡