፴፭ኛው የሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ተፈጸመ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

35

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጥቅምት ፯ – ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ለአራት ቀናት ሲካሔድ የቆየው ፴፭ኛው የሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ተፈጸመ፡፡

በጉባኤው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አህጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የአድባራና ገዳማት አስተዳዳዎች፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፣ እንደዚሁም ጥሪ የተደረገላቸው የአገር ውስጥና የውጪ አገር እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በፓትርያርኩ ርእሰ መንበርነት፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ መሪነት የተካሔደው ይህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ቡራኬ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ በቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ በረከት ተሰጥቷል፤ እንደዚሁም የኹሉም አህጉረ ስብከትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ ክፍሎች ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ‹‹እንዘ አልብነ ኵሉ ብነ፤ ምንም የሌለን ስንኾን ኹሉ የእኛ ነው፤›› /፪ኛ ቆሮ.፮፥፲/ የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ቃለ በረከት የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹… እኛ ካህናት ኹሌም መጨነቅ ያለብን ስለ ሀብት ሳይኾን ስለ ምእመናን ጥበቃ ነው፡፡ ምእመናን ካሉ ሀብቱ አለና፡፡ ከኀምሳ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ካሉንና በእነርሱ ላይ ተገቢ ጥበቃና አገልግሎት ካበረከትን የሚጐድልብን አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ የሰበካ ጉባኤ ዐቢይ ተልእኮም ይኸው ነው፡፡ ሰበካ ጉባኤ እኛ ካህናት ሀብታሞች መኾናችንን ያረጋገጠ ወንጌላዊ መሣሪያ እንደ ኾነ ከቶዉኑ ልንዘነጋ አይገባም …›› ብለዋል፡፡

ቃለ ቡራኬያቸውን ሲያጠቃልሉም ‹‹… ሌት ተቀን በመሥራት ምእመናንን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመጠበቅና በመንከባከብ እንደዚሁም የሚጠበቅብንን መልካም ሥነ ምግባር ኹሉ ለምእመናን በማድረግ የቤተ ክርስቲያናችንን ዕድገትና ሉዓላዊ ክብር እስከ መጨረሻው እንድናረጋግጥ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን›› ሲሉ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የመምሪያዎችንና የድርጅቶችን የ፳፻፰ ዓ.ም የሥራ ዘመን ሪፖርት ለጉባኤው ያቀረቡ ሲኾን በድምፅ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ በቅዱስ ፓትርያኩ ቡራኬ መመረቁ፣ በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጀው መጽሐፈ ቅዳሴ አገልግሎት ላይ መዋሉ፣ የ፳፬ ሰዓት የቴሌቭዥን ሥርጭት መጀመሩና በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች አብያተ ክርስቲያናት መታነጻቸው በሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ወርኃዊ የገንዘብ ድጎማና የቀለብ ድጋፍ ማድረጉ፤ በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት የአብነት ት/ቤቶችን፣ ዘመናዊ ት/ቤቶችንና የገቢ ማስገኛ ሕንጻዎችን ማስገነባቱ፤ እንደዚሁም በኢትዮጵያ በሚገኙ ፬፻፮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን በትምህርተ ወንጌል አሠልጥኖ ማስመረቁ፤ በደቡብ ኦሞ፣ በመተከልና በጋሞ ጎፋ አህጉረ ስብከት በድምሩ ዐሥራ ስምንት ሺሕ አምስት መቶ ሰባ ስምንት አዳዲስ አማንያንን አስተምሮ የሥላሴ ልጅነትን ማሰጠቱ፤ አዳዲስና ነባር የኅትመት ውጤቶችን አሳትሞ ማሠራጨቱ፤ በተጨማሪም ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ያከናወነው ተግባርና ያኘው ገቢ ከነወጪና ቀሪው በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ተገልጿል፡፡

ከአህጉረ ስብከት ሪፖርች መካከል የጋምቤላ ሀገረ ስብከት በአካባቢው ቋንቋ ወንጌልን በማስተማር የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ ያደረጋቸውን የአካባቢው ተወላጅ የኾኑ የመንግሥት ሠራተኞችን በጉባኤው እንዲሳተፉ ማድረጉ በጉባኤው ተሳታፊዎች ዘንድ የተደነቀና እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ ተግባር መኾኑ ታውቋል፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በተከፈተበት ዕለት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅራቢነት በምልአተ ጉባኤው በተመረጡ ቃለ ጉባኤ አርቃቂ አባላት አማካይነት ባለ ፳ ነጥብ የጋራ ዓቋም መግለጫ የተዘጋጀ ሲኾን በቅዱስ ሲኖዶስና በቅዱስ ፓትርያኩ የሚወጡ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን መተግበር፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መመራትና ሕግጋቱን ማስፈጸም፣ መንፈሳዊ አስተዳርን በማስፈንና ዘመናዊ ሒሳብ አያያዝን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል፣ የሕገ ወጥ ሰባክያንንና የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ መግታት፣ ለአብነት ት.ቤቶች ትኩረት መስጠት፣ ወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያንን እንዲረከብ በትምህርተ ወንጌል አእምሮውን መገንባት፣ የተማረ የሰው ኀይልን የሚያካትቱ ተቋማትን ማስፋፋት፣ ወዘተ የመሳሰሉት ተግባራት በዓቋም መግለጨው ውስጥ ከተጠቀሱ ነጥቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቅዱስነታቸውን ጨምሮ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ቃለ በረከትና ትምህርተ ወንጌል ከሰጡ በኋላ ላለፉት ሦስት ዓመታት ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ ቅዱስ ሲኖዶስን በዋና ጸሐፊነት ለመሩት ለብፁዕ አቡነ ማቴዎስና ለብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ እንደዚሁም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አህጉረ ስብከት የምስጋና የምስክር ወረቀትና ሽልማት ከቅዱስ ፓትርያርኩ ተበርክቶላቸዋል፡፡

በመጨረሻም የሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ ጸሎተ ቡራኬ ተፈጽሟል፡፡