ፊደል፣ ጥንቱ እድገቱና ተግዳሮቱ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀረቡ
ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ጉባኤ ፊደል የተሰኘና በፊደል ላይ ያተኮረ ፊደል፤ ጥንቱ እድገቱና ተግዳሮቱ በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ሰብእ፣ ቋንቋዎች ጥናት፣ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት ኮሌጅ አዘጋጅነት በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች በዘርፉ ምሁራን ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም በእሸቱ ጮሌ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ ቀርበዋል፡፡
ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተጋበዙ ምሁራን በግእዝ ፊደል ዙሪያ ለበርካታ ዘመናት እንደ ችግር የሚነሡ በተለይም â¹â¹ሞክሼ ፊደላትâºâº መቀነስ ይገባል፤ አይገባም በሚል ክርክር እያስነሳ ቆይቷል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በመረጃ ላይ የተደገፈ ጥናት ማድረግ እንደሚገባ ምሁራኑ በጥናቶቻቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡ የግእዝ እያንዳንዱ ፊደል የራሱ የሆነ ትርጉም፤ ፊደሉም ሆነ ድምጹ አንዱ ከአንዱ ፊደል እንደሚለይ ነገር ግን አማርኛ የግእዝ ፊደላትን እንዳሉ መቀበሉን በጥናቶቻቸው አመላክተዋል፡፡
ለአንድ ቀን በቆየው ጉባኤም፡-
ዶ/ር አየለ በከሪ፡- የግእዝ ፊደል አመጣጥ ከታሪክ አኳያ
ዶ/ር ደርብ አዶ፡- የአማርኛ ሞክሼ ፊደላት በፍጥነት መለየት፣ የሥነ አእምሯዊ ሥነ ልሣናዊ ጥናት
ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ፡- አንዳንድ ነጥቦች ስለ መጽሐፈ ፊደል /ወ/ጊዮርጊስ በተባሉ የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ በብራና የጻፉት መጽሐፍ ላይ ተመሥርተው ያቀረቡት/
አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ፡- ሄዋን፣ ሔዋን፣ ፊደልና ትርጓሜ /በየኔታ አስረስ የኔሰው ጽሑፍ ላይ ተመስርተው ያቀረቡት/
ፕሮፌሰር ባዬ ይማም፡- ፊደል /ፊደልና ሥርዓተ ጽሕፈት፣ የሥርዓተ ጽሕፈት ዓይነት፣ ሥርዓተ ጽሕፈት ለማን. . /
አቶ ታደሰ እሱባለው፡- ተናባቢና አናባቢ ፊደሎች በእንዚራ ስብሐት መጽሐፍ /አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የጻፉት መጽሐፍ ላይ በመነሣት ያቀረቡት/
ዶ/ር ሙሉ ሰው አስራቴ፡- ለውጥና የለውጥ ሙከራ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ጽሕፈት
መ/ር ካሕሳይ ገ/እግዚአብሔር፡- ሞክሼ ቃላትና ዲቃላ ፊደላት በግእዝና በአማርኛ ቋንቋዎች ያላቸው ጠቀሜታ
ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም፡- የኢትዮጵያ ፊደል ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች
በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥናቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በቀረቡት ጥናቶች መሠረት ከታሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች በጥናት አቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም ምሁራን ከጥናቶቹ በመነሣት ሰፊ ግንዛቤ መጨበጣቸውንና በዩኒቨርስቲው ወደፊት ሊሠሩ የሚገባቸውንና በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራዎችን በማዘጋጀትና በማቅረብ በፊደል ላይ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
በጉባኤው ላይ ከአዲስ አበባ የኒቨርስቲ፤ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ፤ ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፤ እንዲሁም ከሌሎቹም ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ምሁራን ጥናቶችን በማቅረብ፤ እንዲሁም ሐሳቦችን በማቅረብ ተሳትፈዋል፡፡