ገነትህን ጠብቅ ዘፍ.2፡15
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.
ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መላክ
በምዕ/ጎጃም ሀገረ ስብከት
የ፬ቱ ጉባኤያት መምህር
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ካሰለጠነባቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ ኤዶም ገነት ነች፡፡ ታላቁ መጽሐፍ እንደሚነግረን “እግዚአብሔር አምላክም በስተምስራቅ ኤዶም ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው በዚያ አስቀመጠው” ካለ በኋላ ገነትን እንዲጠብቃትና እንዲንከባከባት ሓላፊነትን ሰጥቶታል፡፡
ገነት የአራቱ አፍላጋት መነሻ ሰው ከፍሬው ተመግቦ ለዘለዓለም ሕያው የሚሆንበት የዕፀ ሕይወት መገኛ ነበረች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው አትናቴዎስ በቅዳሴው ስለገነት ውበት ሲገልፅ ዕፅዋቶቻቸው ቅጠላቸው እስከ 15 ክንድ ይደርሳል፡፡ መዓዛቸው ልብን ይመስጣል፡፡ ፍሬአቸው ከጣዕሙ የተነሣ ሁሌም ከአፍ አልጠፋም ብሎ ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ልዩ ምድራዊ ገጽታ ተሰጥቷት የተፈጠረችውን ቦታ እንዲኖርባት የተፈቀደለት ሰው ብቻ ነበር፡፡ እንዲኖርባትም ብቻ ሳይሆን እንዲጠብቃትም እንዲንከባከባትም rደራ የተባለው እርሱ ነው፡፡ የተበጀችውን ገነት ምኗን ያበጃታል? እንዲያው በሥራው ሁሉ ሲያሰለጥነው ነው እንጂ፡፡ ለጊዜው ያችን ከምድር ሁሉ የሚመስላት የሌለ ገነት የተባለችውን ቦታ እንዲጠብቃት ነበር ትዕዛዝ የተላለፈለት ገነት ሦስት ዓይነት ትርጉም አላት፡፡
1ኛ ሕይወተ አዳም፡- የመጀመሪያው የገነት ትርጉም ህይወተ አዳም ነው፡፡ ገነት በአማሩና በተዋቡ እፅዋት የተሞላች ጣፋጭ መዓዛ ፣ ፍሬ የማይታጣባት ቦታ ነበረች ህይወተ አዳምም ስትሰራ ልምላሜ ነፍስ ፤ መዓዛ መንፈስ ቅዱስ ፍሬ ክብር የተሞላች እንደነበረች ያሳያል፡፡ ሰይጣን እስኪያጠወልጋት ድረስ የአዳም ህይወት ልምላሜ ይታይባት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ገነትን ጠብቃት ሲለው ህይወትህን ጠብቃት ሲለው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አዋቂ ነውና በህይወቱ ላይ ስልጣን የተሰጠውም ፍጡር ነበር፡፡ መጠበቅም ብቻ ሳይሆን መንከባከብም ለእርሱ የተሰጠ ሓላፊነት ነበር፡፡ ዐቂበ ህግ (የታዘዘውን ህግ መጠበቅ) የህይወቱ መጠበቂያ መንገድ ሲሆን ለእግዚአብሔር የሚያደርገው አገልግሎት ደግሞ ገነት ለተባለች ህይወቱም መንከባከቢያ መንገድ ነው፡፡
በስተምስራቅ በኩል የተተከለች ምስራቃዊት ቦታ በመሆኗ ደግሞ ሌላው አስደናቂ ምስጢር ነው፡፡ ምስራቅ የብርሃን መውጫ ነው፡፡ ከምስራቅ የወጣው ብርሃን ለአራቱ መዓዘናት ሁሉ ይበቃል፡፡ ሰውም ከርሱ በሚወጣው ጥበብ ዓለምን ለውጦ የሚኖር ልዩ ፍጡር መሆኑን ያመለክታል፡፡
ወንድሜ ሆይ ገነትህን እንዴት እየጠበካት ነው አሁንም ከነሙሉ ክብሯ ነው ያለችው፤ እርግጠኛ ነህ ዛሬም እንደጥንቱ ሁሉ ለማየት ደስ የሚያሰኘውን ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ በአንተ ገነት ውስጥ ማግኘት ይቻላል፤ እውነት እልሃለው ያንተን ገነት ለመጎብኘትና ከገነትህም ፍሬ ለመብላ ገነትህን የፈጠረ ጌታ ወደ አንተ እንደሚመጣ ታላቁ መጽሐፍ ይናገራል፡፡
‹‹ወልድ አሁየ ወረደ ውዕቱ ገነቱ ወይብላዕ እምፍሬ አቅማሂሁ›› ወደ ገነት ገባ መልካሙንም ፍፌ ይበላ ዘንድ መኃ 4፡16 መልካም ፍሬ ለማስገኘት ምን ያህል ትተጋለህ፤ አንተ ወዳለህበት ገነት ሲመሽ የህይወትህ መዝጊያ ሰርክ ላይ ድምፁን እያሰማ ፈጣሪህ መምጣቱን እንዳትዘነጋ፡፡ ለነገሩማኮ! ያንተገነት መስሎ የተሰራ ሁሉ የተሟላለት ቦታ ማግኘት አይቻልም፡፡ አንተኮ የታዘዝከው እንድትጠብቅና እንድትንከባከብ እንጅ ምንም እንድትጨምር አይደለም፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ገነትህን ሊያጠወልጉ የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም እግዚአብሔር ግን ያንተን ገነት እንዲሁ አልተዋትም፡፡ መልሰው ወደልምላሜዋና ወደቀድሞ ውበቷ ይመልሷት ዘንድ በውስጧ የሚመላለሱ አራት አፍላጋትን በነዚህ አፍላጋት ህይወት ሰጭነት ገነትህን በህይወት ማኖር ትችላለህ፡፡ አራቱ አፍላጋት የሚባሉት አራቱ ወንጌላውያን ናቸው፡፡ ያንተን ገነት ከልምላሜ አዕምሮ ወደፅጌ ትሩፋት ከፅጌ ቱርፋት ወደፍሬ ክብር እንዲያደርሱ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ በገነት ውስጥ በገነትህ ውስጥ እንዲፈሱ አድርጋቸው፡፡ በገነትህ ውስጥ የበቀለው እፀ ህይወትም የተሰጠህን ልጅነት ያመለክታል፡፡ ያንተ ገነት ማለት በነዚህ ሁሉ ስጦታዎች የተሞላች በመሆኗ የጠላት ዓይኖች በደጅ ስለሚያደቡባት ልትጠነቀቅላት ይገባል፡፡ በሀይማኖት ጠብቃት በጾም በጸሎት በስግደት ተንከባከባት፡፡ በገነትህ መካከል የፈጣሪው ድምፅ ሲሰማ የሚሸሸግ እርቃኑን የቆመ አዳም የተሸሸገባት እንዳትሆን ገነትህን ልትመለከታት ይገባሃል፡፡ ገነትህነን ጠብቃት ተንከባከት
፪ኛ የገነት ትርጉም ዓለመ ቅዱሳን ገነተ ፃድቃን ክርስቶስ ነው፡፡ ፃድቃን በዚች ምድር ሲሆኑ አረጋዊ መንፈሳዊ እንደተናገረው ክርስቶስን ዓለም አድርገው ይኖራሉ፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን የአረጋዊ መንፈሳዊ ወንድሙ ዮሐንስ በበርሃ የሚኖር ወንድሙ አረጋዊን ራስህን የምታስጠጋበት ጎጆ ልስራልህን፤ ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ ‹‹ የሁሉ ማረፊያ ጌታ ;; ለኔ ማረፊያነት አነሰኝን ብሎ ነበር የመለሰለት ስለዚህ ፃድቅ በአፀደ ስጋ በአፀደ ነፍስ ማረፊያ ገነታቸው ክርስቶስ ነው፡፡ ለዚህም ነው በመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ ፅድቁ ለተረጋገጠለት ለፈያታዊ ዘየማን ዛሬ በገነት ትኖራለህ ሉቃ 23፡43 የሚል መልስ የተሰጠው ጥበበኛ ሰው ሰለሞንም የክርስቶስን ወደዚህ ዓለም አመጣጥ ሲገልፅ ‹‹ ውዴ በገነቱ መንጋውን ያስማራ ዘንድ ወረደ መኃ 6፡2 በማለት የምፅዓቱን ዓላማ ይገልፃል፡፡ ከርሱ በቀር ምን መሰማሪያ አለን በራችን መሰማሪያ ገነታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ ጠብቅ ማለት እርሱ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህሪ አንድ ባህሪ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ብለህ እመን ማለት ነው፡፡
በገነት ውስጥ ያሉ አፍላጋት የአራቱ ወንጌላዊያን የምስጢር ምንጭ (መገኛ ክርስቶስ መሆኑን ሲያመለክት ዕፀ ህይወትም የህይወት መገኛ እርሱ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በዚህ ገነት ውስጥ መኖር ለሰው ህይወት ነው፡፡ ረሃብ የለም ውኃ ጥምም የለም ሀዘንና ስቃይም የለምና በዚህ ገነት ውስጥ ይኖር ዘንድ ለሁሉም ጥሪ ተላልፎአል፡፡
፫ኛ. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- በመጽሐፍት ሁሉ መልካም ስም እና ምሳሌ የተሰጠው ከቅዱሳን ሁሉ እንደመቤታችን ማንም የለም ከነዚህ ስሞቿ መካከል ገነት የሚለው አንዱ ነው፡፡ ከነብያት አንዱ የሆነው አባቷ ሰሎሞን በዘመን ሁሉ ተጠብቆ የሚኖር ንጽሕናዋን በገለፀበት አንቀፅ ነበር፡፡ “ገነት ዕፁት ወአዘቅት ኅትምት›› መኃ 4፡12 የታተመች የውሃ ምንጭ የተዘጋች ገነት የሚል ነው፡፡ ይህንን ይዘው ከዚያም በኋላ የተነሱ ሊቃውንት እነቅዱስ ያሬድ እነ ቅዱስ ኤፍሬም ገነት ይዕቲ ነቅዓ ገነት ዐዘቅተ ማየ ህይወት የህይወት ውኃ ምንጭ የገነት ፈሳሾች መገኛ ገነት ተፈስሂ ኦ ገነት ነባቢት ማኅደሩ ለክርስቶስ የክርስቶስ ማደርያው ነባቢት ገነት አንችነሽ ፡፡ እያሉ በየድርሳናቱ አወድሰዋታል፡፡
ገነትና እመቤታችን በሚከተሉት መንገዶች ይመሳሰላሉ፡፡
-
ገነት ምስራቃዊት ቦታ ነች እመቤታችንም በምስራቃዊ የሀገራችን ክፍል የተገኘች መሆኗን ያመለክታል፡፡ አንድም የፀሐየ ፅድቅ የኢየሱስ ክርስቶስ መገኛ ናትና ነው፡፡
-
በገነት ዕፀ ህይወት ይበቅልባታል፡ ከእመቤታችንም እፀ ህይወት ተብሎ የሚጠራ ስጋውና ደሙ የመገኘቱ ምሳሌ ነው፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹ ከእፀ-ህይወት እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም የክርስቶስ ስጋና ደሙ ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ የአማናዊት እፀ ህይወት መገኛ ድንግል አማናዊት ገነት
-
በገነት አራት አፍላጋት አሉ ብለን ነበር እነዚህ የአራቱ ንህናዎቿ ሰው የሚበድልባቸው አራት መንገዶች አሉ፡፡ ማየትና መስማት ማሽተትና መዳሰስ ናቸው ሰው በህይወት ዘመኑ በነዚህ አራት መንገዶች ሲበድል ይኖራል፡፡ እመቤታችን ግን በነዚህ ሁሉ አልበደለችውምና አራቱ የገነት አፍላጋት በእመቤታችን አራት ንፅህናዎች ይመሰላሉ ያልነው በዚህ ነው፡፡ ወንድሜ ሆይ የሚበላውን የሚጠጣውን ያስገኘችልን አማናዊት ገነት ድንግል ማርያም ናትና በርሷ ውስጥ ብትኖር ለህይወትህ መልካም ነውና ደግሜ እልሃለው ገነትን ጠብቃት፡፡