adye abeba 2006

“በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት” ሉቃ.13÷6-9

ዲ/ን ተስፋሁን ነጋሽ

ጳጉሜ 3/2006 ዓ.ም.

adye abeba 2006

 

ጌታችንና መድኃኒታችን ፈጣሪያችንና አምላካችን እግዚአብሔር ወልድ /ኢየሱስ ክርስቶስ/ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አድርጐ ወንጌልን አስተምሯል፡፡ በምሳሌ ማስተማር ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት ሲያስተላልፉት ምግብን በጣፈጠ መረቅ ፈትፍቶ እንደማጉረስ ያህል ይሆናልና፤ እንዲሁም አንድ መልእከት በምሳሌ ጣፍጦ በቋንቋ ዘይቤ ተውቦ ሲቀርብ ምሥጢሩ ልብን ይማርካል፡፡ ስለዚህ የሰው አእምሮ በሃይማኖት ልጓም ተስቦ ለምግባረ ጽድቅ እንዲዘጋጅ ጌታችን ለነጋዴው በወርቅ በዕንቁ፣ ለገበሬው በእርሻ በዘር፣ ለባልትና ባለሙያዎች በእርሾ በቡሆ፣….. ወዘተ እየመሰለ ያስተምር ነበር፡፡ ማቴ.4÷30፡፡

እኛም ጌታ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል ለወቅቱ የሚስማማውን መርጠን እንመለከታለን በሉቃ.13÷6-9 ላይ ይህንንም ምሳሌ መሰለ “ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት አጠገብ የተተከለች በለስ ነበረች ግን ፍሬ ሊፈልግባት ቢመጣ ምንም አላገኘም፡፡ ስለዚህ የወይን አትክልት ጠባቂዋን እነሆ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁምና ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳሉቁላለች? አለው፡፡” እርሱ ግን መልሶ ጌታ ሆይ ዙሪያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት፡፡ ወደ ፊት ግን ብታፈራ ደህና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ አለው፡፡” ተብሎ ተጽፏል፡፡

ይህ ከላይ የተገለጸው ምሳሌ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲተረጐም /ሲመሰጠር/ እንዲህ ነው፤ የወይን አትክልት የተባለች ኢየሩሳሌም ናት፣ አንድ ሰው የተባለ እግዚአብሔር ነው፣ በለስ የተባሉ ደግሞ ቤተ እስራኤል ናቸው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም” ይላል ኢሳ.46÷25፡፡ ራሱ ጌታችንም “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው፡፡” ብሏል ዮሐ.4÷35 ፡፡ ስለዚህ ሰማያዊያን መላእክትን እንዳይራቡ ያደረገ አምላክ እስራኤል ዘሥጋን ገበሬ በማያርስበት ዘር በሌለበት ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ መና ከሰማይ አውርዶ የመገበ ጌታ ተራበ ሲባል ያስገርማል! ግን ፍጹም አምላክ እንደመሆኑ ፍጹም ሰው ሆኗልና አልተራበም አንልም፤ በሥጋ ተርቧልና የዕፀ በለስ ፍሬን ፈለገ፡፡

ይኸውም የበለስ ውክልና ከተሰጣቸው ቤተ እስራኤል የሃይማኖትና የምግባር ፍሬን እንደፈለገ ያመለክታል፡፡ “በለስ ዘይቤ ቤተ እስራኤል እሙንቱ” ተብሏልና እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን በቅዱሳን ነቢያት አድሮ የሃይማኖት /የምግባር/ ፍሬ ባገኝባቸው ብሎ ወደ እስራኤል ሔደ፤ ግን ምንም አላገኘም፡፡ እንዲያውም ሕዝቡ ቅዱሳን ነቢያትን በመጋዝ እየሰነጠቁ፣ በምሳር እየፈለጡ በማጥፋት ከዘመን ዘመን ወደተለያየ አዳዲስ ባዕድ አምልኮአቸው ሲገቡ አየ፡፡ ስለዚህ የበለስዋን ጠባቂ “ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም ፍሬ አላገኘሁባትምና ቁረጣት” አለው፡፡ ሦስት ዓመት ያለው ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ነገሥታትና ዘመነ ካህናትን ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የወይን ጠባቂዋ የተባለ መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል “ተራድቼ ሥራ እስካሠራቸው ድረስ የዘንድሮን ይቅር በላቸው” እያለ መለመኑን ያጠይቃል፡፡

አንድም ሰው የተባለ አብ ቢሉ በልጁ ህልው ሆኖ፣ ወልድ ቢሉ ሰው ሆኖ ሃይማኖት፣ ምግባር ፍለጋ ወደ እስራኤል ሄደ፡፡ ሦስት ዓመት በመዋዕለ ስብከቱ እየተመላለሰ ሲያስተምራቸውም ምንም ፍሬ አላፈሩምና “ይህችን ዕፀ በለስ ቁረጣት” አለው፡፡ መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ግን “ተራድቼ ሥራ እስካሠራቸው ድረስ ይቅር በላቸው፡፡” ብሎ ለመነ የጌታን ትምህርት ያልተቀበሉ አይሁድ ግን የንስሐን ፍሬ ለማፍራት በጄ የሚሉ አልሆኑም፡፡ በአንደበታቸው የአብርሃም ልጆች ነን ይላሉ፤ ነገር ግን የአብርሃምን ሥራ ሊሠሩ አልቻሉም፡፡ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው” እንዲል፡፡

ስለዚህ ጌታ ከዕፀ በለሷ ዛፍ ምንም የሚበላ ፍሬ ስላላገኘ ረገማት፡፡ አንድም ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረገመ፡፡ “በአንጻረ በለስ ረገማ ለኃጢአት” እንዲል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ጉዳይ እስራኤል ከበረከት ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳገኙ ሲገልጽ “አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾህ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፡፡” ብሏል፡፡

ዛሬም ገበሬ ዘርን ዘርቶ አርሞና ኮትኩቶ ከአሳደገ በኋላ የድካሙን ፍሬ እንደሚጠብቅ ሁሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችንም በድንቅ መግቦቱ ከአሳደገን ልጆቹ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬን ይፈልግብናል፡፡ ግን ጌታ ወደ በለስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይሆን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ የሚገባውን ፍሬ እንድናፈራ ያዘናልና መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳይደክም፣ እንዳይጠወልግ፣ እንዳይደርቅና አላስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ወደ እሳት እንዳይጣል የንስሐን ፍሬ ልናፈራ ይገባናል፡፡ ሕይወት ያለ ንስሓ ክንፍ እንደሌላት ወፍ ናትና፡፡

በንስሓ ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱ ሰዎች ግን ይቅርታን /ምሕረትን/ ያገኛሉ፡፡ እግዚአብሔር የሚመለከተው ያለፈ ማንነታችንን ሳይሆን የዛሬውንና የወደፊቱን ሕይወታችንን ነውና፡፡ ቅዱስ ያሬድ “ኢተዘኪሮ አበሳ ዚአነ ኢኃደገነ ፍጹመ ንማስን ኄር እግዚአብሔር ኃጢአታችንን በማሰብ እንጠፋ ዘንድ ከቶ አልተወንም ቸር አምላክ ነውና” እንዲል፡፡ አዎ! እኛ በንስሓ ከተመለስን አምላካችን በኃጢአታችን ላይ አያስኬደንም፤ እርሱ የኃጢአታችንን አድራሻ ክረምት በፈለቀው ባሕር ውስጥ ይጥለዋልና፡፡ ሚክ.7÷18፡፡

እኛ ሰዎች ልብ ካልን በአዲሱ የዘመን መለወጫ ከተፈጥሮ እንኳ ብዙ ነገር መማር እንችላለን፡፡ አዝርእት፣ እፅዋት፣ ታድሰው፣ ቅጠላቸው ለምልሞ በአበባ ተንቆጥቁጠው እናያለን፡፡ ጋራ ሸንተረሩ አረንጓዴ ለብሶ፣ አፍላጋት በየቦታው እየተንፎለፎሉ፤ አዕዋፍ በዝማሬ፣ እንስሳት በቡረቃ ሰማይ ምድሩን ልዩ ያደርጉታል፡፡ ታዲያ ግዑዛኑ ፍጥረታት ጽጌ መዓዛቸውን የአዲስ ዓመት መሥዋዕት አድርገው ሲያቀርቡ እኛስ ምን ይዘናል?

ሰው ሠራሽ ሆኖ መዓዛ የሌለውን፣ ፍሬ የማያፈራውንና አበባ መሰሉን ሳይሆን፣ እግዚአብሔር የፈጠረውን፣ ያለመለመውንና አብቦ መልካም መዓዛ የሚሰጠውን የተፈጥሮ አበባን እንሁን፡፡ ያን ጊዜ ዝንቦች ሳይሆኑ ንቦች ማርን ለማዘጋጀት ይቀስሙናል፡፡ ስለዚህ በሃይማኖት ብቻ ያይደለ በምግባርም እናብብ፡፡ ያን ጊዜ ከዘማሪው ክቡር ዳዊት ጋር “በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል የምድረ በዳ ተራራሮችም ይረካሉ” ብለን ለመዘመር እንበቃለን፡፡ መዝ.64÷11-13፡፡

በአጠቃላይ አዲስ ዘመን የአምላክ ስጦታ /በረከት/ ነው፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው ዘመኑ በፈጣሪ ምልጣን የተያዘና የተገደበ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፤ ሰው ዘመኑ እንደ ሣር ነው፡፡ እንደ ዱር አበባም ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ያልፋል” በማለት ሰው ካደገ በኋላ በሕመም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወለዳል፡፡ ባለፈው ዓመት ብዙዎች ወደሞት መንደር ደርሰዋል፤ እኛም እንደነርሱ መንገደኞች መሆናችንን እንርሳ፡፡

ባለቅኔው፡-
“በሉ እናንተም ሒዱ የእኛም ወደዚያው ነው ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው” እንዲል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም በበኩሉ “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት የሰው ሁሉ ክብሩ ሥጋዊ ሕይወቱና ተድላ ደስታው አንድ ጊዜ፣ አንድ ወቅት ለምልሞና አምሮ የሚታይ ሆኖ ሳለ ያው ደግሞ ሳይቆይ የሚጠፋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢሳ.40÷8፡፡ ስለዚህ በአዲሱ ዘመን ራሳቸውን ለከፍተኛ ግብ የሚያዘጋጁ ሁሉ ወደ ተቀደሰ መንፈሳዊ ሕይወት ሊሸጋገሩ ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠን እድሜም የአጭር ጊዜ እንግዳ መሆናችንን ስለሚያስገነዝበን የምንሸኘውም እንዲሁ ባልታወቀ ጊዜ ውስጥ መሆኑን በመረዳት እውነተኛ ሃሳባችንና ሥራችንን ለተተኪው ትውልድ የማይረሳ አስመስጋኝ ቅርስ መሆን አለበት፡፡

እንዲህ ዓይነቱ መልካምነት ደግሞ ለክርስቲያን በአዲሱ ዘመን እንደሎተሪ ዕጣ የሚደርሰው ሳይሆን ራሱ ፈልጐ የሚሆነው ነው፡፡ ስለዚህ ይልቁንም በአሁኑ ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉ ፍጻሜ እያገኘ ባለበት ዘመን ፍቅር በጠፋበት ዘመን አብዛኛው ሕዝብ ለማይረባ ነገር ብሎ ደገኛ ሃይማኖቱን እየለቀቀ ወደ አልባሌ ቦታ ሲገባ የሕይወት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ እኛ በአዲሱ ዓመት የሕይወት ለውጥን ካሳየን የእግዚአብሔር ጸጋ በውስጣችን ሥራውን በመጀመር በአንድ ሰንሰለት ላይ በርካታ የሕይወት ለውጥን ያመጣልናል፡፡ ይህ የሕይወት ለውጥ በአዲሱ ዘመን ውስጥ ለመኖሩ ተግባራዊ መለኪያው ደግሞ ቀጣይነቱ፣ ፍጹም ተጋድሎውና ግልጽ መሆኑ ነውና ራሳችንን እንመርምር፡፡ 1ጢሞ.4÷7፡፡

ባለቅኔው፡-

“አዲስ ሰው ስትሆን ጽድቅን ሳታፈራ እንዲያው እንደታጠርክ በክፋት ወጋግራ አሮጌውን ሳትጥል አዲስ መደረቱ የዘመን ቅበላ ይቅር ምናባቱ!” እንዲል፡፡

የዚያች የወይን ጠባቂ “ወደፊት ብታፈራ ደህና ነው ያለበለዚያ ግን ትቆርጣታለህ” እንዳለ ለነፍሳችን አንድ ነገር ሳንይዝ፣ ዘመናችን እንዳያረጅና እንዳይቆረጥ ዛሬ ለበጐ ሥራ እነነሣ፡፡ መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም “ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል” ይላልና፡፡ ማቴ.3÷10 እነሆ ! ዛሬ ግን እንደ እግዚአብሔር ቸርነት አሮጌውን ዓመት አሳልፈን ለአዲሱ ዓመት በቅተናል፡፡ ስለዚህ አዲሱን ዓመት በመንፈሳዊ ሕይወታችን ጐልምሰን፣ ሁላችንም ለተቀደሰ ዓላማ ተሰልፈን፣ ከክፉ ምግባራችንም ተመልሰን የምንቀደስበት የምንባረክበት የሰላም፣ የጤናና የደስታ ዘመን ያድርግልን አሜን!!