ማኅበረ ቅዱሳን የ20 ዓመት ጉዞውን ሊገመግም ነው፡፡
ነሐሴ 1 ቀን 2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደጀኔ
ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ያሳለፋቸውን ሁለት ዐሥርት ዓመታት ጉዞውን የሚገመግም መሆኑ ተገለጸ፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም በነሐሴ ወር የሚደረገውን የማኅበሩን ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክተው እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን ያከናወናቸው የ20 ዓመት ጉዞዎች በጠቅላላ ጉባኤው ላይ አንሥቶ እንደሚገመግም ገልጸዋል፡፡
ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ በየ2 ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ መጀመሩን የገለጹት ሰብሳቢው ማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ታሪካዊ ነው ብለዋል፡፡ ከነሐሴ 26-28 ቀን 2004 ዓ.ም. ለ3 ቀናት በሚዘልቀው ጉባኤ ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ሲሆን በዚህም ጉባኤ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ማእከላት፣ ወረዳ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት የሚሳተፉበት እንዲሁም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለ3 ቀናት በሚካሄደው 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቀጣይ የ4 ዓመት ስልታዊ እቅድ ከማጽደቅ ጀምሮ ቀጣዩን የአመራር ምርጫም እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ለ10ኛ ጊዜ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ከሀገር ውስጥ 44 ማእከላት፣ ከውጪ 9 ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች፣ 303 ወረዳ ማእከላት፣ እንዲሁም የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች እንደሚገኙና ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ ከአንደ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በጉባኤው ላይ ይታደማሉ፡፡