መ ሰብአ ነነዌ

ርእሰ ደብር ብርሃኑ አካል

‹‹ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም›› የሦስት ቀን ጾም የጾሙት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማዋም (ነነዌ) በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትኾን መሥራቿም ናምሩድ ነው (ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪)፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የሆነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶ ነበር (ዮናስ ፬፥፲፩)፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል ዮናስ የስሙ ትርጓሜ ርግብ የሆነ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይን ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሕዝብ ላከው (ሉቃ.፲፩፥፴)፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፤ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ በዚያን ጊዜ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢትን ተናገረ (፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩)፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል (፩ኛነገ.፲፯፥፲፱)፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ሆድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል (ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪)፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ‹‹ሔደህ በነነዌ ላይ ስበክ›› ባለው ጊዜ ነቢዩ ዮናስ ‹‹አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ›› ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔርም ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ ‹‹ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ›› ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይሆንም›› አሉ፡፡ ወደ ባሕሩ ለመጣል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜም ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አደረሰው፡፡ እግዚአብሔር የቅል ተክልን ምሳሌ በማድረግ ቅጠሉ በመድረቁ ዮናስ ባዘነ ጊዜ ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ሆኑ ያሳዝኑኛል›› በማለት ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መሆኑን አስረድቶታል፡፡

ዮናስም ነነዌ መሬት ላይ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረዳ፤ የነነዌ ሰዎችንም ‹‹ንስሐ ግቡ›› እያለ መስበክ ጀመረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ሆኖ ከላይ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል (ትንቢተ ዮናስ)፡፡ ታኅሣሥ ፭ ቀን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ‹‹ወበልዐ አሐደ ኀምለ›› በማለት ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር ያህል ሰዎች በእሳቱ እንደ ጠፉ ይነግረናል፡፡

ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ነው፤ በሦስት ቀናት ጾምና ጸሎት ንስሐ የገቡ የነነዌ ሰዎች ከጥፋት እንደ ዳኑ ሁሉ፣ በብሉይ ኪዳን አስቴር ሦስት ቀን ጾማ፣ ጸልያ በእስራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች (አስ.፬፥፲፭-፲፮)፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ሕፃኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ አግኝታዋለች (ሉቃ.፪፥፵፮)፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው ምላሽ መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መሆኑን ገልጿል (ሉቃ.፲፫፥፴፪)፡፡

ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው፡፡ ይኸውም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል፡፡ ዮናስ ለስብከት ፈቃደኛ ባይሆን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ እንዲሔድ አድርጎታል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አይደለም፤ እርሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ የነነዌ ሰዎች የተነሳሕያን ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ  ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ሆኑ ያሳዝኑኛል›› ያለው፡፡

ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀልን እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን፣ ጸልየን ከኃጢአታችን እንነጻ ዘንድ ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለችበት ወቅት እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለ ሆነ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ፤›› ይለናል፡፡

ስለሆነም በነቢዩ ዮናስ ላይ የተደረጉ ተአምራትንና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመሆኑን በማስተዋል፣ ለነነዌ ሰዎች የወረደውን ምሕረት በመገንዘብ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች እና ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል፡፡ ስንጾምም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶ በኃጢአት ለጠፋው ዓለም ይቅርታውን ይልካል፡፡ በመጾማችን ራሳችን ከመዓትና ከመቅሠፍት ከመዳናችን ባሻገር በእኛ በደል ምክንያት አገራችን፣ ዕፀዋቱና እንስሳቱም ሳይቀር ከድርቅና ከቸነፈር ይተርፋሉና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር