ፍረጃና መዘዙ

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ሰኔ ፳፬፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ፍረጃ አንድን አካል ወይም ሰው ማንነቱን የማይገልጠው ስም፣ እውነታን ባላገናዘበ መልኩ ግላዊና ማኅበረሰባዊ በሆነ መንገድ ለሰዎች ስያሜ መስጠት፣ ከአንድ ጉዳይ ተነሥቶ ሁሉን መጥላትና ማንቋሸሽ ነው፡፡ ፍረጃውን የሚያደርጉ ሰዎችም ፍረጃውን መሠረት አድርገው በክፉ የፈረጁት ግለሰብ ወይም ቡድን አንዳች ቅጣት እንዲደርስበት ስለሚፈልጉ ለዚያ ፍረጃና ቅጣት ምስክር አድርገው የሚያቀርቡት እውነታን ሳይሆን የራሳቸውን ትርክት ነው፡፡ ፍረጃ ሰዎችን ለማግለልና ለመነጠልም እንደ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግልና በቀላሉ የማይነቀልም ሂደት/ቀጣይነት ያለው ነው፡፡ ፍረጃውን ለሚያደርጉ ሰዎችና ፍረጃቸውንም ለሚቀበሉ ሰዎች በፈረጇቸው ሰዎች ላይ ከሕግና ከሥርዓት ወጥተው የራሳቸውን ፍርድ በመስጠት ከድብደባ እስከ ግድያ የሚደርስ ወንጀል እንዲፈጽሙ ያደርጋቸዋል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መፈረጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ምእመኖቿን በአግላይነት፣ በርስት ቀሚነት፣ በማንነት ነጣቂነት፣ በፖለቲካ አራማጅነት እና በፖለቲከኞች መጠቀሚያነት ሲፈርጁ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከሦስት ወገን ይቀዳሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና አስተምህሮ የማይቀበሉ፣ የቤተ እምነታቸውንም አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥላላት የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ሁለተኛዎቹ “የብሔር” /የጎሳ/ ፖለቲካ አራማጆች የሆኑና ማናቸውንም የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ቤተ ክርስቲያንን ለማጥላላት የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ሦስተኛዎቹ ደግሞ “ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገሮች ከደረሱበት የባለጠግነት እድገት ደረጃ እንዳትደርስ እንቅፋት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት” ብለው በሐሰት ከድምዳሜ የደረሱ ናቸው፡፡ ሦስቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ቤተ ክርስቲያንን መጥላታቸውና እንድትጠፋም አጥፊዎች ለሚያነዱት የጥፋት እሳት የጥፋት ነዳጅ ማቀበላቸው ነው፡፡

የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የመነኮሳት፣ ካህናት እንዲሁም ምእመናን ግድያዎችና መፈናቀሎች፣ የቤተ ክርስቲያን ምጣኔ ሀብት ማፍሪያና ምንጮች መውደም የዚህ ፍረጃ ውጤት ሆኗል፡፡ ፖለቲከኞች ለአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ የፈለገውን የፖለቲካ ርእዮት ማራመድ እንደ መብት ቢቆጥሩም ቤተ ክርስቲያን “ሰው በሰውነቱ፣ በተፈጥሯዊ ማንነቱ ሊታይ ይገባዋል፤ ሰውን በቋንቋ፣ በጎሳ፣ በቦታና በመሳሰሉት መስፈርቶች ከፋፍሎ እርስ በርሱ እንደ አውሬ ማጫረስ ተገቢ አይደለም፡፡ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው ለሰው እንጂ ለጎሳ እና ለቋንቋ አይደለም የሚለውን ክርስቶሳዊ አስተምህሮ ሊያከብሩላት አልወደዱም፡፡ በምዕራባውያኑ የከፋፍለህ ግዛ (Divide and Rule) የተቀዳውን ሰውን በሰውነት ሳይሆን በሌሎች ተፈጥሯዊ ባልሆኑ መስፈርቶች (Social constructed bases) የሚመድበውን የቅኝ ገዥዎች ርእዮተ ዓለም ያራምዳሉ፡፡ በዚህም አቋማቸው ሊገፉም ሊነቀፉም አይፈልጉም፡፡ ይህን አቋም ማራመዳቸውም መብታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከእነርሱ እሳቤ በተቃራኒ የቆመውን ለመክሰስና በክፋት ለመፈረጅ ግን ትዕግሥት የላቸውም፡፡

በሀገሪቱ ታሪክ መሪዎች የነበሩ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ስሕተት የቤተ ክርስቲያን ስሕተት አድርጎ የመቁጠር ዝንባሌያቸውም ከፍ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት መልካም ባህሎች ማለት የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ፣ የማኅበራዊነት በጎ ዕሴቶች ምንጩ ክርስትናው መሆኑ ቢታወቅም፣ በክርስትናው የሚታየው አለባበስ፣ ዜማ፣ ሥርዓትና ወግ “ከእንቶኔ ጎሳ ነው!” የሚለውን በጥናት ያልተጻፉ ንግግር ሲናገሩ በሰፊው ሕዝብ መካከል የሚፈጠረውን አሉታዊ ተፅዕኖ አላስተዋሉትም፡፡ “የጠብ፣ የጦርነትና የመተላለቅ ምንጭ የሆነውን መለያየት የሚዘራው ሰይጣን ነው” ብለን እንዳንሰብካቸው ሰውን መለያየት የእነርሱም ፖለቲካዊ ርእዮት አስተምህሮ ስለሆነ የሰይጣን ሥራ ነው የሚለውን መስማት አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ በምትባለው ታላቅ ቤት ውስጥ እየኖርን በጎጥና “ብሔር” (ጎሳ) በቋንቋና በመሳሰሉት መከፋፈል ያመጣው ውጤት መገዳደል፣ መቆሳሰል፣ መጎዳዳት መሆኑ በግልጽ ቢታወቅም ለእነርሱ ጥቅም እስካመጣላቸው ድረስ ግድ አይሰጣቸውም፡፡

የፍረጃው መንሥኤ ውጤት፣ ያልተቋረጠ ጥቃት

በዚህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተው ጥቃት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ መነኮሳት ይገደላሉ፤ ገዳማት ጥቃት ይደርስባቸዋል፤ ከሰይጣን ሌላ ማን ያሰማራቸው? ማንነታቸው ያልታወቀላቸው ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ያንቋሽሻሉ፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርጉም “ተው” ባይ የላቸውም፡፡ መነኮሳት ታርደው፣ ምእመናን ተፈናቅለው፣ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ ድርጊቱ እንዲወገዝ ብቻ ሳይሆን እንዲነገር አይፈለግም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ “ስትታረድ ዝም በል፤ ስትፈናቀል ዝም በል” ከማለት ውጭ ትርጒም አይኖረውም፡፡ በዝቋላ ገዳም ባሉ ዓለምን ንቀው በምናኔ በሚኖሩ ገዳማውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃትም የዚህ ዘርፈ ብዙ ጥቃት አንዱ መገለጫ መሆኑንም ማስተዋል ይገባል፡፡

አራጅ መታረዱ፣ ገዳይ መገደሉ፣ አሳዳጅ መሳደዱ የማይቀር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስም ታሪክም ያስተምረናል፡፡ (ምሳ.፲፫፥፳፮) የገዳማውያኑ መገደል ፖለቲከኞቹ ትናንት የዘሩት ዛሬም እየደገሙት ያለው ቤተ ክርስቲያንን በክፋት የመፈረጁ ውጤት መሆኑን ልብ እንበል፡፡ ግድያውና ማሳደዱ ውጤት እንጂ መንሥኤ አይደለም፡፡ መንሥኤው ፍረጃው ነው፤ መንሥኤው ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተው የጥላቻ ንግግር ነው፡፡ እንኳን ዓለምን ንቀው፣ እርሱን ተስፋ አድርገው፣ ጸብአ አጋንንቱን፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ድምፀ አራዊቱን ታግሠው በገዳም በጸሎት የሚኖሩ ሰዎች ቀርቶ በዓለም በኃጢአት የሚኖሩ ሰዎች እንኳን በግፍ እንዲገደሉ የእግዚአብሔር ፈቃዱ አይደለም፡፡ ገዳማውያንን ገድሎ፣ ክርስቲያኖችን አፈናቅሎና በቀዬቸው ተወስነው እንዳይኖሩ አሳቅቆ፣ አብያተ ክርስቲያናትን አፈናቅሎ በሰላም ተደላድሎ መኖር አይቻልም፡፡ የሚፈርድ፣ ደም አፍሳሾችን የሚበቀል እግዚአብሔር በሰማይ አለና፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ይታደገን!!!