የሚዛን ተፈሪ ማዕከል 14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

 

ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በሚዛን ተፈሪ ማዕከል ሚዲያ ክፍል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የሚዛን ተፊሪ ማዕከል ከሰኔ 13 እስከ 15 2006 ዓ.ም 14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ በአቡነ ተክለ ሃይማኖትና ቅዱስ ኡራኤል የእናቶች አንድነት ገዳም የስብከተ ወንጌል አዳራሽ አካሄደ፡፡

ሦስት ቀናት በፈጀው ጉባኤ የማእከሉ 2006 ዓ.ም ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማዕከሉ ሰብሳቢ በአቶ መስፍን ደጉ የቀረበ ሲሆን፤ በእቅድ አፈጻጸሙ በተገቢው ሁኔታ የተከናወኑትን፤ ያጋጠሙ ችግሮች ፤ የተወሰዱ የመፍትሄ ሃሳቦች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ችግሮች ከአባላት የአገልግሎት ዝለት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ክፍሎች ያቀዷቸውን እቅዶች አባላት የማስፈጸም አቅማቸዉ ያልተመጣጠነ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መሠረት የተሻለ የእቅድ አፈጻጸም እንዲሁም ዝቅተኛ የዕቅድ አፈጻጸም ያሳዩ ክፍሎችም ተለይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ለ2007 ዓ.ም. ክፍሎች ራሳቸውን በማጠናከር ያቀዷቸውን እቅዶች ተግባራዊ በማድረግ ጠንክረው እንዲሰሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የ2007 ዓ.ም ዕቅድ በማዕከሉ የዕቅድ ዝግጅትና ከትትል ክፍል ቀርቦም በውይይት በማዳበር ማስተካከያ ተደርጎበት ጸድቋል፡፡

ከማእከሉ አባላት በተጨማሪም ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከዋናው ማዕከል፣ ከምዕራብ ማዕከላት ማስተባበርያ፣ ከወረዳ ማዕከላት፣ ከግቢ ጉባኤያትና ከግንኙነት ጣብያዎች ተወክለው የመጡ እንግዶች በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡