“ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ”  (ኢዩ.፩፥፲፬)

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው

የካቲት ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

እንኳን ለታላቁ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን! አምላካችን ጾማችንን በሰላም አስጀምሮ በሰላም ያስፈጽመን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን!

ጾም ከሚበላ፣ ከሚጠጣ መቆጠብ፣ መከልከል፣ ከጥሉላት ምግቦች መታቀብ፣ ሕዋሳትንም ከክፉ ነገር መከልከል፣ ዐይን ክፉ ከማየት፣ ጆሮ ክፋ ከመስማት፣ አንደበት ክፋ ከመናገር፣ ኅሊና ክፋ ከማሰብ መከልከል፣ ራስንና ስሜትን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ነው።

ርቱዓ ሃይማኖት እንዲህ ይላል “ከጾም የሥጋ ንጽሕና፣ የነፍስ ቅድስናና ድንግልና ይወለዳሉ።  ይህች ጾምም የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ መርከብ ናት፤ በውስጧ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ይኖራሉ። ሩቅ ሀገር የሚሄዱት ያለ መርከብ በባሕር ላይ ፈጽሞ መሄድ እንዳይቻላቸው ሁሉ እንዲሁ ስለጽድቅ የሚጓዙትም በመንፈሳዊት ሐመር ካልታሳፈሩ አንዲት እርምጃ ስንኳን መራመድ አይቻላቸውም።” (ርቱዓ ሃይማኖት ገጽ ፺፩-፺፪)

ጾም ወደ መንፈሳዊት ሀገር መሸጋገርያ ድልድይ ነው።  ያች መንፈሳዊት ሀገር ደግሞ መግቢያ በሯ እጅግ የጠበበች፣ ብዙዎች ሊገቡባት የማይችሉ፣ ለተመረጡት እና መመረጣቸውን ለጠበቁ ሁሉ የምትሰጣቸው፣ በጽድቅና በመልካም ምግባር የጸኑ፣ በጾም እና በጸሎት ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው ያስገዙ፣ ሐሳባቸው እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የሆነላቸው ብቻ የሚወርሷት  የደስታ እና የምስጋና ሀገር ናት። ጌታችን በጠባቡ በር ግቡ ሲለን ይህን ለመፈጸም ቅጥነተ ኅሊና ያስፈልጋል፡፡ ሐሳባችን አእምሯችን ከወፈረ በጠባቡ መንገድ ማለፍ አይችልምና። ቅጥነተ ኅሊና እንዲኖረን ታድያ ጾም ትልቅ ድርሻ አለው።

ጾም ማለት ሰው ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው፣ ምስጋናቸው ዕረፍታቸው የሆኑትን መላእክትን የሚመስልበት፣ የነፍስን ቁስል የምታድን፣ የሥጋን ፍላጎት የምታስወግድ፣ የትሕትና መምህር፣ የጸሎት እናት፣ የእንባ መፍለቂያ፣ የበጎ ሥራ ሁሉ መሠረት፣ የሥራ ሁሉ መጀመርያ ናት። (ማቴ.፬፥፩-፬)  “እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ መቅድመ ኩሉ ግብር ሰናይት፤ ጾም ማለት የጸሎት እናት የትሕትና እኅት፣ የእንባ ምንጭ፣የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት ” እንዲል ፈልፈለ ማሕሌት ቅዱስ ያሬድ። ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ የምናስገዛበት ነው። ክርስቲያኖች እውነተኛ ደስታን ከፈለጋችሁ ሥራችሁን በጾም ጀምሩ፤ ጾምን ቀድሱ፤ ጉባዔውን ዐውጁ፤ በጾማችሁ ሁሉንም የስሜት ህዋሳት አሳትፉት።

መጾም ለምን ይጠቅማል?

የጾም ጥቅሟ ብዙ ነው፤ “እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው” ተብሎ ተዘርዝሮ የሚያልቅም አይደለም፡፡ “የአንጾኪያ ቤተ ክርስትያን ነቢያትና መምህራን ሳውልንና በርናባስን ለመሾም ይጾሙና ይጸልዩ ነበር። ይህን ስላደረጉ መንፈስ ቅዱስ ተናገራቸው” እንዲል፡፡ (የሐዋ.፲፫፥፩-፬) ስለዚህ ጾም ይህን ያህል ታላቅ ኀይል ያላት ናት በተለይ ደግሞ ከጸሎት ጋር ስትሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምነጋገርባት ነች። ስንጾምም የሚያበረታንን እንጅ የሚያደክመንን እንጀራ አንብላ፤ ሰላም የሚሰጠንን እንጅ ሰላም የሚነሣንን እንጀራ አናዘውትር፤ ለነፍሳችንና ለሥጋችን የሚጠቅም እንጅ በሁለቱም ወገን ደዌ የሚያመጣብንን እንጀራ አንብላ፤ ይኸውም በጾም ወቅት የክርስቶስን ሥጋና ደም መቀበልን ማዘውተር ነው፤ ልባችሁ በፀጋ ቢጸና መልካም ነው እንጅ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩ አልተጠቀሙምና እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ። (ዕብ ፲፫፥፱)

ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው መግቢያ ላይ “ኩኑ እንከ ከመ ብእሲ ጠቢብ ዘይጸውም ወዘይጼሊ ወያስተሠሪ ኃጢአቱ ሑሩ በጽድቅ ትርከቡ ሠናየ፤ እንደ ሚጾም፣ እንደ ሚጸልይ፣ ኃጢአቱን እንደ ስለ ኃጢአቱ ሥርየትን ለማግኘት እንደሚደክም ሰው ጥበበኛ ሁኑ መልካሙንም እንድታገኙ በእውነት ተመላለሱ” በማለት ጥበበኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ይነግረናል። ከእኔ በላይ ጠቢብ፣ የጥበብ ሰዎች እያላችሁ እራሳችሁን የምትጠሩ ሰዎች በእውነት ጾም ትጾማላችሁን? ጸሎትስ ታደርጋላችሁን? እንግዲያውስ የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው  እንዲል  ጠቢባን ሳትሆኑ ሞኞቾ ናችሁ። (፩ቆሮ.፫፥፲፱)

ጌታችን የጾመው ፵ ቀን ሆኖ ሳለ ለምን እኛ ፶፭ ቀን እንጾማለን በሚለው ጥያቄ አንድ ሐሳብ እናንሳና ወደ ዐቢይ ጾም የመጀመርያ ሳምንት ዘወረደ እንለፍ። ጌታችን የጾመው ከዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ቅድስት ከሚለው ጀምሮ የሚታሰብ ሲሆን ይህ ሳምንት ግን የንጉሥ ጾም አጃቢ፣ አምላካችን የጾመውን ጾም ለመጾም እንድንበቃ በጾም በጸሎት የምንለምንበት፣ የታላቁ ጾም መቀበያ ነው። ንጉሥ ከእልፍኙ ሲወጣ ከፊትም ከኋላም እንዲታጀብ የንጉሣችን የክርስቶስ ጾምም እንዲሁ ታጅቦ የሚጾም ጠላትን ድል የምናደርግበት ጾም ነው። አንድም “ጾመ ሕርቃል” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የሮም ንጉሥ ሕርቃል በነገሠበት ዘመን የክርስቶስ መስቀል ዳግመኛ ወደ ፋርስ ወርዶ ጠፍቶባቸው ስለነበር ንጉሡ ሕርቃል መስቀሉ እንዲያስመልስላቸው እግዚአብሔር ኃይል እንዲሆነው የጾሙት ጾም ነው። “መስቀል ተረክበ እምዘ ተኀብዐ ወገብረ መድምመ በኢየሩሳሌም ቅድመ ወበፋርስ ዳግመ፤ መስቀል ከጠፋበት ተገኘ፤ መጀመሪያ በኢየሩሳሌም ድንቅ ነገር አደረገ፤ ዳግመኛም በፋርስ” እንዲል፡፡ (ስንክሳር መጋቢት ፲)

           ዘወረደ

ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፡፡ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ.፫፥፲፫)

የዐቢይ ጾም የመጀመርያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡ ምክንያቱም የድኅነት ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፀነሠ፤ ተወለደ፤ ተጠመቀ፤ ጾመ፤ አስተማረ ወዘተ…. ከመባሉ በፊት ወረደ ይቀድማልና ነው፡፡ ኃይለ ቃሉም የተወሰደው (ዮሐ.፫፥፲፫) “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ዘወረደ እም ላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘያሐዩ በቃሉ፤…ከሰማያት የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤ በቃሉ የሚያድን የሁሉ ጌታ እርሱን አላወቁትምና” እንዳለ  ለድኅነት ለመድኃኒት የመጣውን የሁሉ ጌታ አይሁድ እንደ ሰቀሉት ይናገራል። (ጾመ ደጓ ዘወረደ)

የቃሉ ትርጉም

ከሰማይ ከወረደው በቀር ሲል ጌትነቱን፣ የባሕርይ አምላክነቱን፣ ልዕልናውን ሲገልጽልን ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት ለተልእኮ ከመኖሪያቸው ከሰማይ ወርደዋል፤ ወደ ሰማይም ወጥተዋል፡፡ የእርሱን ግን ብቸኛና ልዩ መሆኑ ለማስረዳት “… ከወረደው በቀር” በማለት ገለጸው፡፡ ይኸውም በነቢይ ”አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ”  ተብሎ የተነገረለት ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ የተወለደ ድኅረ ዓለም ለድኅነት ከሰማይ የወረደ ከእመቤታችን የተወለደ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የአብ አንድያ ልጅ መሆኑን ሲናገር ነው፡፡ (ሚኪ.፭፥፫) ‘ከወረደውም በቀር ወደ ሰማይ (ወደ አብ ቀኝ) የወጣ የለም” ሲል “አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ የሆነ ከእርሱ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ወይም በአብ ቀኝ (ዕሪና) የተቀመጠ የለም” በማለት አምላክነቱን አስረድቷል፡፡ ሥግው ቃል  ክርስቶስ በምድር እያስተማረ ሳለ በሕልውና ከእግዚአብሔር አብ እንዳልተለየ ሲያስተምራቸው “….እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” አለ፡፡

የወረደው እርሱ ማነው?

እግዚአብሔርን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ፣ በሥልጣን፣ በመለኮት፣ በአገዛዝ የሚተካከለው ነው፡፡ (ዮሐ፲፥፴ ፲፬፥፲-፲፩ ፲፯፥፲ ፲፮፥፲፭)

የእግዚአብሔር አብ ልጅ እግዚአብሔር ወልድ ነው፡፡ (መዝ.፻፱፥፩፣ዘካ.፪፥፰-፱)

የእግዚአብሔር አብ እና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ ከእግዚአብሔር የተለየ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ሕልው ሆኖ የሚኖር ነው እንጂ፡፡ እንዲሁ ሁሉ የእግዚአብሔር ቃልም ከእግዚአብሔር የተለየ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ እግዚአብሔር ነው እንጂ፡፡ (ዮሐ.፩፥፩-፲፬ ፩ኛ ዮሐ፭፥፯)

በፍጥረታት፣ በሕይወትና በሞት ሁሉ ላይ መለኰታዊ ሥልጣን ያለው፣ የሚሰገድለትና ጸሎትን የሚቀበል፣ በሁሉ ቦታ የሚገኝ፣ በዘመን የማይወሰን፣ ቀዳማዊና ደኃራዊ፣ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር፣ አዳኝና ነጻ አውጪ፣ መጋቤ ዓለማት፣ አኃዜ ዓለማት፣ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡

እንዴት ወረደ?

በሕልውና ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ እግዚአብሔር ወልድ በማኀፀነ ድንግል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ ተወለደ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያየዋል” እንዳለ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት ተወስኖ ለፍጥረቱ ተገለጸ፡፡(ኢሳ.፵፥፩‐፭)  በዚያ ዘመን የነበሩትን ይልቁንም አምነው የተከተሉትን ከዘመኑ ደርሰው እርሱን በማየታቸው ዕድለኞች እንደሆኑ እንዲህ በማለት ቅዱስ ማቴዎስ ይናገራል፤  “የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፣ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸሁ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም፡፡” (ማቴ.፲፫፥፲፮‐፲፯)

ለምን ወረደ?

እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማየት የወረደው የድኅነት ሥራ ለመፈጸም ነው፡፡ ሕግ በማፍረስ ከገነት የወጣውንና ከጸጋ እግዚአብሔር የተለየውን ሰው ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ለመባል ሊወለድ ወረደ። (ገላ.፬፥፩-፯) የእዳ ደብዳቤያችንን ሊቀድልን፣ የጥል ግድግዳችን ሊያፈርስ ወልደ እግዚአብሔር ወረደ፤ ተወለደ (ቆላ.፪፥፲፫፣፩፣፳)

ታላቁ የቤተ ክርሰትያናችን መምህር ቅዱስ አትናቴዎስ የአምላክን ወደዚህ ዓለም መውረድና መምጣት እንዲህ ሲል በማስተዋልና በአድናቆት ገልጾታል፤ “እርሱ አምላካችን የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ በመካከላችን በመግኘቱ ጥሩ የትሕትና መምህር ሆነን፡፡ እርሱ በባሕርይው አምላክ ሆኖ ሳለ እርሱ ራሱ ወደ እኛ መጣ፡፡ እንደ እኛም እየበላ እየጠጣ የመጣበትን ዓላማ አስተማረን (ነገረን)፡፡ ዳሩ ግን በእርሱ ፈንታ እኛ ወደ እርሱ እንድንሔድና ይቅርታ እንጠይቅ ዘንድ ብንገደድ ኖሮ ከኛ የተፈጥሮ ድክመት የተነሣ እንዴት እንችል ነበር? ስለዚህ ጌታችንም ኃጢአተኛ፣ ጉስቋላ፣ ደካማ ወደ ሆነው ወደ እኛ መጣ፤ ሥጋችንንም ተዋሕዶ፤ በመካከላችንም ተገኝቶ በሚረዳን፣ በሚገባን ቋንቋ ፍቅሩንም አሳየን፤ እርሱነቱንም እንድናደንቀው ባሕርይውንም እንድንረዳ አደረገን፤ ክብርንም ተጎናጸፈን ወደ መንግሥቱ እንድንገባ ገለጸልን፡፡”

በመጨረሻም ጾምን እንጹም፤ ባልእንጀራችንን እንውደድ፤ እርስ በእርሳችን እንዋደድ “ተፋቀሩ በበይናቲክሙ፤ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት አምላካችን አዝዞናልና። (ዮሐ.፲፫፥፴፬፣ጾመ ድጓ ዘዘወረደ)

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።