ጥንታዊው አሸተን ቅድስት አርሴማ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ህንፃን ለመሥራት ጥሪ ቀረበ።
በወ/ኪዳን ወ/ኪሮስ
በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተችው የአሸተን ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ህንፃ ለማሠራት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ምእመናኑን ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።
የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ አባ ወልደ ነአኩቶ ለአብ እንደገለጡት፤ ግራኝ አህመድ በኢትዮጵያ አብያተ ክርስትያናት የጥፋት ዘመቻ ባወጀ ጊዜ ካጠፋቸው ታላላቅ ገዳማት አንዱ የሆነው ይህ ታሪካዊ ቦታ፣ ቤተክርስቲያኑ ሲፈርስ የተወሰነው ነዋየ ቅዱሳቱ በአሸተን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እንዲቀመጥ ሲደረግ ሌሎችን ቅርሶች ጠላት በማያገኝበት ዋሻ እንደደበቁት ይነገራል፡፡
ሕዳር 6 ቀን 2001 ዓ.ም በቦታው መቃኞ/መቀረቢያ/ ተሰርቶ የቅድስት አርሴማ ታቦት ገብቶ የአካባቢው ምእመን እየተገለገለ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ የቤተክርስቲያኑን መሰረት ድሮ ቤተክርስቲያኑ ይገኝበት በነበረው ቦታ ላይ የወጣ ሲሆን ቀሪውን ሥራ አጠናቆ ለመጨረስ በአካባቢው የሚገኘው ምእመናንም በኑሮ ዝቅተኛ ስለሆነ ገንዘብ ቢያዋጡም ቤተክርስቲያኑን ከፍጻሜ ለማድረስ አለመቻሉን አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
ህንፃ ቤተክርስቲያኑን ሥራ በገንዘብ ለመደገፍ ለምትፈልጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላሊበላ ቅርንጫፍ የአሸተን ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የሒሳብ ቁጥር 40 ብላችሁ መላክ የምትችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሰሜን ወሎ ሃገረ ስብከት ከቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በኩል በስተመሥራቅ 6 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ከተጓዙ በኋላ ይህችን ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ያገኟታል። አቀማመጧ ጉብታ ላይ ስለሆነ በአካባቢዋ ያሉትን የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትንና አካባቢውን ለመቃኝት እጅግ የተመቸች ናት።
በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አባ ተክለ ፅዮን በተባሉ ቅዱስ አባት እንደተመሰረት የሚነገርለት ይህ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን በ1929 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የቤተክርስትያኑ ሊቃውንት ብዙ መከራ እንደደረሰባችው ይነገራል።