ጾመ ፍልሰታ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ አይሁድ ‹‹እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት›› ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡
ከዚህ ላይ ‹‹ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ ገቡ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ በመሠረቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት ተለይተው እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡ በመኾኑም እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፭ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋን ‹‹ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ›› ያሰኘውም ይህ ምሥጢር ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ ‹‹ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ›› እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት ‹‹ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?›› አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡
በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?›› ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ሥጋዋን ይሰጣቸው (ያሳያቸው) ዘንድ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል (ነገረ ማርያም፤ ትርጓሜ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም)፡፡
ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹ፍልሰት› የሚለው ቃል ‹‹ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ ‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን) የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡
በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡
በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ዅላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡
ስለኾነም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ መብት እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና (ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡