የጽዮን ምርኮ – ክፍል አንድ

ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ከምዕራፍ ፬ – ፯ ባለው ክፍል ከሚገኘው ታሪክ ውስጥ የምንረዳው ብዙ ቁም ነገር አለ፡፡ ታሪኩ የእግዚአብሔርን ኀይልና ምሕረት፣ የኀጢአትን አስከፊነት፣ የትዕቢተኞችን ውድቀት፣ የበጎዎችን በረከት፣ የደፋሮችን ጥፋት፣ ወዘተ ያስተምራል፡፡ ከዚህም በላይ ለሐዲስ ኪዳን የድኅነት ሥራ ምሳሌነት ያለው ትምህርትም ነው፡፡ ይህንን ታሪክ በአርእስት ከፋፍለን እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት (የታቦተ ጽዮን) መማረክ /፩ኛ ሳሙ. ፬፥፩-፳፪/

እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተዋጉ ጊዜ ድል ተነሱ፤ አራት ሺሕ ያህል እስራኤላውያንም ተገደሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንዲህ ሲሉ መከሩ ‹‹እኛ ዛሬ በፍልስጥኤማውያን የተመታነችው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ከእኛ ጋር አብራ ባለመውጣቷ ነው፡፡ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያንን ድል እንድንነሳ ታቦተ ጽዮን ትምጣልን፡፡›› የካህኑ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም ታቦተ ጽዮንን ይዘው መጡ፤ ታቦተ ጽዮን ወደ ሥፍራው ስትደርስም ታላቅ ደስታና ዕልልታ ተደረገ፡፡ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ይዘው ሲወጡ ድል ያደርጉ ነበርና፡፡ ነገር ግን እነርሱ እንደ ጠበቁት ሳይኾን ቀርቶ ሠላሳ ሺሕ የሚሆኑ እስራኤላውያን በጦርነቱ ተገደሉ፤ ሁለቱ የሊቀ ካህናቱ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም ሞቱ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦትም ተማረከች፡፡ ከጦርነቱ ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ከተማው ገብቶ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት እንደ ተማረከች፣ አፍኒንና ፊንሐስም እንደ ሞቱ፣ እጅግ ብዙ ኃያላነ እስራኤል በጦርነቱ እንደ ወደቁ ለካህኑ ዔሊ በነገረው ጊዜ ዔሊ በድንጋጤ ከተቀመጠበት ወንበር ወድቆ ሞተ፡፡ ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበርና የአማትዋንና የባሏን ሞት በሰማች ጊዜ ምጥ ደረሰባት፤ ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ ስሙንም ‹ኢካቦድ› ብላ ጠራችው፤ ትርጕሙም ‹‹ክብር ከእስራኤል ለቀቀ›› ማለት ነው፡፡

ከዚህ ታሪክ ብዙ ቁም ነገሮችን እንማራለን፤ አስቀድሞ እስራኤል ታቦተ ጽዮንን ይዘው የዮርዳኖስን ባሕር ከፍለው ተሻግረዋል፤ አሞናውያንን፣ ፌርዜዎናውያንን፣ ሞዓባውያንን ድል አድርገዋል፡፡ የኢያሪኮን ግንብ አፍርሰው ምድረ ርስትንም ወርሰዋል፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከፊታቸው በማስቀደም እነዚህን ታላላቅ ተአምራት ያደረጉ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን እንዴት ድል ተነሱ? የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦትስ እንዴት ተማረከች?›› የሚሉ ጥያቄዎች ከተነሡ ለታቦተ ጽዮን መማረክ፣ ለኃያላነ እስራኤል ድል መነሳት፣ ለካህኑ ዔሊ ሞት፣ እንዲሁም ለልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ በጦርነቱ መሞት ዋና ምክንያት የአፍኒንና ፊንሐስ ኃጢአት እንደዚሁም የዔሊ አለመታዘዝ ነው፡፡

የአፍኒንና ፊንሐስ ኀጢአት

፩ኛ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው መሥዋዕት ስቡ ሳይቃጠል አስቀድመው ሥጋ መብላታቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር›› ይላል /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፲፪/፡፡ እግዚአብሔርን አያውቁም ማለቱ ለአምላክነቱ የሚገባውን ክብር አይሰጡም ለማለት ነው እንጂ የሊቀ ካህን ልጆች ኾነው ስለ እግዚአብሔር ህልውና መግቦት፣ ገዥነት፣ ወዘተ አያውቁም ለማለት አይደለም፡፡ የአዋቂ አጥፊዎች እንደ ኾኑ ለመናገር ነው እንጂ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለው የስብ መሥዋዕት ሳይቀርብ አስቀድመው ጥሬ ሥጋ ሳይቀር ገና ሳይቀቀል ይወስዱ ነበር፡፡ እንኳን ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ሥጋ መመገብ ከድካም ውጤት ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን አለመስጠት በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቃል፡፡ ዐሥራት ከገንዘብ፤ በኵራት ከእንስሳት፤ ቀዳምያት ከአዝዕርት ከፍራፍሬ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ስጦታ ነው፤ ይህንን ማድረግም ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡

ስቡ ሳይቃጠል፣ መሥዋዕቱም ሳያርግ ለሆዳቸው ያደሩ አፍኒንና ፊንሐስ ሥጋ በመብላታቸው ምክንያት ‹‹ምናምንቴዎች›› እንደ ተባሉ፣ ዛሬም እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ልማት የሚናፍቁ ደጋግ ክርስቲያኖች የሚያስገቡትን ዐሥራት፣ በኵራት፣ ቀዳምያት በመዝረፍ ቤተ ክርስቲያንን የሚበድሉ ብዙ ምናምንቴዎች አይታጡም፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ ሲስገበገቡለት የነበረው ሥጋ አላዳናቸውም፡፡ እነርሱ ያለ ቀባሪ በጠላት ሰይፍ ተመተው እንደ ወደቁ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን የሚዘርፉ፣ ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ ዅሉ ሥጋቸው በደዌ፣ በመቅሠፍት፤ ነፍሳቸውም በሲዖል መቀጣቱ አይቀርም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት እኛ እንድንማርባቸው እንድንገሠፅባቸው ነውና ከዚህ ታሪክ ትምህርት ወስደን ሰማያዊውን ጸጋ በምድራዊው ጥቅም ለውጠን እንዳንጐዳ ሰውና እግዚአብሔርን ከሚያስቀይም መጥፎ ድርጊት ለመመለስ ዛሬውኑ መወሰን ይኖርብናል፡፡ ‹‹ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ /ሮሜ. ፰፥፮/፡፡

፪ኛ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር መሰሰናቸው

ዝሙት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተጠላ፣ ሰውነትን ዅሉ የሚያረክስ ኃጢአት ነው፡፡ ሌሎቹ ኃጣውእ በአፍኣ ይሠራሉ፤ ዝሙት ግን በገዛ ሥጋ ላይ ስለሚሠራ ሰውነትን ዅሉ ያሳድፋል፡፡ ‹‹ከዝሙት ሽሹ፤ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ዅሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙት የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአት ይሠራል፤›› /፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፰/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ይሰስኑ ነበር፡፡ የእነዚህን ሰዎች ኃጢአት እጅግ የከፋ የሚያደርገው በመገናኛው ድንኳኑ ውስጥ ዝሙት መፈጸማቸው ነው /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፪/፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም ቅዱስ ነውና በቅድስና እንድናገለግለው ይፈልጋል፡፡ ‹‹ኩኑ ቅዱሳነ ወቀድሱ ርእሰክሙ እስመ ቅዱስ አነ እግዚአብሔር አምላክክሙ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ እንደ ኾንኩ እናንተም ቅዱሳን ኹኑ፤ ሰውነታችሁንም ቀድሱ›› /ዘሌ. ፲፩፥፵፬/ በማለት በሊቀ ነቢያቱ ቅዱስ ሙሴ አንደበት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ውጭ በማንኛውም ነገር መመካት ወይም መታመን ዝሙት ነው፡፡ ሰው በወገን፣ በሥልጣን፣ በሀብት ወይም በዕውቀት እየታበየ የሚያቀርበው መባዕ፣ የሚጸልየው ጸሎት በአጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎት ከንቱ ነው፡፡ መጀመሪያ እነዚህን ዝሙታት ማስወገድ አለበት፡፡ በእውነት የእኛስ አገልግሎታችን በንጽሕና በቅድስና የታጀበ ነውን? ብዙ ንጹሐን ቀሳውስትና መነኮሳት እንደዚሁም ዲያቆናት እንዳሉ ዅሉ ሥጋቸውን በዝሙት እያሳደፉ በድፍረት ማገልገል አለብኝ በማለት ማኅበረ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚበጠብጡ እንዳሉ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በአፍኒንና ፊንሐስ የዝሙት ኀጢአት ምክንያት በአስራኤል ላይ ያደረሰው ቍጣና መቅሠፍት ዛሬም በረከሰ ሰውነታቸው ቤተ መቅደሱን በሚደፋፈሩ ሰዎች ምክንያት የምናጣው በረከትና የሚመጣው መቅሠፍት ቀላል አይኾንም፡፡

እስራኤል ከግብጽ ወጥተው ወደ ምድረ ርስት ሲጓዙ የአሕዛብን መንደሮች ያቋርጡ ነበር፡፡ በሰጢን መንደር በሰፈሩበት ጊዜ የእስራኤል ጐበዛዝት /ጐልማሶች/ በአሕዛብ ቈነጃጅት በዝሙት ተነደፉ፡፡ ከእስራኤል አንዱ ከምድያማዊቷ ሴት ጋር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ተኛ፡፡ የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለእግዚአብሔር ሕግ በመቅናት ሁለቱንም በአንድ ጦር ሆዳቸውን ወግቶ ገደላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጣው ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ቆመ፡፡ ስለዚህም ‹‹ለእርሱ፣ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም ክህነት ቃል ኪዳን ይኾንለታል፤›› በማለት እግዚአብሔር አምላክ ለፊንሐስ ወልደ አልዓዛር ቃል ኪዳን እንደ ሰጠው በመጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል /ዘኊ. ፳፭፥፲፫/፡፡

ዛሬም በዝሙት ሰውነታቸውን እያረከሱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ካላገለገልን የሚሉትን እንደ አልዓዛር ልጅ እንደ ፊንሐስ በመንፈሳዊ ቅንዓት ተነሳሥተን ልንገሥፀቸው ይገባል፡፡ ራሳቸውን ያረከሱ አገልጋዮች በድፍረት ቤተ መቅደስ ሲገቡ ርኵሰታቸውን እያወቀ ዝም ብሎ የሚያይ ምእመን መልካም ሥራ መሥራት መልካም እንደ ኾነ እያወቀ ባለመሥራቱ ፍርድ ያገኘዋል፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው፡፡ ወገኖቻችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የኾነውን ሰውነታቸውን በዝሙት፣ በዘረኝነት፣ በትዕቢት፣ በስርቆት፣ በአጠቃላይ በኃጢአት ሲያረክሱ እያየን ዝም አንበል፡፡ ቢሰማን ያን ሰው እንጠቅመዋለን፤ ባይሰማንና በክፉ ሥራው ቢጸና ግን በራሱ ላይ የእሳት ፍሕም ያከማቻል /ምሳ. ፳፭፥፳፪/፡፡

፫ኛ ሌሊት ሲነድ የሚያድረውን እሳት ማጥፋታቸው

አፍኒንና ፊንሐስ ሌሊት በደብተራ ኦሪት ሲነድ የሚያድረውን ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የእሳት ቍርባን ያጠፉ ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፰/፡፡ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ማስቀረት ክብር ይግባውና ባለቤቱን ማቃለል ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የሚያቃልለውን እንደሚያዋርድ፣ የሚያከብረውን እንደሚያከብር ራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹ያከበሩኝን አከብራለሁና፤ የናቁኝም ይናቃሉና፤›› /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፴/፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ የነበረውን ዐሥራት፣ በኵራት፣ ቀዳምያት እኛስ እያቀረብን ነውን?

ይቆየን፡፡