ፅንሰተ ማርያም ድንግል
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ነሐሴ ሰባት ቀን ከሚዘከሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፅንሰት አንደኛው ነው፡፡ በዓሉን ለመዘከር ያህልም የእመቤታችንን የመፀነስ ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችሁ፤
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ አያቶች ቴክታ እና በጥሪቃ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለ ጠጎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መካኖች ነበሩ፡፡ ዘራቸውን ባለመተካታቸውና ሀብታቸውን የሚወርስ ልጅ ባለማግኘታቸውም ያዝኑ፣ ይተክዙ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በጥሪቃ ሚስቱ ቴክታን ጠርቶ ‹‹አንቺ መካን፤ እኔ መካን፡፡ ይህ ዅሉ ገንዘብ ለማን ይኾናል?›› አላት፡፡ ቴክታም ‹‹እግዚአብሔር ከእኔ ልጅ ባይሰጥህ ከሌላ ይሰጥህ ይኾናል፡፡ ሌላ ሚስት አግብተህ ልጅ አትወልድምን?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ በዚህ አኳኋን እያዘኑ ሲኖሩ አንድ ቀን ነጭ እንቦሳ (ጥጃ) ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ልጅ ስትደርስና ስድስተኛዪቱ እንቦሳም ጨረቃን፣ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ ራእይ አዩ፡፡
ራእያቸውን ለሕልም ተርጓሚ ሲነግሩም ‹‹የጨረቃዪቱ ትርጕም ከፍጡራን በላይ የምትኾን ልጅ እንደምታገኙ የሚያመለክት ነው፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጠልኝም፡፡ እንደ ነቢይ፣ እንደ ንጉሥ ያለ ይኾናል፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ይህን ሲሰሙ ‹‹ጊዜ ይተርጕመው ብለው›› ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ለዘር ሊያበቃቸው ፈቅዷልና መካኗ ቴክታ ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ‹ሄኤሜን› አለቻት፡፡ ትርጕሙም ‹ስእለቴን (ምኞቴን) አገኘሁ› ማለት ነው፡፡ ሄኤሜንም ለዓቅመ ሔዋን ስትደርስ ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለዱ፡፡ ለሐናም ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ እነርሱም እንደ በጥሪቃና ቴክታ መካኖች ኾኑ፡፡
በእስራኤላውያን ባህል መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይቈጠር ነበርና ሐና እና ኢያቄም ብዙ ዘለፋና ሽሙጥ ይደርስባቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ ሔዱ፡፡ የዘመኑ ሊቀ ካህናት ሮቤል መካን መኾናቸውን ያውቅ ነበርና ‹‹እናንተማ ‹ብዙ ተባዙ› ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም የነገረውን ቃል ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? እግዚአብሔር ቢጠላችሁ እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን?›› ብሎ መሥዋዕታቸውን ሳይቀበላቸው ቀረ፡፡ አንድም ከአዕሩገ እስራኤል (ከአረጋውያን እስራኤላውያን) የተወለዱ ሰዎች የሚመገቡትን ተረፈ መሥዋዕት እንዳይመገቡ ከለከላቸው፡፡ በዚህ እያዘኑ ሲመለሱ ከመንገድ ላይ ከልጆቻቸው ጋር የሚጫወቱ ርግቦችንና አብበው ያፈሩ ዕፀዋትን ሐና ተመለከተች፡፡ እርሷም ‹‹ርግቦችን በባሕርያቸው መራባት እንዲችሉ፤ ዕፀዋትንም አብበው እንዲያፈሩ የምታደርግ ጌታ እኔን ለምን ልጅ ነሳኸኝ?›› ብላ አዘነች፡፡
ከቤታቸው ሲደርሱም ‹‹እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጠን ወንድ ከኾነ ለቤተ እግዚአብሔር ምንጣፍ አንጣፊ፣ መጋረጃ ጋራጅ ኾኖ ሲያገለግል ይኑር፤ ሴት ብትኾንም መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ስታገለግል ትኑር›› ብለው ተሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ሐምሌ ፴ ቀን ኹለቱም ራእይ አዩ፡፡ ሐና ‹‹በሕልሜ ፀምር (መጋረጃ) ሲያስታጥቁህ፤ በትርህ አፍርታ ፍጥረት ዅሉ ሲመገባት አየሁ›› ብላ ያየቸውን ራእይ ለኢያቄም ነገረችው፡፡ ኢያቄምም ‹‹ጸዓዳ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፣ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ›› ብሎ ያየውን ራእይ ለሐና ነገራት፡፡ ወደ ሕልም ተርጓሚ ሔደው ትርጕሙን ሲጠይቁም ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አንተ አልፈታኸውም፤ ጊዜ ይፍታው›› ብለው ተመለሱ፡፡ በሌላ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብሎ የሕልሙን ትርጕም ትክክለኛነት ነግሯቸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ብሉይ ኪዳን (ዓመተ ዓለም፣ ዓመተ ፍዳ) ተፈጽሞ የሐዲስ ኪዳን መግባት ሊበሠር፤ ጌታችንም ሊፀነስ ፲፬ ያህል ዓመታት ሲቀሩ በፈቃደ እግዚአብሔር ነሐሴ ፯ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀንሳለች፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ በቅድስት ሐና ማኅፀን ሳለች ካደረገቻቸው ተአምራት መካከልም በርሴባ የምትባል ሴትን ዓይን ማብራቷ አንደኛው ነው፡፡ ይህቺ አንድ ዓይና ሴት (በርሴባ) ‹‹እግዚአብሔር በረድኤት ጐበኘሽ መሰለኝ፤ ጡቶችሽ ጠቁረዋል፤ ከንፈሮችሽ አረዋል›› ብላ የሐናን ማኅፀን በዳሰሰችበት እጇ ብታሻሸው ዓይኗ በርቶላታል፡፡
ይህንን አብነት አድርገውም እንደ እርሷ የሐናን ማኅፀን በመዳሰስ ብዙ ሕሙማን ከደዌያቸው ተፈውሰዋል፡፡ እንደዚሁም ሳምናስ የሚባል ልጅ በሞተ ጊዜ ሐና የአልጋውን ሸንኮር ይዛ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት ከሞት ተነሥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ አያቱ ሐና ሆይ! ሰላም ላንቺ ይኹን! ሰላምታ ይገባሻል!›› በማለት ሕልም ተርጓሚ ያልፈታውን ራእይ በመተርጐም ከቅድስት ሐና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ ከእመቤታችን ደግሞ እውነተኛው ፀሐይ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል …፤ ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን መረጠ፤ አከበረ፤ ለየ፤ ቀደሰ …፤›› (መዝ. ፵፭፥፬) በማለት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደ ተናገረው፣ አምላክን ለመውለድ የተመረጠችው ማኅደረ ማለኮት፤ የዓለሙን ቤዛ በመውለዷ ‹‹ቤዛዊተ ዓለም›› እየተባለች የምትጠራው፤ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረችው፤ የድኅነታችን ምክንያት የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን የተቋጠረችው (የተፀነሰችው) ነሐሴ ፯ ቀን ነው፡፡ ፅንሰቷም እግዚአብሔር በባረከውና ባከበረው ቅዱስ ጋብቻ በተወሰኑት ወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ሥርዓት ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በሥጋዊ ፈቃድ የተፀንሽ አይደለሽም፤ ሕጋዊ በኾነ ሥርዓት ከሐና እና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፤›› እንዳሉ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡
ስለዚህም ‹‹ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ! እውነተኛውን ምግብ፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፤›› በማለት አባ ሕርያቆስ እንዳመሰገኗት፣ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን፤ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማዳን የሚቻለውን፤ እውነተኛውን ምግበ ሥጋ ወነፍስ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ወለደችልን ‹‹እናታችን፣ እመቤታችን፣ አማላጃችን፣ የድኅነታችን ምክንያት፣ ወዘተ›› እያልን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናከብራታለን፤ እናገናታለን፤ እናመሰግናታለን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አይለየን፡፡ እናቱን በአማላጅነት፤ ራሱን በቤዛነት ለሰጠን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር፣ ምስጋና ይድረሰው፡፡
ምንጭ፡– ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፭፥፴፰፡፡