ማኅበረ ቅዱሳን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሔደ
ነሐሴ 27 ቀን 2006 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
የማኅበረ ቅዱሳን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በማኅበሩ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሀገር ውስጥና የውጭ ማእከላት፤ የወረዳ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተወካዮች፤ የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አሥፈፃሚ አባላት፤ የማኅበሩ ልዩ ልዩ ክፍል ተጠሪዎች፤ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት አካሄደ፡፡
የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፈዎች ከነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ የጸሎት፤ የመርሐ ግብር ትውውቅና ማስገንዘቢያ በጠቅላላ ጉባኤው አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ በዶክተር ዳኝነት ይመኑ ቀርቧል፡፡ የእጽበተ እግር መርሐ ግብርም ተከናውኗል፡፡
ነሐሴ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ጉባኤው በጸሎተ ወንጌል ተጀምሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክትና የማኅበሩ የሁለት ዓመታት የዕቅድ ክንውን ዘገባ በማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ ቀርቧል፡፡ በቀረበው ዘገባም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማትን በማጠናከር ረገድ፤ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር ከአህጉረ ስብከቶች ጋር እየተሠሩ ስለሚገኙ በርካታ ተግባራት ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን በማጠናከር ረገድ፤ የማኅበሩን ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ እየተሠሩና በመሠራት ላይ የሚገኙ ሥራዎች፤ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሔዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የ2005 ዓ.ም. የማኅበሩ የሒሳብ ሪፖርት በማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፤ እንዲሁም የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት በአቶ የሺዋስ ማሞ የቀረቡ ሲሆን፤ የ2004 ዓ.ም. እና የ2005 ዓ.ም. የሁለቱን ዓመታት የኦዲት ሪፖርት ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው የውጭ ኦዲተር በማስመርመር በድርጅቱ ሓላፊ የኦዲት ሪፖርቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት በማካሔድ አጽድቋቸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከ1996 ዓ.ም. በማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ጸድቆ ሲሠራበት የቆየው የማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅትና የምርጫ ሥነ ሥርዓት መመሪያ በአሁኑ ወቅት ማኅበሩ ከደረሰበት የእድገት ደረጃና የአገልግሎት ስፋት አንጻር ሊጣጣም ባለመቻሉ መመሪያውን ማሻሻል በማስፈለጉ በሥራ አመራር ጉባኤው የተሰየመው ኮሚቴ የጥናቱን ረቂቅ ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቧል፡፡ በቀረበው የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅትና የምርጫ ሥነ ሥርዓት መመሪያ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ በተሳታፊዎች ውይይት ተካሒዶበት ለማሻሻያ የሚጠቅሙ በርካታ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡ አጥኚ ኮሚቴውም የቀረቡለትን ገንቢ ሃሳቦች በማካተት ለመደበኛ ሥራ አመራር ጉባኤ እንዲያቀርብ፤ ሥራ አመራር ጉባኤውም የቀረበለትን ማሻሻያውን መርምሮ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጠቅላላ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው በሁለተኛ ቀን ውሎው ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምሥራቅ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ የተገኙ ሲሆን፤ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ያሰባሰባችሁ እግዚአብሔር ነው፤ በእናንተ ኃይል አልተሰባሰባችሁም፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር አስነስቷችኋልና በጉዟችሁ ፈተና ሊገጥማችሁ ይችላል፡፡ ፈተና ደግሞ ያለ ነው፤ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ ከሚወድህ ይልቅ የሚጠላህ ይጠቅምሃል እንዲሉ አባቶቻችን ካልተፈተኑ ክብር አይገኝም፡፡ በአገልግሎታችሁ እንደጸናችሁ ሳትበሳጩ ልትጓዙ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ማኅበሩን ይባርክ” ብለዋል፡፡
በቀጣይነትም ጠቅላላ ጉባኤው የግቢ ጉባኤያት የእድገትና ውጤታማነት መርሐ ግብር ስልታዊ አቅጣጫና እቅድ በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት /ከ2007 – 2017/፤ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ እቅድ አጋማሽ ዘመን ግምገማ በሚሉ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡
የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት እድገትና ውጤታማነት ስልታዊ አቅጣጫና እቅድ ለሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ በቀረበው ጥናት ላይ ተሳታፊዎችን በ23 ቡድን በመከፋፈል ውይይት ተደርጓል፡፡ በቡድን ውይይቱ የተነሱ በርካታ ነጥቦችን በግብአትነት በመያዝ በዋናነት በተያዙ የጥናቱ ክፍሎች ተከፋፍለዋል፡፡ በዚህም መሠረት የተነደፉት ግቦች፤ ዓላማዎች፤ ስልቶችና ተግባራት ስልታዊ እቅዱን ከማሳካት አንጻር፤ የግቢ ጉባኤያትን ስልታዊ እቅድ ከማስፈጸም አንጻር መዋቅራዊ አደረጃጀቱ ምን መምሠል እንዳለበት፤ በቀረበው ሰነድ ላይ የተጠቀሰው ገንዘብ ማግኛ ስልትና ምንጭ ተገቢ መሆኑን መመልከት፤ የግቢ ጉባኤያት ሁኔታ በአገልግሎት ክፍሎች በዋና ጉዳይነት አካቶ መሥራት በሚሉት ነጥቦች ሥር ለይቶ በመያዝ ለመደበኛ ሥራ አመራር ጉባኤ ለውሳኔ በማቅረብ፤ ሥራ አመራር ጉባኤው የቀረበለትን ሠነድ መርምሮ በማጽደቅ ተግባራዊ እንዲሆን ጠቅላላ ጉባኤው ወስኗል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ እቅድ አጋማሽ ዘመን ግምገማ በማስመልከት ከጥር 2005 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2006 ዓ.ም. የተከናወኑትን ሥራዎች ተገምግመው ሓላፊነት በወሰደው አጥኒ ቡድን ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርበዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ውይይት በማድረግ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት ቀጣይ አፈጻጸማችን ምን መምሰል እንደሚገባው ለማሳየት ቢሞከር፤ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከስትራቴጂክ እቅዱ አንጻር አስታርቆ ማስኬድ፤ የክብደት አሥራር ሥርዓቱን ግልጽ ማድረግ፤ ግምገማው ከስልታዊ እቅዱ ጋር በደንብ ቢታይ የሚሉና ሌሎችም ጠቃሚ ነጥቦች ከተካተቱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ የጥናት ቡድኑ ከጠቅላላ ጉባኤው በተሰጡት ሃሳቦች መሠረት የግምገማውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመደበኛ ሥራ አመራር ጉባኤ እንዲያቀርብ፤ ሥራ አመራር ጉባኤውም አጽድቆ በሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲያስተላልፍ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው ማጠቃለያ ላይም የዝግጅቱ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዳኝነት ይመኑ ለጉባኤው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ድርጅቶችንና በጎ አድራጊ ምእመናንን በዝርዝር በመጥቀስ በጠቅላላ ጉባኤው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ጉባኤው እሰኪጠናቀቅ ድረስ ላሳዩት አርአያነት ላለው ሥነ ምግባር የተላበሰ ታዛዥነትና ተሳትፎ አመስግነዋል፡፡
በጉባኤው ማጠቃለያም ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ለሦስት ቀናት በትዕግስት፤ በታዛዥነትና በንቁ ተሳታፊነት ለአገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን በማምንጨት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው ከ650 በላይ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡