‹‹ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ›› (መዝ.፻፵፩፥፯)

ነሐሴ ፳፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በሰማይና ምድር በሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ ምስጉን የሆነ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንን ውበት እንድንመለከትባቸውና እግዚአብሔርን  ለማመስገን እንድንሰባሰብባቸው ምክንያት አድርጎ ከሰጠን  ቅዱሳን አባቶች መካከል ታላቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንዱ ናቸው፡፡

አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ፈቃድና በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል አብሣሪነት ከቅዱሱና ከካህኑ አባታቸው ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፻፪፲፪ዓ.ም. በቡልጋ አውራጃ ኢቲሳ በምትባል ቦታ ተወለዱ፡፡

አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተወለዱ በሦስት ቀናቸው የትንሣኤው መታሰቢያ በምትሆን በታወቀች በዕለተ ሰንበት ከቀኑ በሦስት ሰዓት እጃቸውን አንሥተው ወደ ሰማይ በመመልከት     ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በባሕርይ በሕልውና አንድ የሚሆን አብ በአካል በስም ልዩ ነው፡፡ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባሕርይ በሕልውና አንድ የሚሆን ወልድ በአካል በስም ልዩ ነው፡፡ ከአብ ከወልድ ጋር በባሕርይ በሕልውና አንድ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ በአካል በስም ልዩ ነው›› ብለው አመስግነዋል ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን (ምእመንን) ባማረ በተወደደ ትምህርታቸው ደስ የሚያሰኟትና በጽኑ ሃይማኖታቸውም ሥራዋን የሚያጸኑ ናቸውና በአርባ ቀን በጥምቀት የወጣላቸው ስም ፍስሓ ጽዮን (የጽዮን ደስታ) የሚል ነበር፤ ከዕለታት አንድ ቀን ለአደን በወጡበት አጋጣሚ ግን ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ካሳደረባቸው በኋላ በቅዱስ ሚካኤል አማካኝነት በወንጌል መሳሪያነት እንስሳትን ከማደን ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለማደን እንደተመረጡና ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባልና ይህም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡

ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኢትዮጵያን በወንጌል ብርሃን ለማድመቅ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባን ለማስተማር እና ለማጥመቅ እንደ እንደ ቅዱስ ፊልጶስ ብዙ ተጉዘዋል፡፡

እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች በጻድቃን ጸሎት እጅግ የምንመካው እንዲሁ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር እጅግ ብዙ ቃል ኪዳንን ስለሰጣቸውና በጻድቃን ጸሎት እግዚአብሔር ይረዳናል፤ በጻድቅ ሰው ጸሎትም በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ እናገኛለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር ፻፵፩፥፯ ‹‹አቤቱ ስምህን አመሰግን ዘንድ ነፍሴን ከወኅኒ አውጣት፤ ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ›› በማለት የተናገረው ለዚህ ነው፡፡

በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን የሃይማኖታችንን ዋጋ እስከምናገኝና ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንደ ቸርነቱ እስኪንወርስ ድረስ እንደ ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያትና ሊቃውንት    በጸሎታቸው የሚጠብቁን እንደ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያሉ አባት ናቸው፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር ባወቀው ነገር በእግዚአብሔር በኩርነት የጻድቅ ሰው ሞት ልዩ ነው ያለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ (መዝ.፻፲፭፥፭)፤አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ከዚህ ዓለም ድካም ለማሳረፍ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወዳጅ እናቱ ከድንግል ማርያም ጋር፣ ዐሥራ አምስቱ ነቢያት፣ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ብዙዎቹም የሰማይ ሠራዊት የመላእክት አለቆች የብርሃን ልብስን ይዘው ተገኝተዋልና፡፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅግ ብዙ ቃል ኪዳንን ሰጥቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በስማቸው ለሚያንጽ፣ የገድላቸውን መጽሐፍ ለጻፈ እና ላጻፈ፣ እንግዳ ለተቀበለ፣ በጻድቁ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የበዓል ቀን ደስ ብሎት ያከበረ ሰው ቢኖር ሺህ ዓመት ከአባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር አብሮ እንደሚኖር ቃል ገብቶለታል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስለ ቀናች ሃይማኖታቸው፣ ስለዚህችም የቀናች ሃይማኖት ለማስተማር ስለ መዞራቸው፣ ደማቸውንም ስለ ማፍሰሳቸው፣ ጣዖታትንና አጋንንትን ስለ ማጥፋታቸው፣ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መውረዳቸው፣ ለጸሎት በመቆም ብዛት ስለተሰበረው እግራቸው፣ ስለ ጾማቸውና ስለ ልቡናቸው ንጽሕና በአጠቃላይ ሰባት የብርሃን አክሊላትን ከጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዕረፍታቸው ተቀብለዋል፡፡

በቅዱስ ወንጌል ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም›› በማለት ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ቃል (ማቴ.፲፥፵-፵፪) በተግባር የምትፈጽም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም መጋቢት ፳፬ ቀን የፅንሰታቸውን፣ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የልደታቸውን፣ ጥር ፳፬ ቀን የስባረ ዐፅማቸውን (እግራቸው የተሰበረበትን)፣ ግንቦት ፲፪ ቀን የፍልሰተ ዐፅማቸውን፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍታቸውን በዓል በታላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡

በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር በመራቅ ስብራት ላጋጠማት ነፍሳችን ያለ ዕረፍት ቆመው የጸለዩት የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጸሎትና በረከት ይጠብቀን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ምንጭ ፡-

  • የመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ
  • ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት