የትንሣኤ የቅዳሴ ምንባብ 1 (1ቆሮ. 15፥20-41)
አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል፡፡ በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአልና፥ በሁለተኛው ሰው ትንሳኤ ሙታን ሆነ፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞት እንዲሁ በክርስቶስ ሁሉ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ሰው ሁሉ በየሥርዐቱ ይነሣል፤ በመጀመሪያ ከሙታን የተነሣ ክርስቶስ ነው፤ ከዚያ በኋላ በክርስቶስ ያመኑ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ ይነሣሉ፡፡ እግዚአብሔር አብ መንግሥቱን እጅ ባደረገ ጊዜ፥ ገዥም ሁሉ፥ ንጉሥም ሁሉ፥ ኀይልም ሁሉ በተሻረ ጊዜ፥ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል፡፡ ጠላቶቹ ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪወድቁ ድረስ ይነግሥ ዘንድ አለውና፡፡ ከዚያ በኋላ የመጨረሻው ጠላት ይሻራል፤ ይኸውም ሞት ነው፡፡ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶለታልና፥ “ሁሉ ይገዛለት” ባለ ጊዜ ግን ሁሉን ከሚያስገዛለት በቀር እንደ ሆነ የታወቀ ነው፡፡ ሁሉም በተገዛለት ጊዜ ግን እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ በሁሉ ይሆን ዘንድ፥ ያን ዕለት ወልድም ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል፡፡
ያለዚያማ ለምን ያጠምቃሉ? ሙታን እንዲነሡ አይደለምን? እንግዲህ እኛስ ሁልጊዜ መከራን ስለምን እንቀበላለን? ወንድሞቻችን ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነውና በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክህት ሁል ጊዜ እገደላለሁ፡፡ በውኑ በኤፌሶን ከአውሬ ጋር የታገልሁ ለሰው ብዬ ነውን? ምንስ ይጠቅመኛል? ሙታን የማይነሡ ከሆነ እንግዲህ እንብላ እንጠጣ፥ ነገም እንሞታለን፡፡ ወንድሞቻችን አያስቱአችሁ፤ ክፉ ነገር መልካም ጠባይን ያበላሻልና፡፡
ለጽድቅ ትጉ፤ አትሳቱ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁት ሰዎች አሉና፤ ነገር ግን እንድታፍሩ ይህን እላችኋለሁ፤ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚነሡስ በምን አካላቸው ነው? የሚል አለ፡፡ አንተ ሰነፍ! አንተ የምትዘራው እንኳን ካልፈረሰ አይበቅልም፡፡ የምትዘራውም የስንዴ ቢሆን፥ የሌላም ቢሆን የምትዘራት ቅንጣት ብቻ ናት እንጂ ይህ ኋላ የሚገኘው አገዳው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አገዳን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱ ዘርም አገዳው እየራሱ ነው፡፡ የፍጥረቱ ሁሉ አካል አንድ አይደለምና፤ የሰው አካል ሌላ ነው፤ የእንስሳም አካል ሌላ ነው፤ የወፍ አካልም ሌላ ነው፤ የዓሣ አካልም ሌላ ነው፡፡ ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን በሰማይ ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው፤ በምድርም ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው፤ የፀሐይ ክብሩ ሌላ ነው፤ የጨረቃም ክብሩ ሌላ ነው፤ የከዋክብትም ክብራቸው ሌላ ነው፤ ኮከብ ከኮከብ በክብር ይበልጣልና፡፡