ጾመ ነነዌ
ጥር፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ቸር፣ መሐሪና ይቅር ባይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር የነነዌ ሕዝብ በንስሓ፣ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ካልተመለሱ ነነዌ እንደምትጠፋ እንዲያስተምርና እንዲያስጠነቀቅ ሲያዘው ነቢዮ ዮናስ ግን በቸርነቱ ሲምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እንደሚባል አስቦ መሸሽን መረጠ፡፡ ‹‹ተነሥና ወደ ነነዌ ሀገር ግባ፤ በድለውኛልና ነነዌ በሦስት ቀን ትጠፋለች ብለህ ስበክ›› አለው። ዮናስ ግን ‹‹የአንተ ምሕረት እጅግ የበዛ ሲሆን ትጠፋለች ብዬ ተናግሬ እሳት ከሰማይ ሳይወርድ ቢቀር ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን?›› አለና ሊሸሽ መንገድ ጀመረ። (ዮናስ ፩፥፩-፫)
አምላክም የየዋሁን የዮናስን ልብ ያውቃልና በድንቅ ጥበቡ የጉዞውን አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ነነዌ ምድር ወሰደው፡፡ (ዮናስ ፩፥፬-፲፯) ዮናስም ነነዌ መሬት ላይ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረዳ፤ የነነዌ ሰዎችንም ‹‹ንስሐ ግቡ›› እያለ ሰበከ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ሆኖ ከላይ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል (ትንቢተ ዮናስ)፡፡
ከዚህ በኋላ የተጻፈው ታሪክ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፤ እርሱም ተቈጣ። ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና ‹‹አቤቱ፥ እለምንሃለሁ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽም፣ ምሕረትህም የበዛ፣ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር፡፡ አሁንም አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ›› አለው። እግዚአብሔርም ‹‹በውኑ ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን?›› አለ።
ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፤ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፤ ከተማይቱንም የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፤ ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው። በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፤ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት፡፡ ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ፤ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ሞትን ፈለገና ‹‹ከሕይወት ሞት›› ይሻለኛል አለ። እግዚአብሔርም ዮናስን ‹‹በውኑ ስለዚህች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን?›› አለው። እርሱም ‹‹እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል›› አለ። እግዚአብሔርም ‹‹አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፣ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፣ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?›› አለው፡፡ (ዮናስ ፬፥፩-፲፩)
ምሕረቱ የበዛው አምላካችን የነነዌ ሰዎችን ይቅር እንዳላቸው ሁሉ እኛንም ጸሎታችንን ሰምቶ፣ ልመናችንን ተቀብሎና ጾማችንን አስቦ ምሕረትን ያደርግልን ዘንድ ከክፋት ርቀን፣ ከቂም በቀል ከጥላቻ ነጽተን፣ በበጎነትና በመልካም ምግባር ጾሙን እንጹም!
አምላካችን እግዚአብሔር ምሕረትን ያድርግልን፤ አሜን!!!
