“መኑ ውእቱ ገብር ኄር” “ታማኝ አገልጋይ ማነው”? ማቴ.24፥45
ሚያዚያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ር ምስጢረ ሥላሴ ማናየ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ ሰያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ጾመ ድጓ በተባለው ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በሆነው ጾመ ድጓ መጽሐፍ ሳምንቱን የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን፡- የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብርኄርን የሚያወሳ ነው ማለት ስለ ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ በማቴ.25፥14-25 የተገለጸውና በዕለቱ የሚነበበው ወንጌልም የሚነግረን ይህን ነው፡፡
“አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሄደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ አስር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ አለው፡፡ “ገብርኄር ወምዕመን ዘበሁድ ምዕምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍስሐሁ ለእግዚእከ” “አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፡፡ “አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡
አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ቀርቦ “ጌታዬ አንተ ክፉና ጨካኝ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ እንደሆንክ ስለአወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ” አለው፡፡ “አንተ ሰነፍ ባሪያ መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር”፡፡
ንዑ የዚህን ሀኬተኛ መክሊት ውሰዱና አስር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል፡፡ ንዑ ይህን ሰነፍና ሃኬተኛ ባሪያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑዕ ጨለማ ወደአለበት ውሰዱት ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት” አለ ማቴ.25፥14-25፡፡
ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት በዕለተ ምጽአት ለሁሉም በአገለገለው አገልግሎት ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡
ያገለገሉትን ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፎች ደግሞ ጥርስ ማፋጨት ስቃይ ጽኑዕ ጨለማ ባለበት ሲዖል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል፡- “ታማኝ አገልጋይ ማነው”? ይህ እያንዳንዱ በአርዓያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው የዚህን አምላካዊ ጥያቄ መልስ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡
1. ታማኝ አገልጋይ ማነው? ሙሴ ነው፡፡
ሙሴ ታማኝ አገልጋይ ነበር ታማኝ አገልጋይ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ “በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በህልም አናግረዋለሁ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው” ዘኁ.12፥6፡፡ ይህ የፍጡር ምስክርነት ሳይሆን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በዕውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይሆን? እንጃ የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረሃ፣ ስደት፣ መከራ፣ የፈርዖን ግርማ እና ቁጣ ያልበገረው አርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ አርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል የቀኑ ሀሩር የሌሊቱን ቁር/ ብርድ/ ታግሶ በታማኝነት አገልግሏል፡፡ ታማኝነቱ እስከሞት ነበር፡፡
“ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶ ወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኀጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ ከባለሟልነትህ አውጣኝ /ዘጸ.32፥31፡፡ አያችሁ ታማኝ አገልጋይ እኔ ልሙት ሌሎች ይዳኑ የሚል ነው አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሰዎች ይሙቱ እኔ ልኑር ሰዎች ጦም ይደሩ እኔ ልብላ ሰዎች ይራቆቱ እኔ ልልበስ ሰዎች ይዘኑ እኔ ልደሰት ነው፡፡ ይህ ታማኝ አገልጋይ ያለመሆን መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡ ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ግን “ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ” የሚባለውን መሰል ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሪፖርት የሚያቀርቡ፣ የሚወደሱ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መክፈል የማይሹ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይሆን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾሁን፣ መከራውን ውጣ ውረዱን ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ ሌሎች በጭልፋ የሚቆነጥር አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው መና ያወረደው ደመና የጋረደው ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከብሮበታል ተመስግኖበታልም፡፡
2. ታማኝ አገልጋይ ማነው? ዳዊት ነው፡፡
ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲያገለግል እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃ መርጦ በተሰጠው ሥልጣን ያልተመነ የሳዖልን በትረ መንግሥት በሳሙኤል እጅ ተቀብቶ ተቀብሏል፡፡
በተሰጠው ሥልጣን በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ ታማኝነቱንም እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረለት ለእርሱም መስክሮለታል፡፡
“እግዚአብሔር እንደልቡ የሆነ ሰው መርጧልና” የዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተልሔም እልክሃለሁ” 1ሳሙ.13፥13፣ 16፥2፡፡
“ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ” እንዲል መዝ.88፥20፡፡ “ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት” ይህን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰዓታት በተባለው ድርሰቱ፡- “ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብዕሴ ምዕመነ ዘከመልብየ” አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን ሆኖ አገኘሁት ሲል ተርጉሞታል፡፡ የተገኘው በታማኝነት ነበር ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንሆንና ሀብት ሹመት ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ መዋሸት ሥልጣኔ ይሆንልናል፡፡ ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን ያስጥለው ነበር፡፡
“እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር ከመንጋውም ጠቦት ይወሰድ ነበር በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር ከአፉም አስጥለው ነበር በተነሳብኝም ጊዜ ጉረሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይሆናል እንግዲህ እገድለው ዘንድ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል” አለ 1ሳሙ.17፥34፡፡
ዛሬስ ቢሆን በእስራኤል ዘነፍስ በምዕመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል እነዚህን ድል የሚነሣ በጎቹን ምዕመናን ከተኩላ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል ብሎ የሚታመን የኢአማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ሆነ ከመንፈሳዊያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው በሙስና ያልተዘፈቀ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚሆን ሰው ታማኝ አገልጋይ ማለት ያ ነው፡፡ በመኀላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ ዳኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ ወታደር፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛ ታማኝ መሆን አለበት፡፡
መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ ታማኝ አይደለም ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና ቆይ ሻይ ልጠጣና የሚል ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል ድሆችን የሚበድል ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡
ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ በርበሬ በገል ጨምሮ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ እንደእየ አቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መሆን አለበት፡፡
3. ታማኝ አገልጋይ ማን ነው? ዮሴፍ ነው፡፡
ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ያልበላ በትንሽ የታመነ ሰው ነበር፡፡ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጴጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፡፡ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡
“ዮሴፍ ተሸጠ አገልጋይም ሆነ እግሮቹ በእግር ብረት ስለሰሉ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው ንጉሥ ላከ ፈታውም የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው የቤቱም ጌታ አደረገው በገንዘቡ ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገስጽ ዘንድ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ” መዝ.104፥17፡ በዚህ ሁኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣ ባቱን ሲገባ ደረቱን እያየች ዐይኗን ጣለችበት በዝሙት አይን ተመለከተችው፡፡
“የጌታውም ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለችበት ከእኔም ጋር ተኛ አለችው እርሱም እምቢ አለ፡፡ ለጌታው ሚስቱ እንዲህ አላት እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ሁሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም በዚህ ቤት ከአኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስት ስለሆንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ ይህን ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር” ዘፍ.39፥7፡፡
በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፡፡ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ሁሉ ተረክቦ ነበር የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ይህን በታማኝነቱ ማለፍ ችሏል፡፡ ዛሬ በእየአንዳንዱ ጓዳ እንደ እሳት የሚያቃጥሉ አገልጋዮች ናቸው ያሉት ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉ ናቸው የሚበዙት እንኳን በሁሉ ገንዘብ ለመሾም አይደለም፡፡ በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ጠፍቷል፡፡ ዮሴፍ ግን በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰር እንኳ ያለ ሹመት አላደረም የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብፅን በሙሉ መርቷታል፡፡ በግብፃውያን በሙሉ ተሾሟል በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ “በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል” እንዲል ማቴ.25፥24፡፡
ጌታውም መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለሆንህ በብዙ እሾምሀለሁ” ከነዚህ ሦስት ታማኝ አገልጋዮች ሕይወት ሁሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መሆን መጀመሪያ የሚጠቅመው ለራስ ነው ከዚያ በኋላ ለሀገር ለወገን ለቤተ ክርስቲያን ላመኑት ላላመኑት ሁሉ ይጠቅማል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ያቀዳጃል መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራል፡፡
ጻድቃን ሠማዕታት ቅዱሳን በታማኝ አገልግሎታቸው ፈጣሪያቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡ በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት ይሁዳ፣ ሐናንያ፣ ሰጲራ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፡፡ በአካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል ሐዋ.5፥1፣ 1፥25፡፡
ለዚህ ነበር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ አድነኝ ደግ ሰው አልቋልና ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና” መዝ.11፥1፡፡ ስለዚህ ሁሉም በአለበት ያአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ “አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ” የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል መስማት ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን መንግሥቱን እንድንወርስ “ገብርኄር” እንድንባል አምላካችን ይርዳን፡፡