ማኅበረ ካህናት ዘሰሜን አሜሪካ Mahibere Kahinat North America
ከሁሉ አስቀድመን እኛ የመንፈስ ልጆቻችሁ ካለንበት ከሰሜን አሜሪካ ሆነን ቡራኬአችሁ ይድረሰን እንላለን!
ውድ አባቶቻችን የታላቋ ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ላለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ ለሁለት መከፈል ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰውን ውድቀት በእኛ በመንፈስ ልጆቻችሁ ካህናት እንዲሁም ምዕመናን ላይ የደረሰውን ሐዘን ታላቅነት ለቤተ ክርስቲያን ከእናንተ በላይ የቀረበ ባለቤት ስለሌላት ከእናንተ በላይ የሚረዳው ሊኖር አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በኢትዮጵያ ከመንግሥት ምሥረታ ጀምሮ የነበራትን አስተዋጽዖ፣ እንዲሁም በዕውቀት ምንጭነትና በታሪክ መሠረትነት የነበራት ስፍራ እየደበዘዘ ተቀባይነቷ እየቀነስ፣ እንዲሁም ለአገር ግንባታና ለትውልድ ጥቅም ልታውለው የምትችለው የእናንተ የአባቶቻችን ሊቃውንት ዕውቀትና የእኛ የልጆቿ የካናትና ጸጋ፣ የምዕመናን ልጆቿ የትምህርት ችሎታ፣ ገንዘብና የሰው ኃይል በአንድነት እጦት ባክኗል፤ እየባከነም ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም ሲቆጫችሁና ሲያንገበግባችሁ እንደኖረም እኛ ካህናት በቅርብ ስለ ምናውቃችሁ ነጋሪ አያሻንም፡፡ ከዚህም የተነሳ እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ ካህናት የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ለማስመለሰ የበኩላችንን ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡
በሀገራችን በኢትዮጵያ ወቅቱ የይቅርታና የመቻቻል ጊዜ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ስትጸልዩበት ስታለቅሱበትና ስትናፍቁት የነበረው የኢትዮጵያ ትንሣኤ እየታየ ያለበት ወቅት ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ተለያይተውና ተራርቀው በጠላትነት ይፈራረጁና አንዱ ሌላኛውን ሽብርተኛ ይል የነበረበት ሁኔታ ተቀይሮ አንዱ ለአንዱ ምሕረት እያደረገ እየታረቁ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በብዙ ዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች በመንግሥት ምሕረት እየተፈቱ የሚገኙበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ወቅቱ የጸሎታችሁንም ውጤት በዓይታችሁ እያያችሁ የምትገኙበት ወቅት ነው፡፡ ይህ እየሆነ በሚገኝበት በዚህ ወሳኝ የይቅርታ ወቅት ከይቅርታ መምህራን የሚጠበቀውን ይቅርታ ለታላቋ ቤተ ክርስቲያናችን ተልዕኮ ስትሉ አለመተግበር የእኛን የልጆቻችሁን ልብ ምን ያህል ሊጎዳ እንደሚችልና ይልቁንም አሁን የሚደረገው እርቅ ባይሳካ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ ምን ያህል እንደሚያወሳስበውና አገልግሎታችንንም ምን ያህል እንደሚጎዳው እንድትረዱልን እንወድዳለን፡፡
እኛ የሰሜን አሜሪካ ካህናት እናንተን አባቶቻችንን ወደ ላይ መናገር ሥርዓቱም የክህነቱ የሥነ ምግባር ሕግም እንደ ማይፈቅድልን እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ ልጅ የጎደለበትን ለማግኘት አባቱን መጠየቅ የልጅነት ወጉ በመሆኑ የልጅነት መብታችንን ተጠቅመን በልጅነታችን እንድትፈጽሙልን የምንሻውን ጥያቄ በልጅነት ፍቅር ስናቀርብ በአባት ፍቅር ተረድታችሁ እንድትመልሱልን በታላቅ አክብሮትና ትሕትና የሚከተሉትን ጥያቄዎቻችንን እናቀርባለን፤
1ኛ. እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት በወሰደው ለውጥ እርምጃ በሕግ ሽብርተኛ የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሽብርተኛ መዝገብ ነጻ በሆኑበት፣ ለ20 ዓመታት በጠላትነት ይፈላለጉ የነበሩ ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች ያለቁበት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች የጦርነት ታሪክ ተቋጭቶ እርቅ የተፈጸመበት ወቅት ነው፡፡ ስለዚህ አባቶቻችንን የምንጠይቅበት በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ውጭ ባለው አስተዳደር ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈው ውግዘት ለዕርቁ ስኬት ሲባል አስታራቂ አባቶች ወደ ሰሜን አሜሪካ ከመምጣታቸው በፊት እንዲነሳ እንጠይቃለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሰበብ አስባቡ እርቁ ባይሳካ በውጭ ያለው አስተዳደር ኢትዮጵያ ገብቶ ጽ/ቤት ከፍቶ ሥራውን ለመጀመር የሚያዳግተው ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተጽዕኖ እንደማይኖር በመንግሥት የተረጋገጠ ስለሆነ ይህን ጥፋት ለማስቀረት ወቅቱ አሁን መሆኑን ለአባቶቻችን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
2ኛ. እኛ የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት ቤተ ክርስቲያናችን ከዚህ በፊት የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚብሔር የስጣትን ዕድል ሳትጠቀምበት የቀረችበት ጊዜ አያሌ በመሆኑ የተሰማን ሐዘን ከፍተኛ ቢሆንም ዳግመኛ ዕድል መስጠት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር አሁን የሰጣት ዕድል ወሳኝ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ይህን ዕድል እንድትጠቀምበት አባቶቻችንን በታላቅ አክብሮት እየጠየቅን ይህ ሳይሆን ቀርቶ እርቁ ሳይሳካ ቢቀር በአንዲት እምነት ሁለት አስተዳደር ምክንያት ከማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት በላይ ተጎጂ የሆንነው እኛ የሰሜን አሜሪካ ካህናት በመሆናችን ቤተ ክርስቲያናችንን ለመታደግ ያለ ምንም ልዩነት የአገር ውስጥና የውጭ አስተዳደር ብለን ሳንከፋፈል ለማገልገል የወሰንን መሆናችንን በትሕትና እናስታውቃለን፡፡
ስለዚ ውድ አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያናችን የበለጠ ችግር ውስጥ ከመግባቷ በፊት ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር የሚበጅ የለውጥ እርምጃ እንድትወስዱ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ከዚህ ደብዳቤ ጋር የማኅበሩ አባላት የ246 ካህናትን ሥም ዝርዝር አባሪ አድርገን የላክን መሆኑን እንገልጻለን፡፡
መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ሰይፈ ገብርኤል አብሰን
የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት ሰብሳቢ
ግልባጭ፡-
- ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊት ዲሞክራሲያዊት መንግሥት ጠ/ሚ ጽ/ቤት