የምኩራብ ወንጌል(ዮሐ. 2÷12-ፍጻ. )
ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ÷ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡
የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን÷ ርግቦችንም የሚሸጡትን÷ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን÷ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡ ርግብ ሻጮችንም÷ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም÷ “የቤትህ ቅናት በላኝ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ፡፡
አይሁድም መልሰው÷ “ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳያለህ?” አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም÷ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው፡፡ አይሁድም÷ “ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?” አሉት፡፡ እርሱ ግን ይህን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለ ተባለ ሰውነቱ ነበር፡፡ ከሙታን በተነሣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደ ነገራቸው ዐሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃልና ጌታችን ኢየሱስ በነገራቸውም ነገር አመኑ፡፡
ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳለም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በስሙ አመኑ፡፡ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ግን አያምናቸውም ነበር፤ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና፡፡ የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም፤ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡