“መከራ ልትቀበሉ እንጂ በስሙ ልታምኑ ብቻ አልተጠራችሁም” (ፊል. ፩፥፳፱)

 

ዘመናችን መረጃ በፍጥነት የሚለዋወጥበት፣ ስላሙ ሲደፈርስ ደቂቃ የማይፈጅበት እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰዎች ሞትን ለመሸሽ የማያደርጉት ጥረት የለም፡፡ ኃያላን ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ የኤሌክትሪክ አጥር፣ የድኅንነት ካሜራ እያዘጋጁ ወንጀልንና ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ መንገዳቸው ሥጋዊ ፍላጎትን የተከተለ በመሆኑ መፍትሔ ማሰገኘት አልቻለም፡፡ ችግሩ የሚፈታው ሁልጊዜ ችግርን ወደ ሌላ በመጠቆም አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

ምዕራባውያን የአዳጊ ሀገሮችን ቅርስና መዋዕለ ንዋይ እየዘረፉ ወደ ሀገራቸው ሲወሰዱ ኖረዋል፡፡ አሁን ደግሞ እነሱው ባሳዩዋቸው መንገድ ሌሎች ሀብታሞች የሰበሰቡትን እንዳይበሉት እያደረጉዋቸው ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ከምኑም የሌሉበት ክርስቲያኖች ለአደጋ እየተጋለጡ፣ የሚደርስላቸው አጥተው እግዚአብሔርን እየተማጠኑ ነው፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆኑን የሶሪያ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የተሸፈነው ሁሉ የእልክ መወጫና የጦር መለማመጃ የሚያደርገው ክርስቲያኖችን ነው፡፡ መስቀል የጨበጡ ካህናትን ገድሎ የሚገኝ ደስታ፣ ምእመናንን የሚያረጋጋና ለሀገር ሰላም የሚጸልይን ጳጳስ አስሮ የሚገኝ ሰላም እንዴት ያለ ሰላም ሊሆን እንደሚችል መገመት ያዳግታል፡፡

በመካከላችን የተፈጠረውን ልዩነት ተወያይተን እንፍታው፣ ከጦርነት ጥፋት እንጂ ልማት አናገኝም የሚሉት ወገኖች እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ ሀገር በወንበዴዎች ጠፍታ እንደምታድር በሰላማውያን ደግሞ ተሠርታ ታድራለች፡፡ ሰላማውያን ከሆንን ለእኛ የሚያስፈልገን ለሌሎችም እንደሚያስፈልጋቸው ስለምናምን ያለውን ተካፍለን እንጠቀማለን፣ ከሌለ ደግሞ በጋራ ሠርተን የምናገኝበትን ዘዴ እንቀይሳለን፡፡ በዓለማችን እየተሠራ ያለው ግን የሌላውን ነጥቆ የራስ ማድረግ ነው፡፡ የድሀ ሀገሮችን ቅርስ፣ ንዋያተ ቅድሳት እየዘረፉ ወስደው የራሳቸው የሚመስልበትን ሕግ አውጥተው ይኖራሉ፡፡ የታሪኩ ባለቤቶች የራሳቸውን ንዋያተ ቅድሳት ከፍለው ይመለከታሉ፡፡ ይህም የዓለም ሕግጋት የተንሸዋረረና ላለው የሚያደላ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ትክክለኛ መፍትሔ ለማምጣት ከተፈለገ ፍትሕ ያለ አድሎ ለሁሉም መስጠትና በኢኮኖሚ የዳበሩት ሀገሮች ድሆችን እናውቅላችኋለን፣ እኛ ያልናችሁን ብቻ ፈጽሙ የሚለው አሠራር መታረም አለበት፡፡

እምነት ያላቸው ሰዎች ግን እንኳን የሌላውን ሊነጥቁ የራሳቸውንም አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ መመሪያቸውም “እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት፡፡ በዚህም ለሸማግሌዎች ተመሰከረላቸው፡፡ ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፣ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደሆነ በእምነት እናውቃለን” (ዕብ. ፲፩፥፲፫) የሚለው ቃል ነው፡፡ ተስፋቸው ለዘለዓለማዊው ዓለም በመሆኑም በምድር ሰላማውያን ሆነው ይኖራሉ፡፡ የማይታየውን ተስፋ ስለሚያደርጉም እንደሚታረድ በግ እየተጎተቱ ወደ ሞት ሲወሰዱ በደስታ ይቀበሉታል፡፡ ሞትንም የሚንቁት ከመከራ፣ ከውጣውረድ፣ ከስቃይ የሚያርፉበትና ዳግም ሞት ወደሌለበት የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ነው፡፡

ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ሲኖሩ ደስታና ኀዘን፣ ማግኘትና ማጣት ቢፈራረቅባቸውም ታግለው ለማሸነፍ፣ እግዚአብሔርን ጠይቀውም መፍትሔ ለማምጣ ይሞክራሉ፡፡ የሚደርስባቸውን ፈተና በጸጋ የሚቀበሉትም በተስፋ ኗሪዎች ሀገራቸው በሰማይ መሆኑን በደንብ የተረዱ በመሆናቸው ነው፡፡ ኃይል እያላቸው የሚሸሹት፣ ማድረግ እየቻሉ አቅም የሌላቸው የሚመስሉት ዘለዓለማዊው ድኅነት በመሞት እንጂ በመግደል የሚገኝ ባለመሆኑ በመስጠት እንጂ በመቀማት ባለመገኘቱ ነው፡፡ የነገሥታት ወገኖች የነበሩት ሰማዕቱ ቅዱስ አቦሊ፣ አባቱ ዮስጦስና እናቱ ታውክልያ ዙፋኑ ለእነሱ እንደሚገባ እያወቁ ስለዘለዓለማዊው ጊዜያውን ናቁት፡፡ የሮማ ሕዝብ ከዲዮቅልጥያኖስ እነሱ እንደሚሻሉት፣ በጉልበት ሳይሆን በእምነት እንደሚመሩት እነሱም፣ ዲዮቅልጥያስም፣ ሕዝቡም ያውቃሉ፡፡ ያደረጉት ግን ለክርስትና ፍቅር ብለው ሥልጣናቸውን መተውና ሰማዕትነትን መቀበል ነው፡፡ አቅም የላቸውም እንዳይባሉ ብቻቸውን ተዋግተው የጠላት ሠራዊት መመለስ እንደሚችሉ አሳይተዋል፡፡ ክርስትናቸው ግን ከዚያ እንዲያልፉ አላደረጋቸውም፡፡ በዚህም ገዳያቸው ዲዮቅልጥያኖስ በክፉ እነሱ ግን በመልካም ሲታወሱ እንዲኖሩ የሚያደርጋቸውን ሥራ ሠርተው ዐልፈዋል፡፡ ሁልጊዜ አስቡን፣ ከአምላካችሁ አስታርቁን እየተባሉ ይለመናሉ፡፡

ክርስቲያኖች እምነት እንጂ ፍርሃት መገለጫቸው አይደለም፡፡ ጦር መሣሪያ የታጠቁት ባዶዋቸውን የቆሙትን ክርስቲያኖች የሚፈሯቸው እምነት ያላቸው ሰዎች እግዚአብሔር አብሯቸው ስለአለ ምን ያህል እንደሚያስፈሩ ማሳያ ነው፡፡ መፍራት የነበረበት ባዶ እጁን ያለና ሞት የተፈረደበት እንጂ ንጹሐንን ወደ ሞት በመውሰድ የሚገድል አይደለም፡፡ በክርስቲያኖች የሚፈጸመው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ንጉሡ እለእስክንድሮስ በፍርሃት እንዲርድ ያደረገው የሦስት ዓመቱ ሰማዕቱ ቂርቆስ ነው፡፡ የእምነት ሰዎችን አላውያን ነገሥታት ብቻ ሳይሆኑ አጋንንትም ይፈሯቸዋል፡፡

እምነታቸውን ጋሻ በማድረጋቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በአጸደ ሥጋ ለምንኖር ሁሉ ኃይላችን፣ ብርታታችን፣ ትውክልታችን፣ ጋሻ መከታችን መሆናቸውን ሐዋርያው “እነሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፣ ተስፋቸውን አገኙ፣ የአናብስትን አፍ ዘጉ፡፡ የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ከሰይፉ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፣ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ፡፡ ሴቶችም እንደ ትንሣኤ ቀን፣ ተነሥተውላቸው ሙታኖቻቸውን ተቀበሉ፤ ተፈርዶባቸው የሞቱም አሉ፤… የገረፉዋቸው፣ የዘበቱባቸውና ያሰሩዋቸው ወደ ወኅኒ ያስገቧቸው አሉ፡፡ በመጋዝ የሰነጠቋቸው፣ በድንጋይ የወገሯቸው፣ በሰይፍም ስለት የገደሏቸው አሉ፤ ማቅ፣ ምንጣና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፣ ተቸገሩ፣ መከራ ተቀበሉ፣ ተራቡ፣ ተጠሙም፡፡ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፣ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ (ዕብ. ፲፩፥፴፫-፴፰) በማለት ገለጠው፡፡ የእስራኤል ኃያላን የሃይማኖት ሰዎች ሕዝበ እግዚአብሔርን ለመጠበቅ ያደረጉትን ተጋድሎ በመዘርዘር ወደ ሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት የሚሸጋገረው የሐዋርያው ትምህርት ለደከሙት ብርታት የሚሆን ነው፡፡

ሐዋርያው አስቀድሞ እምነታቸውን ነገረን፡፡ በመቀጠልም እምነታቸውን ለመጠበቅ የፈጸሙትን ተጋድሎ አስረዳን፡፡ አስከትሎም በዚህ ዓለም በፈጸሙት ተጋድሎ በእምነት እንደተመሰከረላቸው፣ የተስፋ ቃል እንደተገባላቸው አበሰረን፡፡ ሐዋርያው የእነዚህን አበው ተጋድሎ የተረከልን በእምነት እንድንጸና፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ፈተና ዛሬ አለመጀመሩን ተገንዝበን እንድንረዳው ነው፡፡ ወታደር ጀብድ የፈጸሙ ጀግኖችን ተጋድሎ እየተረከ የወታደሮችን ስሜት እንደሚቀሰቅስና ፍርሃታቸውን እንደሚያርቅላቸው ሁሉ ክርስቲያኖችም በእምነት የጸኑትን፣ ይህን ዓለም ታግለው ያሸንፉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ በመተረክ አርአያ እንድናደርጋቸው እናንተን ያጸና እኛንም ያጽናን እንድንላቸው ነው፡፡ በሃይማኖት ጽኑ፣ የሚያልፈውን በማያልፈው ለመተካት የሚደርስባችሁን ታገሱ፣ በእምነት ጽኑ፣ ጎልምሱም የሚለው ትምህርት ለክርስቲያኖች ስንቅ ነው፡፡ ፍርሃትን አርቆ በእምነት ለመጽናት የሚያበቃ ነው፡፡

በተስፋ የሚጠብቁት ስለበለጠባቸው በዚህ ዓለም የሚደርስባቸውን መከራ መታገሥ እንዳለባቸው ሐዋርያው “እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ በክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፡፡ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛልና፤ ይበልጥብኛል፡፡ ደግሞም ስለ እናንተ በሕይወተ ሥጋ ብኖር ይሻላል፡፡ ይህንም ዐውቄ ለማደጋችሁና ለሃይማኖትም ለምታገኙት ደስታ እንደምኖር አምናለሁ” (ፊል. ፩፥፳፫-፳፭) በማለት ገልጦታል፡፡ በዚህ ቃል ሐዋርያው የራሱን ፍላጎት ገለጠ፡፡ ለምእመናንና ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውንም አሳወቀ፡፡ የሃይማኖት ሰዎች እንደነሱ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር እንደሚገባ አስገነዘበ፡፡ ይህም ክርስቲያኖች ሌላውን ለመጥቀም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ቢናፍቁ እንኳ ሊያዘገዩት እንደሚችሉ ያስረዳል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ትገፋለች፡፡ ወድቃ ግን አታውቅም፡፡ የሚገርመው አላውያን ቤተ ክርስቲያንን ለመግፋት የዘረጉት እጃቸው እምነትን ገንዘብ አድርጎ መመለሱን እያየን መሆኑ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ እንዲህ ነው፡፡ አንዱ ሲቆረጥ ከሥሩ በሺሕ የሚቆጠሩ እያበቀለ ክርስትና እንድታብብ አድርጓል፡፡ የሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ በሀገራችንም ሰማዕትነት አያምልጥህ እያሉ በአንድ ቀን ስምንት ሺሕ ገበሬ ምእመናን ሰማዕታትን ተቀብለዋል፡፡ ይህም በታሪክ እንዲዘከሩ፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲታሰቡ አድርጓቸው ይኖራል፡፡

በየዘመኑ ዲያብሎስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና ያስነሣል፡፡ አይታለፍም የተባለው ታልፎ፣ አይሆንም የተባለው ተፈጽሞ እየታየ ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ፤ ቀስቱን ጨረሰ፤ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ትዋጋለች፤ ተሸንፋ ግን አታውቅም” በማለት መናገሩ ምስክር ነው፡፡ ዲያብሎስ እንደማያሸንፉት እያወቀ፣ ክርስቲያኖችም በጸሎት ኃይል እንደሚያደክሙ እየተረዳ ቤተ ክርስቲያንን ይዋጋል፡፡ ዲያብሎስ የሚያተርፈው ቢኖር ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ያሰለፋቸው ጀሌዎቹ በክፋታቸው ከጸኑለት አብረውት ገሃነመ እሳት እንዲወርዱ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ የአባቶቻችንና እናቶቻችን ቅድስና እንዲገለጥ ያደርጋል እንጂ ያሰበው ተሳክቶለት፣ ምኞቱ ሞልቶለት አያውቅም፡፡

ክርስቲያኖች ክርስትናን የተቀበሉት፣ የሥላሴ ልጅነትን ያገኙት ለማመን ብቻ ሳይሆን መከራም ለመቀበል መሆኑን ሐዋርያው “የእነሱ ጥፋት የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙትን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ፡፡ ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቷችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም፡፡ እንዲሁም እኔን እንዳያችሁኝ የእኔንም ነገር እንደሰማችሁ ምን ጊዜም ተጋደሉ” (ፊል. ፩፥፳፰-፴) በማለት ገልጦልናል፡፡ ይህን የምንለው ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ሲኖር መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ምንም አያስፈልጋቸውም ለማለት አይደለም፡፡ ከሁሉ የሚቀድመው በእምነት ጸንቶ፣ ነቅቶና ተዘጋጅቶ መኖር እንደሚያስፈልግ ለመግለጥ እንጂ፡፡ እምነት ያላቸውና ትውክልታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ ደግሞ በዚህ ዓለም እንዴት እንደሚኖሩ ያውቁነታል፡፡ ራሳቸው ዘመኑን ዋጅተው ነው እኛንም ዘመኑን ዋጁ የሚሉን፡፡

የክርስትና ማእበል በሆነችው ኢትዮጵያ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል ልዩነት ሳይገድበን ተንቀሳቅሰን ይመቸናል በምንለው አካባቢ ወልደን፣ ከብደን፣ ወጥተን፣ ወርደን፣ ነግደን አትርፈን እንኖራለን፡፡ ማን ነህ፣ ከየት መጣህ፣ ሃይማኖትህ ምንድን ነው የሚል ወገን በሀገራችን አይታሰብም ነበር፡፡ ዓለምን ከምናስደንቅበት ነገር አንዱ በሌሎች ዓለማት በበጎ የማይታዩት ክርስትናና እስልምና በኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነው መኖራቸው ነው፡፡ በብዙዎች አካባቢዎች ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ሲያጡ ከመሬታቸው ቆርሰው፣ ከኪሳቸው ገንዘብ አውጥተው፣ የሰበካ ጉባኤ አባል ሆነው አብያተ ክርስቲያናትን ያሠሩ ብዙ ሙስሊም ወገኖቻችን ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት ጠባቂ የሆኑና ቤተ ክርስቲያንን በጥበቃነት የሚያገለግሉ ሙስሊም ወገኖቻችን መኖራቸው የሚገልጠው በሃይማኖት ልዩ ብንሆን በማኅበራዊ ሕይወት፣ በባህል ለምን እንለያለን ብለው ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ታሪኮችን በሐመር መጽሔት፣ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ስርጭት ስናስተላልፍ መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ይህንን የምንገልጠው ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በትክክል የተፈጸመ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ የገረመንም እንዲህ በሚደረግባት ሀገር ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች የጥፋት ዓላማ እየሆኑ በመምጣቸው ነው፡፡

ሰሞኑን በሶማሌ ክልል ክርስቲያኖችን ብቻና ቤተ ክርስቲያንን መርጠው ጥፋት ሲታወጅባቸው የእስልምና ጉዳዮችም፣ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ድርጊቱን እንደሚያወግዙት የገለጡት የአንዱ በሰላም ማደር ለራስ ሰላምም ስለሚጠቅም ነው፡፡ በሌላ በኩልም እንዲህ ያለ ጥፋት በሀገራችን ያልተለመደ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ወገኖች የሰጡት መግለጫ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያኗ ከሰጠችው የጠነከረ ነው፡፡ አሜሪካና ኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ አባቶች ይቅር ተባብለው ዕርቁንም በሚሊኒየም አዳራሽ ባበሠሩበት ወቅት የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የወንጌላውያን ኅብረትና የቃለ ሕይወት ተወካዮች ያደረጉት ንግግር ይህ ድምፅ ከቤተ ክርስቲያን ነው ከሌላ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ይህ ደስታ ሳይፈጸም በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጭፍጨፋና ቃጠሎ ተተካ፡፡ ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር እንዲህ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን የምንገልጠው ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ በተሳለ ሰይፍ ላይ ለቆሙት በማዘን ነው፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ቤተ ክርስቲያንን ብዙዎች ለመግፋት ሞክረው ነበር አልቻሉም እንጂ፡፡ ዐርፍተ ዘመን ገትቷቸው፣ ተአምር ተደርጎ ተመልሰው አምላኬ ሆይ ሳላውቅ ባጠፋሁት አትቅሰፈኝ ሲሉ ኖረዋል፡፡ አንመለስም ያሉትም አሟሟታቸው ምን ይመስል እንደነበር የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማንበብ በዲዮቅልጥያኖስ፣ የዮልዮስቂሳርና በሌሎችም የደረሰውን ማሰብ ይገባል፡፡

የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ ሞክሮ የነበረው ዲዮቅልጥዮስ የደረሰበትን መከራ ገድሉንና ስንክሳር መጽሐፉን ማንበብ ይገባል፡፡ በቅድስት አርሴማና በተከታዮቿ ላይ በቃላት ተነግሮ የማያልቅ መከራ አድርሶ የነበረው የአርማንያው ንጉሥ ድርጣድስ አእምሮው ተነሥቶት ለሰባት ዓመታት እንደ በራሃ እሪያ ሣር ሲበላ ኖሮ በገባሬ ተአምራት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ ጸሎት እንደዳነ፣ ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳርያንና ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን ከዋሉበት አላሳድር፣ ካደሩበት አላውል ብሎ የነበረው በአቴንስ የፍልስፍና ትምህርት ቤት የትምህርት ቤት ጓደኛቸው የነበረው ዩልዮስቄሳር መጨረሻቸው አላማረም፡፡ እነሱ ስለ ጓደኝነት፣ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ጭምር ብለው ቢታገሱት አልሰማም በማለቱና ከጦርነት ሲመለስ እነሱንም ለመግደል ቤተ ክርስቲያናቸውንም ለማቃጠል ዝቶ ጠላቶቹን ለመውጋት ሲሔድ ቅዱስ ባስልዮስ ክርስቲያኖችን ካሳደደ ከሔደበት በሰላም እንደማይመለስ ነገረው፡፡ ንጉሡ ድንኳን ውስጥ በተኛበት የቅዱስ መርቆርዮስ ሥዕል በጦር ወጋው፡፡ ከአልጋው ሳይነሣ ቀረ፡፡ አጃቢዎቹ ወዳለበት ቢገቡ በደም ተንክሮ ስላገኙት ደንግጠው ተበተኑ፡፡

በክርስቲያኖች ደም እጃቸውን የታጠቡ ወገኖች የደረሰባቸውን ለማወቅ መጻሕፍትን ማንበብ ሊቃውንትን መጠየቅ ይገባል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግፈኞች “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ. ፭፥፲፮) ለተባለላቸው ከስቃይ ወደ ረፍት መሸጋገሪያ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእነሱን ደካማ ጎን የክርስቲያኖችን ጥብዓት የሚገልጥ ነው፡፡ ክርስቲያኖች “ክርስትና ሊኖሩት እንጂ ሊያወሩት ብቻ እንደማይገባ፣ ወንጌል በተግባር ሲገለጥ እንጂ እንደ ርዕዮተ ዓለም በቃላት ብቻ በንግግር ማሳመር እንደማይሰበክ ሕያው ምስክር ናቸው፡፡ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ከመንጸፈዳይን ለማውጣት መከራ ተቀብሏል፤ ሞትንም ድል አድርጎ ተነሥቷል፡፡ ትንሣኤውን በሚመስል ተንሣኤ ተነሥተን ከክርስቶስ ጋር እንኖር ዘንድ ሞቱን በሚመስል ሞት መተባበር እንዳለብን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናል፡፡ የኑሮዋቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው የተባልናቸው ዋኖቻችን ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሁሉ መስለውታል፡፡ እኛም እነሱን እንድንከተልና እንድመስላቸው አርአያነታቸውን መከተል ይገባናል፡፡”

ለእግዚአብሔር ሕዝብ ብሎ መከራ የመቀበልን አርአያነት ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እንድንማር ሐዋርያው “ሙሴ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና፡፡… የማይታየውን እንደሚታየው አድርጎ ጸንቶአልና” (ዕብ. ፲፩፥፳፭-፳፯) በማለት አስተምሮናል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያስገነዝበው የክርቲያኖች በመከራ የማይገበሩ መሆን ነው፡፡

እንደ ሀገር የምንበለጽገውና ሰላማችን እውን የሚሆነው በሰላም ተከባብረን ስንኖር ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ያለንን መጠቀም፣ የጎረስነውን መዋጥ አንችልም፡፡ ሌት ዕንቅልፍ ቀን ረፍት አናገኝም፡፡ ዛሬ በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጀመረው ጥፋት መልኩን ለውጦ ብዙዎችን እንዳይበላና መጨረሻችንን ዳር ቆመው አይተው መሬታችንን ለመውረር ለሚጎመጁት ጠላቶቻችን መንገድ ጠራጊ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ጥፋት ቢከሠት እንኳ ጥፋትን በጥፋት መመለስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም፡፡ የተጠቃሉት አብያተ ክርስቲያናትና የሞቱና የተሰደዱ ክርስቲያኖች እስከ አሁን በክልሉ መንግሥት መልካም ፈቃድና በሕዝቡ አብሮ የመኖር ባህል በቦታው  ብዙ ዓመታት ኖረዋል፡፡ መቀጠል የሚኖርበት እንደ እስከአሁኑ በፍቅር መኖር ነው፡፡ የሚስተካከል ካለ ማስተካከል፣ ጎደሎ ካለ መሙላት፣ የሚያስቸግር ካለ ማስተካከል እንጂ ሰላማውያንን ማወክ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን አእምሮ ያለው ሕፃናትም ያውቁታል፡፡ መንግሥት አልባ ለመሆን ካልፈለግንና ሀገራችን ውስጥ ቀምቶ የሚበላ እንዲኖር ካልፈለግን በቀር፡፡ ወደፊት አብረን እንድንኖር የሚያደርጉንን እየተመካከርን መሥራት፣ የሚያስቸግሩ ካሉ ማስተካከል ይገባል፡፡ እምነትን ሽፋን አድርጎ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያይ ካለ ቢቻል መክሮ ማስተካከል አልመለስም ካለ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እያሳወቅን ሰላማችንን ጠብቀን መኖር ይጠበቅብናል፡፡

የተሰደዱት እንዲመለሱ፣ የተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሠሩ፣ የሟች ወገኖች እንዲደገፉ ማድረግ ይገባል፡፡ ችግሩን ወደ ሌላ መጠቆም አይጠቅምም፡፡ የሚጠቅመው መፍትሔ ማበጀትና ፍቅርንና አብሮ መኖርን የሚያጸና ተግባር መፈጸም ነው፡፡ ዐይን ስለ ዐይን የሚለው ሕግ ቀኝህን በመታህ ግራውን አዙርለት በሚለው ቢተካም ለሀገር ደኅንነት ሲባል ጥፋተኞች የሚታረሙበትን፣ ዳግም ለጥፋት እንዳይሰለፉ የሚሆኑበትን ሥራ መሥራት ከመንግሥት፣ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከፍትሕ አካላትና ከሚመለከታቸው ሁሉ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው “መከራ ልትቀበሉ እንጂ በስሙ ልታምኑ ብቻ አልተጠራችሁም” በማለት ሐዋርያው የተናገረውን እንዳንረሳው ለማድረግ እንደሆነስ ማን ያውቃል፡፡ ማን ያውቃል ነገ ከነገወዲያ ከተቃጠሉት ዐሥር አብያተ ክርስቲያናት ሁለትና ሦስት ዕጥፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያንፁ ክርስቲያኖችን እግዚአብሔር ሊያሥነሣም እንደሚችል ማመን ያስፈልጋል፡፡

  ምንጭ  ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከነሐሴ16-ጳጉሜ5ቀን 2010ዓ.ም

“ከእንግዲህ በኋላ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠልና ክርስቲያኖችን በጭካኔ መግደል በዝምታ አይታይም” ብፁዕ ሥራ አስኪያጅ

 

                                                       ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን

በካሣሁን ለምለሙ

በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች በተለየ መልኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያነጣጠረ ቃጠሎ፣ ዝርፊያ፣ እንዲሁም በክርስቲያኖች ላይ የሚካሔደው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ከእንግዲህ በኋላ በዝምታ ሊታይ እንደማይገባ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ገለጡ፡፡
ለሀገር ብዙ ዋጋ በከፈለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በአማኞቿ ላይ ለበርካታ ዓመታት አረመናዊ ድርጊት በተደጋጋሚ ሲፈጸም ቆይቷል፡፡ እምነትን ትኵረት በማድረግ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከፍተኛ በደል መፈጸሙን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው በተለይም በጅማ፣ በጅግጅጋ፣ በኢሊባቡር እንዲሁም በባሌ ጎባ ችግሩ እጅግ በጣም የከፋ ከመሆኑ የተነሣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ምእመናን በጭካኔ በስለት ታርደዋል ካህናትም ተገድለዋል ብለዋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ዘግናኝ በደሎች ለወደፊቱ የሚፈጸሙ ከሆነ ወደ ፈጣሪ መጮኽ እንደተጠበቀ ሆኖ ከእንግዲህ በኋላ ግን በቤተ ክርስቲያኗም ሆነ በአማኞቿ ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ለመመከት የምንገደድ ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲኗም የሚሰማት ካገኘች መጮኽ እስካለባት አካል ድረስ ጩኾቷን ታሰማለች፡፡ ቤተ ክርስቲያናቸው እየተቃጠለ፤ እምነታቸው እየጠፋ መሆኑን ምእመናን በመገንዘብ ከእንግዲህ በኋላ የተከፈለው ሁሉ መሥዋዕት ተከፍሎ እራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ብፁዕነታቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ሥጋ ወደሙ የሚፈተትባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል፤ ካህናትና ምእመናን እንደ ከብት ሲታረዱ ከእንግዲህ በኋላ ዝም ብሎ የሚያይ ምእመን ሊኖር እንደማይገባ ሥራ አስኪያጁ ገልጠው የእስከ አሁኑ ትዕግሥትና ዝምታ ቤተ ክርስቲያንን፣ ምእመናንንና ሃይማኖታችንን በእጅጉ እየጎዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለሀገርና ለወገን ባለውለታ የሆነች ቅድስትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ በዐደባባይ ክብሯ ዝቅ ብሎ የጥፋት ዱላ ሲያርፋባት በጣም ልብ ይነካል፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ ለሀገር ምሶሶ መሆኗ ለመንግሥት ያልተሰወረ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያኗና በአማኞቿ ላይ የተቃጣውን እኵይና አርመኔዊ ተግባር በአፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበው፤ ካልሆነ ግን እየታረደና እየተቃጠለ ዝም የሚል ስለማይኖር የከፋ እልቂት እንዳይከተል ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት፣ ሕዝብና ሕግ ባለበት ሀገር ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖችና ካህናት እንደ አውሬ ታድነው በጭካኔ መታረድ የለባቸውም፤ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁ መቃጠል የለባቸውም፤ ምእመናንም ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል የለባቸውም በማለት ብፁዕነታቸው አሳስበዋል፡፡
ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተፈጸመው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት አሥር አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው፣ ካህናትና ምእመናን መታረዳቸው እንዲሁም ሀብት ንብረታቸው መውደሙና መዘረፉ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ ለመገንባትና ሀብት ንብረታቸው የተዘረፈባቸውን ምእመናን እንደ ገና ለማቋቋም የተቋቋመ ኮሚቴ እንዳለ የገለጡት ብፁዕነታቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ምእመናን እጃቸውን በመዘርጋት የበረከቱ ተካፋይና የቤተ ክርስቲያኗ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በውጭ ሀገር የሚገኙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያንና በአማኞቿ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ ድርጊት እግዚአብሔር እንዲያርቀው በጸሎት ከማሳሰብ በተጨማሪ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


ምንጭ  ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከነሐሴ16-ጳጉሜ5ቀን 2010ዓ.ም