ፀአተ ክረምት (ዘመነ ክረምት የመጨረሻ ክፍል)
መስከረም ፳፭ ቀን ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ከአሁን በፊት ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ትምህርት በአምስት ተከታታይ ክፍል ስናቀርብላችሁ ቆይተናል፡፡ ለመከለስ ያህል ‹‹ክረምት›› የሚለው ቃል ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት መኾኑን፣ ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ ክረምት እንደሚባል፣ ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን እንደ ኾነ፤ ይህ ዘመነ ክረምትም በሰባት ንዑሳን ክፍሎች እንደሚመደብ፣ ይኸውም፡-
፩ኛ ከሰኔ ፳፭ እስከ ሐምሌ ፲፱ ቀን ያለው ጊዜ ዘርዕ፣ ደመና፤
፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤
፫ኛ ከነሐሴ ፲- ፳፰ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤
፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭/፮ ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዐልት፤
፭ኛ ከመስከረም ፩-፰ ቀን ዮሐንስ፤
፮ኛ ከመስከረም ፱-፲፭ ቀን ፍሬ እንደሚባል ከ ‹‹በአተ ክረምት›› ጀምሮ እስከ ‹‹ዘመነ ፍሬ›› ድረስ ባሉት የዘመነ ክረምት ጽሑፎቻችን ተመልክተናል፡፡
‹‹ዘመነ ፍሬ›› በሚል ርእስ ባቀረብነው በክፍል አምስት ዝግጅታችንም ከመስከረም ፱ – ፲፭ ቀን ያለው ክፍለ ክረምት ‹ፍሬ› እንደሚባልና ይኸውም ልዩ ልዩ አዝርዕት በቅለው፣ አድገው፣ አብበው ለፍሬ የሚደርሱበት፤ የሰው ልጅ፣ እንስሳትና አራዊትም ጭምር የዕፀዋቱን ፍሬ (እሸት) የሚመገቡበት ወቅት እንደኾነ፤ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቀርቡ ምንባባትና ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር እንደሚዳስሱ በማስገንዘብ የምእመናንን ሕይወት ከዕፀዋትና ከፍሬ ጋር በማመሳሰል ትምህርት ማቅረባችን የሚታዎስ ነው፡፡ በዛሬው የ‹‹ፀአተ ክረምት›› ዝግጅታችንም የመጨረሻውን የክረምት ክፍለ ጊዜ የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፯ኛው የክረምት ክፍለ ጊዜ መስቀል በመባል የሚታወቅ ሲኾን ይኸውም ፀአተ ክረምትና በአተ መጸው የሚሰበክበት፣ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርቡ ትምህርቶች ነገረ መስቀሉን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ማለትም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ መሞቱ፣ በሞቱም ዓለምን ስለ ማዳኑ፣ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስላፈሰሰበት ዕፀ መስቅሉ የተቀደሰ ስለ መኾኑ፣ በምእመናን ዘንድም ትልቅ ትርጕም ያለው ስለ መኾኑ ከሌሎች ጊዜያት በላይ በስፋት የሚነገረውና ትምህርት የሚሰጠው በዚህ ወቅት ነው፡፡
ከዚሁ ኹሉ ጋርም በአይሁድ ቅናት በጎልጎታ ለ፫፻ ዓመታት ያህል ተቀብሮ የቆየው የጌታችን ዕፀ መስቀልን ለማውጣት በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት ቍፋሮ መጀመሩ፣ መስቀሉ ከወጣ በኋላም በዐፄ ዳዊትና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ ጥረት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡ የሚዘከረው በእነዚህ ዐሥር የፀአተ ክረምት ዕለታት ውስጥ ነው፡፡ ኹላችንም ሕዝበ ክርስቲያን ይህንን የመስቀሉን ነገር በልቡናችን ይዘን በክርስትናችን ምክንያት የሚገጥመንን ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና በትዕግሥት ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡
‹‹ፀአተ ክረምት›› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረት ‹‹የክረምት መውጣት›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ይህም ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ የፀአተ ክረምት መጨረሻ የሚኾነውም መስከረም ፳፭ ቀን ነው፡፡ የክረምት መውጣት ሲባል ለዘመነ ክረምት የተሰጠው ጊዜ በዘመነ መጸው መተካቱን ለማመልከት እንጂ ክረምት ተመልሶ አይመጣም ለማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት እስከሚያበቃበት እስከ ኅልፈተ ዓለም ድረስ የወቅቶች መፈራረቅም አብሮ ይቀጥላል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን የወቅቶች መፈራረቅ ለመግለጽ ነው ‹‹መግባት፣ መውጣት›› እያሉ በክፍል የሚያስቀምጧቸው፡፡
አንድ የጊዜ ክፍል (ወቅት) ሲያልፍ ሌላው ይተካል፡፡ ‹‹ሲሞት ሲተካ፣ ሲፈጭ ሲቦካ›› እንደሚባለው የሰው ልጅ ሕይወትም እንደዚሁ ነው፡፡ አንደኛው ሲሞት ሌላኛው ይወለዳል፤ አንደኛው ሲወለድ ሌላኛው ይሞታል፡፡ ወቅቶች የጊዜ ዑደት እንደ መኾናቸው ለሰው ልጅ ምቾት እንጂ ለራሳቸው ጥቅም የተዘጋጁ ሕያዋን ፍጥረታት አይደሉም፡፡ በመኾኑም ራሳቸውን እየደጋገሙ ይመላለሳሉ፤ የሰው ልጅ ግን አምሳሉን ይተካል እንጂ ራሱ ተመልሶ አይመጣም፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ እንዳናፍር ዳግም በማናገኛት በዚህች ምድራዊ ሕይወታችን የማያልፍ ክርስቲያናዊ ምግባር ሠርተን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ ከሞት በኋላ ዘለዓለማዊ ፍርድ እንጂ ንስሐ የለምና፡፡
በአጠቃላይ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹እነሆ ክረምት ዐለፈ፤ ዝናቡም ዐልፎ ሔደ፡፡ አበባ በምድር ላይ ታየ፤ የመከርም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ፤ ወይኖችም አበቡ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ …›› /መኃ.፪፥፲፩-፲፫/ በማለት እንደ ተናገረው አሁን የክረምቱ ጊዜ አብቅቶ ሌላ ወቅት ዘመነ መጸው ተተክቷል፡፡ መጭው ጊዜ የተስፋ፣ የንስሐና የጽድቅ ወቅት እንዲኾንልን እግዚአብሔርን ከፊት ለፊታችን ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ እርሱ ከቀደመ መሰናክሎቹን ለማለፍ፣ ፈተናዎችንም ለመወጣት ምቹ ኹኔታዎችን እናገኛለንና፡፡ ክረምቱ አልፎ መጸው ሲተካ ምድር ባገኘችው ዝናም አማካይነት የበቀሉ ዕፀዋት በአበባና በፍሬ ይደምቃሉ፡፡ እንደዚሁ ኹሉ ምእመናንም በተማርነው ቃለ እግዚአብሔር ለውጥ በማምጣት እንደ ዕፀዋት በመንፈሳዊ ሕይወታችን አፍርተን ክርስቲያናዊ ፍሬ ማስገኘት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ፍሬያችን ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንችላለንና፡፡
ይህ መንፈሳዊ ዓላማችን ይሳካልን ዘንድም እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡ እንደዚህ እያልን፤ ‹‹ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም፤ ዘአርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም፤ አፈወ ሃይማኖት ነዓልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም፤ አትግሀነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም፤ ለጽብስት ንህብ ወነአስ ቃህም፡፡›› ትርጕሙም፡- ክረምት ካለፈ፣ ዝናምም ወደ ቦታው ከተመለሰ በኋላ የዱር አበቦችን ያሳየህ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! የሃይማኖት ሽቱን እናስገኝና የሚጣፍጥ የምግባር ፍሬን እናፈራ ዘንድ ተወዳጅ እንደ ኾነው የታታሪዋ ንብና የብልሃተኛዋ ገብረ ጕንዳን ትጋት እኛንም ለምስጋናህ አትጋን›› ማለት ነው /መጽሐፈ ስንክሳር፣ የመስከረም ፳፭ ቀን አርኬ/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡