የጌታችን ልደት እና የመላእክት አገልግሎት

በዲያቆን አለልኝ ጥሩዬ

ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በዓለም ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ጨለማ ያስወግድ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ሰው ኾነ፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው አማናዊው ብርሃን ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ‹‹ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኵሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም፤ በጨለማ ውስጥ ለሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው (ኢሳ. ፱፥፪)፡፡ ቀዳሚ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው በኾነ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት በቤተ ልሔም ተገኝተዋል፡፡ ይህንም ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ወግብተ መጽኡ ብዙኃን ሐራ ሰማይ፤ የሰማይ መላእክት በድንገት መጡ›› በማለት ገልጾታል (ሉቃ. ፪፥፲፫)፡፡ በድንገት መባሉም አመጣጣቸው ግሩም በመኾኑ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት ቀድሞ አመጣጣቸው ጻድቃንን ለመርዳት፣ ሰማዕታትን ከስለት ለመታደግ፣ የተቸገረውን ለማጽናት ነበር፡፡

ዛሬ ግን ስለ ሰው ፍቅር ከሰማይ የወረደውን፣ በጎል (በበረት) የተጣለውን፣ በጨርቅ የተጠቀለለውን አምላክ ከሰው ልጅ ጋር በአንድነት ለማመስገን መጡ፡፡ ‹‹ዮም አሐደ መርዔተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ ንጉሥ፤ ሰውና መላእክት፣ ንጉሥ ክርስቶስን ያመሰግኑ ዘንድ ተባበሩ›› እንዲል፡፡ መላእክት በተፈጥሯቸው የማይሞቱ (ሕያዋን) ሲኾኑ ሰው ደግሞ ሟች ነው፤ ሞት ይስማማዋል፡፡ በጌታችን ልደት ግን መላእክትና የሰው ልጆች በአንድ ማኅበር፣ በአንድ ቃል ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር›› እያሉ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ በአዳም ኀጢአት ምክንያት ፈርሶ የነበረው የመላእክትና የሰው ልጆች ማኅበር ከተቋረጠ ከብዙ ዘመን በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንደ ገና ተጀመረ፡፡ ይህ የምስጋና ኅብረትም ምድር እንደ ልብስ ተጠቅልላ ስታልፍ ወደ ፊት በምትመጣዋ በአዲሲቷ ዓለም፣ በአዲሱ ሰማይ፣ በአዲሱ ቤተ መቅደስ ይቀጥላል (ራእ. ፳፩፥፩-፬)፡፡

አንድነታችን እንደማያቋርጥና በሰማይም እንደሚቀጥል አረጋዊ መንፈሳዊ ሲገልጥም ‹‹እሉሂ ወእልክቱሂ በአሐዱ ኁባሬ አልቦ ማዕከሌነ ወማዕከሌሆሙ፤ በእኛ በደቂቀ አዳም እና በቅዱሳን መላእክት መካከል ልዩነት የለም›› ይላል፡፡ ይህም የኾነው በጌታችን መወለድ ምክንያት ነው፡፡ በጌታችን ልደት ምክንያት እኛም ዳግመኛ ተወለድን፡፡ የጌታችን ልደት የእኛም የክርስቲያኖች ዅሉ ልደት ነው፡፡ ከሦስቱ የቀጰዶቅያ አባቶች (The three Cappadocian Fathers) አንዱ፣ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ሊቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ይህን ምሥጢር ሲገልጥ ‹‹The nativity of Christ is the birthday of the whole human race – የክርስቶስ ልደት የመላው ሰው የልደት ቀን ነው›› ሲል መስክሯል (Hyman of praise to the mother of God)፡፡

ሊቃውንት እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እና ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ከምሥጢራት ዅሉ በላይ ነው፡፡ ይህን ምሥጢር ከማድነቅ ሌላ ሊናገሩት አይቻልም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በመገረም ይህን ጥበብ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረው እርሱ ሕፃን ኾኗልና፡፡ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ፡፡ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚኾን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፡፡ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ፡፡ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት፡፡ ይህን ወዷልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ፷፮፥፲፯)፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በቅዳሴው የእግዚአብሔርን ሰው የመኾን ምሥጢር እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ ‹‹በጐለ እንስሳ ተወድየ አሞኀ ንግሡ ተወፈየ ወከመ ሕፃናት በከየ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ፤ በእንስሳት በረት ተጨመረ፡፡ የንጉሡንም እጅ መንሻ ተቀበለ፡፡ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ፤›› (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ቍ. ፲፯)፡፡

በዚህ ታላቅ በዓላችን የምናደንቀው ሌላው ምሥጢር እግዚአብሔር ወልድ በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን፣ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የመወለዱ ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን ድንቅ የሥጋዌ ምሥጢር ግሩም፣ ዕፁብ እያሉ ያደንቁታል፡፡ ሐዋርያውያን አበውን ተከትለው ከተነሡ የቤተ ክርስቲያን ጠባቆች (Apologists) መካከል አንዱ ቅዱስ ሄሬኔዎስም ፩ኛ የእመቤታችን ዘለዓለማዊ ድንግልና፣ ፪ኛ ድንግል ማርያም አማኑኤል ጌታን መውለዷ እና ፫ኛ የማይሞተው አምላክ መሞት በእግዚአብሔር የዝምታ ሸማ የተጠቀለሉ ሦስት ምሥጢሮች መኾናቸውን ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ የተባለው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጸሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ይህን ድንቅ የተዋሕዶ ምሥጢር በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋል፤

‹‹ሦስቱን ደጆች ያልከፈተ የአብን ልጅ ጥበብ አደንቃለሁ፤ ያለ መለወጥ በኅቱም ድንግልና በመወለዱ፣ የመቃብሩን ደጅ ሳይከፍት በመነሣቱ፣ ደቀ መዝሙርቱ ተሰብስበው ወዳሉበት ቤት በተዘጋ ቤት በመግባቱ እና በሩን ሳይከፍት በመውጣቱ ስለነዚህም ሦስት ደጆች ልቤ አደነቀች፡፡ ከሁለቱ ይልቅ የመጀመሪያው እጅግ ያስደንቀኛል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱን ከዚህ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ አውቃቸዋለሁ፡፡ የመቃብሩን ደጅ የሚመስለው ነገር አለ (ዮሐ. ፳፥፲፱)፡፡ ብልጣሶር የተባለ ዳንኤልን በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ በጣሉት ጊዜ ጕድጓዱን በታላቅ መዝጊያ ዘጉት፡፡ ዳንኤልም በረሃብ እንደ ተጨነቀ ልዑል እግዚአብሔር ባየ ጊዜ መልአኩን ወደ ነቢዩ ዕንባቆም ላከ (ዳን. ፮፥፲፮-፲፯)፡፡ በራሱም ፀጕር አንሥቶ ተሸክሞ ወስዶ ዳንኤል ወዳለበት ጕድጓድ አገባው፡፡ ዳንኤልና ዕንባቆም እንጀራውንና ንፍሮውን በልተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ዕንባቆምም ደጅ ተዘግቶ ሳለ ወጣ፡፡ ስለ ቤቱ ደጅም የሚመስል ነገር አለ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶ ጴጥሮስን ከግዞት ቤት እንዳወጣው በሐዋርያት ሥራ ተጽፏል፡፡ ጴጥሮስንም ካወጣው በኋላ ደጁ ተቈልፎ ዘበኞች በዅሉ ወገን ይጠብቁ ነበር (ሐዋ. ፲፪፥፮)፡፡  ለእነዚህ ለሁለቱ ደጆች ለቅዱሳን የተገኘውን ምክንያት አገኘሁ፡፡ ስለ ድንግልናሽ ደጅ እጠናለሁ፤ ግን ምክንያት አላገኘሁም፡፡ በድንግልና የኖረች ሴትም አላየሁም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር ኾኖ አያውቅም፡፡ ኢኮነ እምቅድመ ዝ ወኢኮነ እምድኅረ ዝ – ከዚህ በፊት አልተደረገም፤ ከዚህ በኋላም አይደረግም፤›› (አርጋኖን ዘቀዳሚት)፡፡

በአጠቃላይ በዓለ ልደት፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የተፈጸመበት በዓላችን ነው፡፡ ለሞት ከመገዛት የዳንበት፤ ጨለማው ተወግዶልን የብርሃን ልጆች የኾንበት፤ የእባብ ራስ የተቀጠቀጠበት፤ ከምድር ወደ ሰማይ ያረግንበትና ከመላእክት ጋር ኾነን ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀረብንበት፤ ከነቢያት ኅብረት ጋር አንድ የኾንበት በዓል ነው፡፡ ድንቅ የተዋሕዶ ምሥጢር የተፈጸመበትን ይህን ልዩ በዓል በመንፈሳዊ ሥርዓት ማክበር ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

ለብርሃነ ልደቱ መዘጋጀት

በዲያቆ ዘላለም ቻላቸው

ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

አዳም የድኅነት ቃል ኪዳንን ከእግዚአብሔር ዘንድ ከተቀበለ ከአምስት ሺሕ ዓመታት በኋላ የአዳምን በደል ካሣ ከፍሎ ከራሱ ጋር ሊያስታርቀው እግዚአብሔር ወልድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በተዋሕዶ ሰው ኾነ፡፡ እግዚአብሔር ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ የነበሩ የቃል ኪዳን ዓመታት አምላካችን የፈጸመዉን የድኅነት ሥራ (ሥጋዌ፣ ሞት፣ ትንሣኤ …) የሰው ልጆች እንዲረዱ ለማስቻል ዝግጅት የተደረገባቸው ዘመናት ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘመናት እግዚአብሔር የራሱ የኾኑ ሕዝቦችን እና ሰዎችን በመምረጥና ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት፣ ለእነዚህ ሕዝቦች ተአምራትን በማድረግና ከጠላቶቻቸው በማዳን፣ ከዚህም ባሻገር ነቢያቱን ልኮ ሕዝቡን በማስተማር፣ ትንቢት በማስነገርና ተስፋ በመስጠት (በማጽናናት)፣ ሱባኤም በማስቈጠር አምላነቱንና ዓለምን ለማዳን ያቀደውን ዕቅድ ቀስ በቀስ፣ በጥቂት በጥቂቱ ገልጧል፡፡ በየዘመኑ የተነሡ ነቢያትም ምንም እንኳን አምላክ ይህን ዓለም እንዴት እንደሚያድነው በግልጽ ባይረዱትም እግዚአብሔር ዓለሙን የሚያድንበትን ቀን እንዲያቀርበው እንዲህ እያሉ ይማፀኑ ነበር፤ ‹‹አቤቱ ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው፤ ውረድም … እጅህን ከአርያም ላክ …›› (መዝ. ፻፵፫፥፯፤ ኢሳ. ፷፬፥፩)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ እንደ ገለገጸልን በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ስለሚመጣው ነገር ዅሉ ትንቢት ተናግረዋል፤ ሱባዔ ቈጥረዋል፤ ሕዝቡም የጌታን ማዳን በተስፋ እንዲጠብቅ አስተምረዋል፡፡ ጌታ ሰው ኾኖ የተወለደው ከዚህ ዅሉ ዝግጅት በኋላ ነው፡፡ የአዳኙ መሲሕ የክርስቶስ መወለድ በጉጉት ይጠበቅ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከእስራኤል መካከል ቅን የነበሩትና በእግዚአብሔር መንገድ የተጓዙት ‹‹መሲሑን አገኘነው … ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው፤›› እያሉ ተከትለውታል (ዮሐ. ፩፥፵፩-፵፭)፡፡ እንግዲህ ይህ ታሪክ ከተፈጸመ ጌታችንም ከተወለደ እነሆ ፳፻፲ ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ እኛም የተደረገውን ዅሉ በትውፊት ተቀብለን በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተሳትፈን በዚህ በድኅነት ጉዞ የተሰጡንን ጸጋዎች ተካፍለን ክርስቲያኖች ኾነናል፡፡

‹‹በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደ ተነሣ እኛም እንደ እርሱሐዲስ ሕይወት እንኖራለን፤›› (ሮሜ. ፮፥፬) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንዳስተማረው ክርስትና፣ በጥምቀታችን ሞተን እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነሥተን በትንሣኤው ብርሃን በአዲስ ሕይወት የምንመላለስበት፤ የእግዚአብሔርን ፍቅር እየቀመስን፣ ያደረገልንን ዅሉ እያደነቅን፣ ጸጋውን ዕለት ዕለት እየተቀበልን የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡ በዚህ ክርስቲያዊ ሕይወት ስንኖር አምላካችን ለእኛ ብሎ የፈጸመውን የማዳን ሥራ (ልደቱን፣ ጥምቀቱን፣ ጾሙን፣ መከራውን፣ ስቅለቱን፣ ትንሣኤዉንና ዕርገቱን እንደዚሁም ዳግም ምጽአቱን) ዘወትር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ሕይወታችን ጌታችን የፈጸመዉን ተግባር ዅሉ በማስታወስ፣ በማሰብ እና በመካፈል ላይ የተመሠረተ መኾን ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን በነገረ ድኅነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን የጌታችን ድርጊቶች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እንድናስባቸው አድርጋለች፡፡ የልደትን፣ የጥምቀትን፣ የስቅለትን፣ የትንሣኤን፣ የዕርገትን … በዓላት የማክበራችን ዋናው ምክንያትም ይኸው ነው፡፡

ዳሩ ግን በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሰውነት በኀጢአት በማቆሸሻችንና ራሳችንን ከጸጋ እግዚአብሔር በማራቃችን፣ እንደዚሁም በልዩ ልዩ ሥጋዊ ጉዳዮች ተጠምደን በወከባ በመኖራችን ይህን ማድረግ ይክብድብናል፡፡ እነዚህን በዓላት ስናከብር ከሚያስጨንቁንና ሕሊናችንን ከሞሉት ሥጋዊ ጉዳዮች ተመልሰን በአንድ ጊዜ ወደ መንፈሳዊ ዐሳብና ተመስጦ መምጣት ስለምንቸገር ቤተ ክርስቲያን ከበዓላቱ በፊት የዝግጅት፣ የማንቂያ ጊዜያት እና አጽዋማት እንዲኖሩም አድርጋለች፡፡ በእነዚህ ወቅቶች ሕሊናችንን ቀስ በቀስ ወደ መንፈሳዊው ዐሳብ እና ወደ በዓሉ ጉዳይ ተመልሶና በዓሉን በናፍቆት ጠብቀን በተገቢው ሥርዓት እንድናከብረውም ታዝዛለች፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ በዓላት ከመከበራቸው በፊት አጽዋማት ይኖራሉ፤ ሥጋ ወደሙን ከመቀበላችንም በፊት እንጾማለን፡፡ ሌሎቹም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከመፈጸማቸው በፊት የጾምና የዝግጅት ወቅቶችን ማሳለፍ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንዲከበር ያደረገችው ከእነዚህ ዘወትር ልናስባቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ የኾነዉን ብርሃኑንና ዘወትር ልናየው የሚገባውን የጌታችንን ልደትን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ በተመስጦ እንድናስበውና ብርሃኑን እንድናየው ነው፡፡ ይህችን በዓመት አንድ ጊዜ የምትመጣዋን በዓልም ቢኾን ከማክበራችን በፊት ዐርባ ሦስት ቀናትን በመጾም እንዘጋጃለን፡፡ በመጾም ብቻ ሳይኾን እነዚህ ዐርባ ሦስት ቀናት ተከፋፍለው የልደት በዓልን በተገቢው መንገድ እንድናከብር የሚያዘጋጁ ትምህርቶችን እንማርባቸዋለን፡፡ በተለይም ከልደት በዓል በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት ይህ ዓላማ አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንዘጋጅ ዘንድ እነዚህን ሦስት ሳምንታት የጌታችንን ልደት በናፍቆት በመጠበቅ እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ኾነን እንድናሳልፍ ታደርጋለች፡፡

በእነዚህ ሳምንታት (በተለይም በእሑዶቹ) የብሉይ ኪዳን ነቢያት የአዳኙን መምጣትና የጌታን ቀን መገለጥ በመናፈቅ ስላሳለፏቸው ጊዜያት ደጋግመን በመማር እነዚያን የጨለማ ዘመናት እንድናስታውስና እኛም በእነርሱ መንፈስ ተቃኝተን ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንናፍቃለን፤ በዓሉን ለማክበርም እንዘጋጃለን፡፡ በዓሉን የምናከብረውም እንዳለፈ ታሪክ ለማሰብ አይደለም፡፡ ልክ በዚያች በልደቱ ቀን ከሰብአ ሰገልና ከእረኞች ጋር እንደ ተገኘን ኾነን እናከብረዋለን እንጂ፡፡ ለዚህም ነው የልደትን በዓል ስናከብር ‹‹ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ፤ ዛሬ በክርስቶስ ልደት ደስታ ሐሤት ኾነ›› እያልን የምናመሰግነው፡፡ ‹‹ዮም፣ ዛሬ›› ማለትም በዓሉ የልደት መታሰቢያ ብቻ ሳይኾን በዚያ በልደት ቀን እንደ ነበርን አድርገን የምከብረው በዓል መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ከልደተ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህ ሳምንታት፣ ነቢያቱ፣ አምላክ ይህን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸውና ነገረ ድኅነትን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሳምንታት ናቸው፡፡

፩. ስብከት

ስብከት ማለት ማስተማር ማለት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ከሙሴ ጀምሮ የነበሩ ነቢያት በሙሉ አዳኝ (መሲሕ) እንደሚመጣ ማስተማራቸው፣ ጌታችንም ነቢያት ይመጣል ብለው ያስተማሩለት አምላክ እርሱ መኾኑን መግለጡ የሚታሰብበት ነው፡፡ ሙሴ ለጊዜው የጌታችን ምሳሌ ለሆነው ለኢያሱ ፍጻሜው ግን ለጌታችን በኾነው ትንቢቱ ‹‹አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ስሙት፤›› ብሎ ለሕዝበ እስራኤል ነግሯቸው ነበር (ዘዳ. ፲፰፥፲፭)፡፡ ጌታችንም ይህ ትንቢት በእርሱ መፈጸሙን ሲያመላክት ‹‹ሙሴ እና ነቢያት ዅሉ ስለ እኔ ይናገራሉ›› እያለ አስተምሯል፡፡ ትንቢቱን ያውቁ የነበሩ በእግዚአብሔር መንገድ የሚጓዙ እስራኤላውያንም በቃሌ አምነው ተከትለውታል፡፡ ሐዋርያትና ሌሎች አባቶችም ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ በተለይ የተነገሩትን ትንቢቶች ዅሉ ያውቁ ለነበሩት እስራኤላውያን ያስተማሩት እነዚህን የነቢያት ትምህርቶች እና ትንቢቶች እያጣቀሱ ነበር፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አስተምሯል፤ ‹‹አሁንም ወንድሞቼ ሆይ፥ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለ ማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ዅሉ አፍ እንደ ተናገረ እንዲሁ ፈጸመ፤›› (ሐዋ. ፫፥፲፯-፲፰)፡፡ በሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ ‹‹ወንድሞች ሆይ፥ የቀደሙ ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና ለእኛ ለሐዋርያትም ያዘዘውን የመድኀኒታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ታስቡ ዘንድ … ዕወቁ፤›› (፪ኛ ጴጥ. ፫፥፩-፫)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ ስለ እግዚአብሔር መገለጥ እንዲህ ሲል አስተምሯል፤ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በኋላ ዘመን ግን ዅሉን ወራሽ ባደረገው፥ ዅሉን በፈጠረበት በልጁ ነገረን፤›› (ዕብ. ፩፥፩-፪)፡፡

፪. ብርሃን

ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የፀናበት፣ ሁሉ ነገር አስጨናቂ የሆነበት፣ ሰው ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ያሉበትን ዘመን «ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ የሚያስወግድና ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን እንዲመጣ እንዲህ እያሉ ይፀልዩ ነበር፡፡ ‹‹ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ እነርሱም ይምሩኝ፡፡ አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደራያህ ይውሰዱኝ፤›› (መዝ. ፵፪፥፫)፡፡ ጌታችንም ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ›› በማለት ለዚህ ጸሎት ምላሽ ሰጥቷል (ዮሐ. ፰፥፲፪)፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ብርሃንነቱ መስክረዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ጌታችን ሰው መኾን (ምሥጢረ ሥጋዌ) በተናገረበት በወንጌሉ የመጀመሪያ ክፍል ጌታችንን ብርሃን ብሎታል፡፡ ‹‹ሕይወት በእርሱ ነበረ፤ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፡፡ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሰነፈውም፤›› (ዮሐ. ፩፥፬-፭)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችን በሚያንጸባርቅ ብርሃን አምሳል እንደ ተገለጠበት ተናግሯል፡፡ ‹‹እኩል ቀን በኾነ ጊዜ በመንገድ በሔደ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሔዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንጸባርቅ አየሁ … አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለኝ፤›› (ሐዋ. ፳፮፥፲፫)፡፡

፫. ኖላዊ

ኖላዊ ማለት እረኛ ማለት ነው፡፡ ነቢያቱ ራሳቸውን እና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደ ተዋቸው እና እንደ ተቅበዘበዙ በጎች በመቍጠር እንዲሰበስባቸውና እንዲያሰማራቸው እንዲህ እያሉ ይማጸኑ ነበር፤ ‹‹ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ (እረኛ) ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ፤›› (መዝ. ፸፱፥፩)፡፡ ጌታችንም ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጥቷል፤ ‹‹ቸር ጠባቂ (እረኛ) እኔ ነኝ፡፡ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል፤›› (ዮሐ. ፲፥፲፩)፡፡

ማጠቃለያ

ዛሬም እኛ በኀጢአት ስንዋከብ ዘወትር ልናየውና ልንመላለስበት የሚገባን ብርሃነ ልደቱ ተሰውሮብናል፣ ከቸር እረኛችን የራቅን የተቅበዘበዝን በጎች ኾነናል፡፡ አንዳንዶቻችን በምናስበው ዐሳብ፣ በምንሠራው ሥራ ውስጥም የአምላክን ሰው የመኾን ምሥጢር ረስተነዋል፡፡ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንዳልተወለደ ነው፡፡ ስለዚህ ያጣነውን ይህን ጸጋ ለማግኘትና ብርሃነ ልደቱን ለማየት፣ በዚያ ውስጥም ለመመላለስ የክርስትናችንን እና የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት ለመጨመር መሻት አለብን፡፡ ስለዚህ እስኪ እኛም በእነዚህ ሳምንታት የብሉይ ኪዳን ሰዎች የነበሩበትን ኹኔታ እየዘከርን፣ ያለንበትን አኗኗር እየመረመርን፣ ስላጣነው ብርሃን ለማሰብ፣ ያጣነውን መልሰን ለማየትና ለማግኘት እንትጋ፡፡ መጻሕፍትን ለማንበብ፣ በጉዳዩ ላይ በተመስጦ ለማሰብ እና ለመወያየት ጊዜ እንስጥ፡፡ ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንዲያበቃንም ‹‹አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ ቸሩ እረኛችን ሆይ፥ ተቅበዝብዘናልና እባክህ ሰብስበን›› እያልን እግዚአብሔርንእንማጸነው፡፡ ሰው ከነኀጢአቱ ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ሊቀርብና ብርሃኑን ሊያይ አይቻለውምና በንስሐ ራሳችንን እናጽዳ፡፡ እነዚህን ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችልንን የዝግጅት ጊዜያት በሚገባ ከተጠቀምን ትርጕም ያለው፣ በሕይወታችንና በመንገዳችን ላይ ለውጥ የሚያመጣ ልዩ የልደት በዓል እናከብራለን፡፡ አምላካችን ብርሃነ ልደቱን እንድንመለከት ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ኖላዊ ኄር

በመሪጌታ ባሕረ ጥበባት ሙጬ

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

‹‹ኖላዊ ኄር›› የሚለው ሐረግ ‹ኖላዊ› እና ‹ኄር› ከሚሉ ሁለት ቃላተ ግእዝ የተዋቀረ ነው፡፡‹ኖላዊ› ማለት ‹እረኛ፣ ጠባቂ› ማለት ሲኾን፣ ‹ኄር› ደግሞ ‹መልካም፣ ቸር ርኅሩኅ፣ አዛኝ› የሚል የአማርኛ ትርጕም አለው፡፡ ስለዚህ ‹ኖላዊ ኄር› ማለት ‹መልካም እረኛ› ማለት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ቅዱስ ያሬድ ባዘጋጀው ስያሜ መሠረት ከታኅሣሥ ፳፩-፳፯ ያለው ሳምንት ‹ኖላዊ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሳምንቱ ካልጠፉት ዘጠና ዘጠኝ መንጋዎች ይልቅ የጠፋውን አንዱን በግ ፍለጋ የመጣው የእረኞች አለቃ፣ መልካሙ እረኛ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታሰብበት ሳምንት ነው፡፡ ቸር ጠባቂያችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኝነት የባሕርዩ ነው፡፡ ‹‹አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር ዘበአማን፤ እውነተኛ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤›› በማለት እንደ ተናገረው (ዮሐ. ፲፥፲፩)፡፡ ጌታችን ይህን መለኮታዊ ሥልጣኑን ለቅዱሳን በጸጋ አድሏቸዋል፡፡ ‹‹… ግልገሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ›› በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ሥልጣን ለዚህ ማሳያ ነው (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯)፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ስለ መንጋቸው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡትን ታላላቅ መልካም እረኞችን የመረጣቸው ከበግ እረኝነት ነው፡፡ አምላካችን ለሕዝቡ የሚራራ ቸር ጠባቂ ነውና የጦር ስልት ከሚያውቁ ኃያላን የጦር ዐርበኞች በግ ጥባቂዎችን ለእረኝነት ይመርጣል፡፡ ቀድሞም ለበግ ጥበቃ በትረ ሙሴ እንጂ የጦር መሣሪያ መቼ ያስፈልግና? መልካም እረኞች የበጎችን ጠባይዕ ያውቃሉ፡፡ ለበጎች ምን እንደሚያስፈልጋቸውም ይረዳሉ፡፡ መልካም እረኞች ለበጎች ይራራሉ፤ ስለዚህም ወደ ለመለመ መስክ፣ ወደ ንጹሕ ምንጭ ይመሯቸዋል። የተሰበሩትን ይጥግኗቸዋል፤ የደከሙትንም ያበረቷቸዋል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም በጎችን ከአንበሳ መንጋጋ፣ ከተኩላ ንጥቂያ ይከላከላሉ፡፡

ከበግ እረኝነት ወደ ታላቅ የሕዝብ መሪነት ከተመረጡት አንዱ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው። ለሙሴ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ ያስገኘለት የቤተ መንግሥት ኃያልነት፤ ዐርበኝነት እና የልዑልነት ማዕረግ ሳይኾን ለእግዚአብሔር መታመኑና ለ፵ ዓመታት በምድያም ተራራዎች፣ በሲና በረሃዎች በሎሌነት ያሳለፈው የበግ እረኝነት ተግባሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ሙሴ ከግብፅ ያመጣውን ትጥቅ አልፈለገውምና ‹‹ኢትቅረብ ዝየ ፍታሕ አሣዕኒከ እምእገሪከ እስመ መካን እንተ አንተ ትቀውም ባቲ ምድር ቅድስት ይእቲ፤ የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማኽን ከእግርኽ አውጣ፤›› በማለት አዝዞታል (ዘፀ. ፫፥፭)፡፡ የቃል ኪዳኗ ምድር የምትወረሰው በእረኛ በትር እንጅ በልዑላን ሰልፍ አይደለምና፡፡ ሙሴ ከሕፃንነት እስከ ጕልምስና የሚያውቀው የፈርኦንን ሕግ እንጅ ስለ እረኞች አልነበረም፡፡ ለመቶ ዓመታት በባርነት ስቃይና ከሞት ጋር ሲተናነቅ ለኖረ ሕዝብ የፈርኦናውያን ሕግ ምን ለውጥ ያመጣለታል?

ክንደ ብርቱው ሙሴ ከቤተ መንግሥት ልዑልነት ይልቅ ወደ ሎሌነት ወርዶ፣ ሥጋዊ ሓላፊነትን ንቆ፣ የቤተ መንግሥት ዝናሩን አውልቆ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጠው የእረኝነት ሥልጣን የኃያልነት ዝናርን ታጥቋል፡፡ ለበጎቹ ሲልም በሲና በረሃ እሳት ነዶበታል። በእረኝነቱም ሕዝቡን ከጥፋት ለመታደግ ከበረሃ አውሬዎች ጋር ታግሏል፡፡ በእረኝነት ተግባር ብቻ ሳይኾን በየዋህቱም አርአያ ኾኗል፡፡ በመከራ እና በስቃይ የኖረ ሕዝብ የቃል ኪዳኗን ምድር ለመውረስ የሚጓዘው ሙሴ በረኝነት በነበረበት የበረሃ ምድረ አቋርጦ ነው፡፡ ጉዞው የሚወስደው ጊዜ ደግሞ ዐርባ ዓመታትን ነው፡፡ መንጋውን ለመምራት ለ፵ ዓመት የበረሃውን ሕይወት ከሚያውቀው ከሙሴ በቀር ማን ይችላል? ለዚህም ነው ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን ዓምድ ውኃ እያፈለቀ፣ መና እያወረደ የቃዴስን ሐሩር ያሳለፋቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ  በእስራኤል ልጆች ላይ በነደደች ጊዜ እንኳን ራሱን ስለ እነርሱ አሳልፎ የሚሰጥ መልካም እረኛ ኾኖ ተገኝቷል – ነቢዩ ሙሴ፡፡ ‹‹ወይእዜኒ እመ ተኀድግ ሎሙ ዘንተ ኃጢአተ ኅድግ ወእመ አኮሰ ደምስስ ኪያየኒ እመጽሐፍከ ዘጸሐፍከኒ፤ ሕዝብኽን ይቅር የማትላቸው ከኾነ እኔን ከጻፍኸው መጽሐፍኽ ደምስሰኝ›› በማለት መማጸኑም ስለዚህ ነው፡፡ የዚህ መልካም እረኛ ጸሎትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝቷል (ዘፀ. ፴፪፥፴፪)፡፡

‹‹ረከብክዎ ለዳዊት ወልደ ዕሴይ ብእሴ ምእመነ ዘከመ ልብየ፤ ዘይገብር ኵሎ ፈቃድየ፤ ፈቃዴን ዅሉ የሚያደርግ የዕሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ›› (ሐዋ. ፲፫፥፳፪) ብሎ እግዚአብሔር የመሰከረለት ቅዱስ ዳዊት የተጠራውም ከበግ ጠባቂነት ነው፡፡ ለንጉሥ ሳኦል በወታደርነት የሚያገለግሉት የጦርነት ልምድ ያላቸው፣ በሰውኛ ዓይን ለቅብዐ መንግሥት ይበቃሉ ተብለው የሚታሰቡት ታላላቆቹ የዕሴይ ልጆች የነቢዩ ሳሙኤልን ቀርነ ቅብዕ ሲጠባበቁ ታናሹ ብላቴና ዳዊት ግን ያባቱን በጎች በዱር ይጠብቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ስለ ብጎቹ ሲል ከአንበሳ ጋር የሚተናነቀውን ታናሹን ብላቴና ዳዊትን መረጠ፡፡ እግዚአብሔር ዳዊትን ለንግሥና እንደ መረጠው የተረዳው ነቢዩ ሳሙኤልም መልእክተኛ ልኮ ዳዊትን አስጠርቶ ቅብዐ መንግሥትን ቀብቶ አነገሠው፡፡ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ አደረ (፩ኛ ሳሙ. ፲፮፥፲፪-፲፫)፡፡

ስለ መልካም እረኛ ሲነሣ በአብነት ከሚጠቀሱ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል በረከታቸው ይደርብንና ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አንደኛው ናቸው፡፡ ጠላት አገራችንን በወረረበት፣ በመንጋው ላይ መከራ እና ችግር በጸናበት፣ እንደዚሁም የንጹሐን ደም በግፍ በፈሰሰበት በዚያ በፈተና ወቅት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያንም ለአገርም የሚያስቡ መልካም እረኛ እንደ ነበሩ የታሪክ መዛግብት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከዐርበኞች ጋር ኾነው ሕዝቡ ለጠላት እጁን እንዳይሰጥና ሃይማኖቱን እንዳይለውጥ ከማስተማራቸው፣ ከማጽናናታቸው ባሻገር በጠላት ፊት ለፍርድ በቀረቡበት ጊዜም መልካም እረኝታቸውን በዐደባባይ መስክረው፣ ለሕዝብ፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር በመቆርቆራቸው በጥይት ተደብድበው በሰማዕትነት አልፈዋል፡፡

ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው፡፡ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል፡፡ ምንደኛ (ቅጥረኛ) እረኛ ግን ለበጎቹ አይጨነቅም፤ በጎቹም አያውቁትም (ዘካ. ፲፩፥፬-፭፤ ዮሐ. ፲፥፩-፲፪)፡፡ ዛሬም በእናት ቤተ ክርስቲያናችን የተሾሙ አባቶች እንደነሙሴ፣ እንደነዳዊት፣ እንደነብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያንም ለአገርም የሚጨነቁ ሊኾኑ ይገባል፡፡ እኛ ምእመናንም እግዚአብሔር አምላካችን መልካም እረኞችን እንዳያሳጣን መለመን ይኖርብናል፡፡ እንደዚሁም ራሳችንን ለሃይማኖታችን ማስገዛት፣ መልካም እረኞችንም አብነት ማድረግና መከተል ይጠበቅብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡