፲፫፻፹፮ አዳዲስ አማንያን የቅድስት ሥላሴ ልጅነትን ማግኘታቸው ተገለጸ!

በደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ዳሰነች ወረዳ ፲፫፻፹፮ አዳዲስ አማንያን በማኅበረ ቅዱሳን የሐዋርያዊ ተልእኮ አስተባባሪነት የቅድስት ሥላሴ ልጅነትን ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ተጠማቂያኑ ባለፉት ወራት መሠረታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት ሲማሩ  ከነበሩ ወገኖች መካከል  መሆናቸው ታውቋል፡፡ ሥርዓተ ጥምቀታቸውም በኦሞ ብሔረ ብፁዓን አቡነ ዜና ማርቆስ ወአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ  አንድነት ገዳም ጥር ፫ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ተፈጽሟል።

በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተገኝተው ሥርዓቱን ፈጽመዋል። ቅድመ ጥምቀት ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስፋፊያ እና ሥርዓተ ጥምቀት ማስፈጸሚያ ተግባራት ሙሉ ወጪ በማኅበረ ቅዱሳን ተሸፍኗዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች  ባለፉት ወራት ባከናወናቸው የሐዋርያዊ ተልእኮ ማስፋፊያ ተግባራት ፹፭፻፵፯ አዳዲስ አማንያን ተምረውና አምነው በመጠመቅ የቅድስት ሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ  ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ይህንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለመፈጸም የሚመለከተው ሁሉ በመሳተፍ ኦርቶዶክሳዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።