የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 118ኛውን ፓትርያርክ መረጠች
ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለ40 ዓመታት ቤተ ክርስቲያኗን ሲመሩ የነበሩትንና በቅርቡ ያረፉትን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ለመተካት 118ኛውን ፓትርያርክ እሑድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. በታላቅ ሥነ ሥርዓት መረጠች፡፡
በካይሮ አባሲያ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በተደረገው የእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በእጩነት ከቀረቡት 3ቱ አባቶች መካከል አንዱን በፓትርያርክነት ለመሾም ዓይኑን በጨርቅ የተሸፈነ ሕፃን እጣውን እንዲያወጣ በማድረግ ብፁዕ አቡነ ታዋድሮስ / ቴዎድሮስ/ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ታዋድሮስ በ1952 እ.ኤ.አ የተወለዱ ሲሆን በፋርማሲ ሳይንስ ከአሌክሳንደሪያ ዩኒቨርስቲ ተመርቀዋል፡፡ከ1997 እ.ኤ.አ ጀምሮ በጵጵስና ተሹመው የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ አምስት ጳጳሳትን ያቀፈ ልዑክ ወደ ግብጽ በመላክ በምርጫው ላይ ተሳትፈው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡