ጽኑ እምነት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፲፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
የእምነት ጽናታቸው የተጋድሎ ሕይወታቸው እጅግ ድንቅ የሆነው፣ ለሌላው ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ገድላቸው ከተጻፈላቸውና የመታሰቢያ በዓል ከሚከበርላቸው ሰማዕታቱ መካከል ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ አብነት የሚሆኑ ናቸው፡፡ እለእስክንድሮስ የተባለው መፍቀሬ ጣዖት፣ ጸላዬ እግዚአብሔር፣ የዲያቢሎስ ምርኮኛ የሆነው በሰው እጅ ከድንጋይ ተጠርቦ ለተሠራው ጣዖት ሕዝቡን እንዲሰግዱ ሲያስገድድ፣ ስቶ ሲያስት፣ ሲያስፈራራ ኖሯል፡፡ አብዛኛው ለሥጋው ሳስቶ፣ መከራውን ተሰቆ ለጣዖት ሲሰግድ ሕፃን ቂርቆስ ግን እምቢ አለ፤ የቀደሙ አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክ ያውቃልና ልቡን አጸና፤ ለመከራው ተዘጋጀ፤ እናቱ ለልጇ ሳስታ፣ ለጣዖት ልትንበረከክ፣ ልትክድ ሲዳዳት ሕፃኑ ግን ጸና፤ መከራውን ሳይሰቀቅ እለ እስከንድሮስ ላቆመው ጣዖት አልሰግድም አለ፡፡
አናንያን፣ አዛርያን እና ሚሳኤልን ከእሳት ያወጣ ፈጣሪ እንደሚያድናቸው መሰከረ፤ የላላው የእናቱ እምነት ይጸና ዘንድ ወደ ፈጣሪው ተማጸነ፤ እናቱን ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አትጠራጠሪ፤ ከዚህ በኋላ ኩነኔ ሥቃይ የለም…›› እያለ አበረታት! መከራውን ሳይሰቀቁ ለቅጣት ከተዘጋጀው ፍሉ ውኃ ቢጨመሩም ሊቀ መላክት መጋቤ አዲስ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደ፤ በተለያዩ ነገሮች ተቀነባብሮ የፈላውን፣ ድምጹ እንደ ክረምት ነጎድጓድ የሚያስፈራውን ፍል ውኃ አቀዘቀዘው፤ የእናትና ልጁ እምነት፣ የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት፣ የእግዚአብሔር አምላክነት ክብር ተገለጠ፤ የጣዖት ከንቱነት የዲያቢሎስ ሐሰተኛነት ተጋለጠ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ የነገረው ሁሉ የእነርሱን ፈለግ ተከትለው፣ በእነርሱ እምነት ዓለትነት ላይ በተመሠረተችው እውነተኛ ሃይማኖት ጥላ ሥር ያሉ ሁሉ ስለያዙት እውነት፣ ስለ እምነታቸው መከራው ይመጣባቸዋል! ፈተናው መልኩን ይቀይራል እንጂ አይቀርም፤ እንደ መንፈሳዊ ብስለታችን፣ እንደ እምነታችን መጠን የሚገጥመንን መከራ (ፈተና) በጸጋ ልንቀበል ክርስትናችን ግድ ይለናል፤ ስለሆነም በአንዳች ነገር መረበሽ ወይም መደናገጥ አይገባም፡፡
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በአባታዊ መልእክቱ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹..ወዳጆች ሆይ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሊገለጥ ደግሞ ሐሴት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ፤ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ…፡፡›› (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፲፪-፲፬)
ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባወደሰበት በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ የሰማዕታት የተጋድሏቸውን ምሥጢር እንዲህ ይገልጠዋል፤ ‹‹…ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ…፡፡›› (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ዳዊት)
በእምነታቸው ጸንቶ፣ ፍርሃት ርቆላቸው፣ ማስተዋል ተሰጥቷቸው፣ የምሥራቹን ወንጌል፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ሰንቀው፣ ሥጋዊው ሞትን ድል አድርገው በክብር ወደ ሰማያዊው ዓለም የተጓዙት ሰማዕታት ታላቅ ተምሳሌት ናቸው፡፡
የቅዱሳኑ ሰማዕታት የቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት እየሉጣ ጸሎት፣ ምልጃና ተራዳኢነት አይለየን፤ በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!
አሜን!!!