ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱስ ኤፍሬም ክፍል 3

ኅዳር 28/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

በዚህ ክፍል ቅዱስ ኤፍሬም በቅድስት ድንግል ማርያም የተፈጸመውን የተዋሕዶ ምሥጢር በማድነቅና በማመስገን የጻፈውን የቅኔ ድርሰት እንመለከታለን፡፡

  1. ጌታ ሆይ አንተን ምን ብሎ መጥራት እንዳለበት የሚያውቅ ሰው ማን ነው?

    ጌታ ሆይ እናትህን ድንግል ብለን እንጥራትን?

    እንዲያ ብለን እንዳንጠራት የአንተ እናት መሆኑዋ ምስክር ይሆንብናል፤

    ጌታ ሆይ እናት እንበላትን? እንዲህ እንዳንል ወንድ የማታውቅ ድንግል ናት፤

    የእናትህ ነገር ለመረዳት የረቀቀ ከሆነ አንተን ሊረዳ የሚችል ሰው ማን ነው?

    ሁሉን በቀላሉ የምታከናውን የሁሉ አስገኝ የሆንክ ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፡፡እርሱዋ ብቻ ያንተ እናት ናት፤

  2. ከሁሉ ጋር ደግሞ እኅትህም ናት፤ ስለዚህም እርሱዋ ለአንተ  እናትም፣ እኅትም፣ ሙሽራም ሆናለች፤

    እንደሌሎች ቅዱሳኖችህ፤ የእናትህን ደም ግባት ገንዘብህ ያደረግህ አንተ እርሱዋን በበረከት ሁሉ አስጌጥኻት፡፡አንተ ወደ እርሱዋ ከመምጣትህ በፊት ቅድስት ድንግል ማርያም በልማዳዊ መንገድ ይጠብቃት ዘንድ ለዮሴፍ ተሰጠች፤

  3. አንተ ወደ እርሱዋ ከመጣህ በኋላ ግን ከተፈጥሮአዊ ሥርዐት ውጪ አንተን በድንግልና ፀነሰችህ፤

    አንተ ብቻ ቅዱስ የሆንክ ጌታ ሆይ እርሷ አንተን ቅዱስ በሆነ ልደት በድንግልና ወለደችህ፤ጌታ ሆይ  ቅድስት እናትህ ድንግል ሳለች አንተን ፀንሳ በመውለድ እናትህነትን ገንዘቡዋ አደረገች፤

  4. ድንግል ሆና ሳለች ከጡቶቹዋ ወተት ፈሰሰ፤

    ድንግል ከሆነች መሬት ንጹሕ ምንጭ እንዲፈልቅ፤

    እንዲሁ ድንግል ከሆነችው እናትህ ጡቶች ወተት ፈለቀ፡፡እርሱዋ አንተን ብትሸከምህ አንተ ጽንዕ ሰጥተሃት ነው፤

  5. በተራብክ ጊዜ አንተን ከጡቶቹዋ ትመግብህ ዘንድ፣

    ነቢዩ ዳንኤል በታላቅ ተራራ የመሰለህ አንተን አንደ ሕፃናት ታቀፈችህ፤

    በፈቃድህ የተጠማህ አንተን በእጆቹዋ በፍቅር ትዳብስህ ዘንድ፤

    የምህረት እሳት የሆንኽ አንተ ክንዶቿን መለኮታዊው እሳት እንዳይቃጥላቸው ጠበቅኻቸው፡፡ጌታ ሆይ እናትህ ግሩም የሆኑ ተአምራት የተፈጸሙበት መካን ናት፤

  6. ወደ እርሱዋ የሁሉ ጌታ የሆነው ገባ፤ የአገልጋዩን አርአያ ነስቶ ተወለደ፤

    የእግዚአብሔር ቃሉ የሆነ እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ ዝምተኛ ሆኖ ተወለደ፤

    ነጎድጓድ የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ ፤ጭምት ሆኖ ተወለደ፤

    እረኛ የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ በግ ሆኖ በመወለድ በአባግዕ ቋንቋ ተናገረ፡፡ጌታ ሆይ የእናትህ ማኅፀን ከተፈጥሮአዊው ሥርዐት በተቃራኒው ፈጸመ፤

  7. ሁሉን ያከናወነ በባለጸግነቱ ወደ እርሷ ገባ፤  ደሃ ሆኖ ተወለደ፤

    ከሁሉ በክብር የሚልቀው እርሱ ወደ እርሷ ገባ፤ ትሑት ሆኖ ተወለደ፤

    በክብሩ ገናና የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ የባሪያውን መልክ ይዞ ተወለደ፤ብርቱ የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ሕፃን ሆኖ በማኅፀን ተገኘ፤

  8. ፍጥረትን ሁሉ የሚመግበው መራብንና መጠማትን ገንዘቡ አደረገ፤ (አጣጣመ)

    ሁሉን በበረከቱ የሚያለብሰውና የሚያስጌጠው እርሱ ራቁቱን ተወለደ፤

    እኛን ለማዳን ሲል የእኛን ተፈጥሮ ገንዘቡ ላደረገ ለእርሱ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡