የትንሣኤ የቅዳሴ ምንባብ 3( ሐዋ.2፥22-37)
“እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ነገር ስሙ፤ እንደምታውቁት በመካከላችሁ እግዚአብሔር በእጁ ባደረገው በከሃሊነቱ በተአምራቱና በድንቅ ሥራዎቹ እግዚአብሔር የገለጠላችሁን ሰው የናዝሬቱን ኢየሱስን ስሙ፡፡ እርሱንም በተወሰነው በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመው ዕውቀቱ እናንተ አሳልፋችሁ በኃጥኣን እጅ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁም ገደላችሁት፡፡ እግዚአብሔር ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና፡፡ ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ አለ፡- እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና፡፡ ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ፡፡ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና፡፡ የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ፡፡
“እናንተ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት ነገር እንደ ሞተ እንደ ተቀበረም፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደ አለ ገልጬ እንድነግራችሁ ትፈቅዱልኛላችሁን? ነቢይ ስለ ነበረ፥ ከአብራኩም የተገኘውን በዙፋኑ እንዲያነግሥለት እግዚአብሔር መሐላን እንደ ማለለት ስለ ዐወቀ፥ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፥ ሥጋዉም በመቃብር እንደማይቀር፥ ጥፋትንም እንደማያይ አስቀድሞ ዐውቆ ተናገረ፡፡ እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እንደማያይ አስቀድሞ ዐውቆ ተናገረ፡፡ እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮቹ ነን፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ገንዘብ አድርጎ ይህን ዛሬ የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው፡፡ ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም፥ ነገር ግን እርሱ አለ፡- ጌታ ጌታዬን አለው፡- በቀኜ ተቀመጥ፡፡ ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስክጥላቸው ድረስ፡፡ እንግዲህ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም መሢሕም እንዳደረገው በርግጥ ይወቁ፡፡” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተከፈተ፤ ጴጥሮስንና ወንድሞቹ ሐዋርያትንም፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሏቸው፡፡