ጾመ ሰብአ ነነዌ
የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም.
ርዕሰ ደብር ብርሃኑ አካል
ጾመ ነነዌ ከአዋጅ አጽዋማት አንዱ ሲሆን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ቀን ደግሞ ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር 17 ቀን ድረስ ነው፡፡ ሲወጣ ወይም ወደፊት ሲገፉ ደግሞ እስከ የካቲት 21 ድረስ ነው፡፡ በእነዚህ 35 ቀናት/ዕለታት/ ስትመላለስ ትኖራለች፡፡ ከተጠቀሱት ዕለታት አይወርድም አይወጣም ማለት ነው፡፡
የሦስት ቀኑን ጾም የጾሙት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ሲሆኑ ከተማዋ በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ መሥራቿም ናሞሩድ ነው፡፡ ዘፍ.10፥11-12 ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የሆነ ከተማ እጅግ ሰፊና ያማረ ፤ የከተማው ቅጥር ርዝመት አሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ነበር፡፡ ሰናክሬም ብዙ ሕንፃዎችንም ሠርቶበት ነበር፡፡ /ዮናስ. 4፥11/
የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ በኃጢአታቸው ምክንያት ሊጠፉ ሲሉ ቸርነትና ምህረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስ መክሮ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ወደ ነነዌ ሕዝብ ሂድ አለው፡፡ ሉቃ.11፥30 ዮናስ የስሙ ትርጉም “ርግብ” ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ትንቢትን ተናግሯል፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል ፡፡ 2ነገ14፥25፣ ት.ዮና1፥1
እግዚአብሔርም “ሄደህ በነነዌ ላይ ስበክ” ባለው ጊዜ “አልሄድም” አለ፡፡ “አንተ መሀሪ ነህ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ስትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ፡፡” ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔር ግን ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧበማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩት ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባህሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ “በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባህር ጣሉኝ” ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነሱም “የሰው ደም በእጃችን እንይሆንብን አይሆንም” አሉት፡፡ ዕጣም ቢጣጣሉ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያው የእግዚአብሔር የማዳን መልእክት ዮናስ እንዲያደርስ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ነነዌ አደረሰው፡፡ ዮናስም ከእግዚአብሔር መኮብለል አለመቻሉን ሲረዳና ነነዌ መሬት ላይ መድረሱ ሲነገረው ለነነዌ ሰዎች “ንስሐ ግቡ” ብሎ መስበክ ጀመረ ዮናስ 1እና2 ፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ማራቸው /ዮና.3/
ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስህተት መሆኑን እግዚአብሔር ቅልን ምሳሌ በማድረግ አስረዳው፡፡ /ዮና.4/ ነቢየ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ሆኖ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል፡፡ በስንክሳር ታኅሣሥ 5 እንደሚነግረን ፤ወበልዓ አሐደ ኀምለ ይላል ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር አጥፍቶአል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የስራጵታ መበለት ሕፃን ዮናስ እንደሆነ /1ነገሥ.17፥19/ ሲያስረዳን ፤ክርስቶስ የዮናስን ከዓሣ ሆድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎታል፡፡ /ማቴ.12፥19-42/ ሉቃ.11፥30-32/፡፡
ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ናት፡፡ ይሄውም አስቴር አስቀድማ ሦስት ቀን ጾማ ጸልያ በእሥራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች ኢሳ.4፥15-16፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ልጇ ሕፃኑ ኢየሱስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ እንዳገኘችው ሁሉ ሉቃ.2፥46 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መሆኑን ገልጿል ሉቃ.13፥32፡፡
የነነዌ ሰዎች የተነሳህየን ምሳሌ ናቸው ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሕዝቦችና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለሆኑ ያሳዝኑኛል ያለው፡፡
ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለበት ወቅት እኛም ብንመለስ እና ንስሐ በንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ “ወደኔ ተመለሱ እኔም ይቅር እላችኋለሁ ”ብሎ አስተምሯል፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጾመ ነነዌ የሚከተሉትን ምሳለዎች እናገኝባታለን ታሪኩን በማስታወስ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሀሪነት የምናስታውስበት ነው፡፡ ይኸውም ፍጥረቶቹ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርጋል፡፡ ዮናስ ፈቃደኛ ባይሆን እንኳ በተለየ ጥበቡ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ሌላ ነቢይ አጥቶም አይደለም እሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለፈለገ እንጂ፡፡
በዮናስ አማካይነት የተደረጉ ተአምራትን መገንዘብና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመሆኑን ተገንዝበን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች አና ለወላጆች መታዘዝን እንማርበታለን፡፡ እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን ጸልየን ከኃጢአታችን እንድንነፃ ነው፡፡ ብንጾም እራሳችን፣ ሃገራችንን፣ እጽዋቱንና እንስሳቱም ሳይቀር በኛ በደል ምክንያት በድርቅ በቸነፈር እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ይቅር ስለሚል ነው፡፡
ጾመን እንድናበረክት ይርዳን
ይቆየን