ጣፋጯ ፍሬ

ግንቦት ፳፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ተፈጥሮ አድሎኝ አንቺን ማወቄ ዕፁብ ድንቅ ሆኖብኛል፤ የሕይወቴ ፍሬ አስቀድሜ ያየሁሽ በልምላሜ ባሸበረቀው በገነት ነበር፤ ጫፍሽ እስከ ሰማይ የሚደርስ፣ ፍሬሽ እንደ ሮማን የተነባበረ፣ ከእግር እስከ ራስሽ ምሉ የሆንሽው ጣፋጯ ፍሬ አንቺ ነሽ፡፡ የፍሬሽን ጣዕም አፌ አጣጥሞ ሳያልቅ ተክተሽ ትገኛለሽ፡፡ አንዲቷን ፍሬሽን በበላኋት ጊዜ ጣዕሟ ከአፌ፣ መዓዛዋ ከአንፍንጫዬ ሳይለይ እስከ ሰባት ቀን ይቆያል፡፡

አባቶቼ ‹‹መዓዛዋ ያለ ደዌ ያለ ሕማም ነፍስን ከሥጋ ይለያል›› ሲሉ የነገሩኝን ሳስብ እጅግ ይደንቀኛል፡፡ ይህ ግሩም የፈጣሪ ሥራ እንዴት ይገለጻል? ‹‹መንክር›› ብቻ ብሎ ማለፍ እንጂ ሌላ ምን ይባላል!የቀመሱሽ ሁሉ ተደነቁብሽ! የአምላክ ጥበብ የተገለጠብሽ ጣፋጯ ፍሬ መተኪያ የለሽ!

ዘለዓለማዊ ሕይወትን የማገኝብሽ ባለ መልካሟ መዓዛ ፍሬ የአምላኬ ስጦታ ነሽ፤ በገነት ፈጥሮ ቢያሳየኝ ሳላውቅሽ መቅረቴና ልመገብሽ ባለመቻሌ እጅጉን ኀዘን ይሰማኝ ነበር፡፡ ፈጣሪ በአንቺ ሕይወትን ሊሰጠኝ ጣፋጭ አድርጎ ቢፈጥርሽ ሳላውቅሽ ያልታዘዝኩትን ፍሬ በልቼ መራራ ሞትን በራሴ አመጣሁ፡፡ አሁን ግን አወኩሽ! የሕይወቴ ጣፋጯ ፍሬ በአንቺ ነፍሴ ተፈውሳለችና፡፡

የአምላክ ቸርነት የተገለጠብሽ የመታዘዜ ምልክት የሆንሽው ጣፋጯ ፍሬ ዕፀ ሕይወት አርዌ ምድር ከሰማያዊ ቤት ለይቶ ያስወጣበትን ዲያብሎስ ያበላንን መርዝ ከጉሮሮዬ መንቅረሽ አስወጣሽልኝ፡፡ ያቺ የበደል ቀን የኀዘኖቼ ሁሉ መጀመሪያ ሆና ዘወትር ስታሠቃየኝ ለ፶፻፭፻ ዘመናት ኖራለች፤ ልረሳት ብል ሳይቻለኝ ቀርቶ ይባስ ብሎ ሞትን እንዳመጣች በማወቅ ትግል የተደረገባት የጉሮሮዬ ማንቁርት ማስታወሻ ሆነኝ፡፡

ያጣሁትን ቅድስናዬን እንዴት ልመለስው? ንጽሕናዬን ከየት ላምጣው? ልጅነቴንስ ከወዴት ላግኘው? ከአምላኬ ያጣላችኝ ያች ዕፀ በለስ ከገነት አስወጥታ ወደ ከፋውና የጨለመው ዓለም ስላወረደችኝ ሕይወቴ መረረብኝ፡፡ ሰላምና ደስታንም አጣሁ፤ ተስፋዬም መነመነ፤ የጌታዬን ቃል ኪዳን ባላስብ ኖሮማ የባሰ ኀዘንና ትካዜ ይሰማኝ ነበር፡፡

በበደሌ ምክንያት እሾህና አሜከላ አብቅላ ሐሣር መከራ ስታበላኝ የኖረችው ምድር ክብርሽንና ገናንነትሽን ልታሳውቀኝ ጊዜዋን ጠበቀች፡፡ ዘመኑ ሲፈጸምም የሕያዋን እናት፣ የዓለም መድኃኒትን በወለድሽልንና ዕፅ ሕይወት በሆነሽው በቅድስት ድንግል ተተክታ የሰውን ዕዳ ሊከፍልብሽ እንደ አሮን በትር አብበሽና አፍርተሽ ተገኘሽ፡፡ የሮማን አበባ መሳይ መልካሟ ርግብ ንጽሕት ድንግል አንቺ ከዕፀ ሕይወት ላይ ያለሽ ጣፋጯ ፍሬ ነሽ፡፡

እናትና አባትሽ ጣፋጭነትሽን ዐውቀው ይመስላል ስምሽን ‹‹ማርያም›› ያሉት፡፡ ከምድር ሁሉ የበለጠው ጣፋጭ መብል ‹‹ማር›› ከገነት ሁሉ ጣፋጭ መብል ‹‹ያም›› መጠሪያሽ ሆኗልና፡፡ ድንግል እመቤት የአንቺን ስም ጠርቼ የአምላኬን ርስት እወርስ ዘንድ ፈቃዱ በመሆኑ መንግሥተ ሰማይ መግቢያዬ አንቺ ጣፋጯ ፍሬ ነሽ፡፡

የወይን ግንድ ተቆርጦ በምድር ሲሰቀል፣ ከመስቀሉ ሥር ተገኝተሽ፣ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ የነሣውን መድኃኒት በጽዋ ተቀብሎ በዓለም ለረጨው ለቅዱሱ መልክተኛ መፈጸሚያ ሆንሽ፡፡ የጽዋ ሞት ያጠጣኝ የጠላት መርዝ በውስጤ እንዳይገኝ አንቺን በእርሱ ጽዋ ተቀብለን በላንብሽ፤ ጠጣንብሽ፡፡ ዕፀ ሕይወት አንቺ ጣፋጯ ፍሬ የነፍስ ምግብ ነሽ፡፡

በኃጢአቴ የተነሣ ተረግሜ ስኖር ነፍሴ አንቺን ተርባ ትጣራ ነበር፤ ‹‹ሔዋን ዕፀ በለስ በልታ ባደረገችው ዓመፅ በባሕርያችን ያደረ የቀድሞው እግርማን በእርሷ የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የሁላችን መመኪያ ነች፤›› … ‹‹እግዚአብሔር “የባሕርይህን ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ” በማለት ለዳዊት በእውነት ማለ›› ተብሎ እንደተተነበየ የአምላክ እናት ‹‹ነቢያት የፈለጓት መድኃኒት›› በመሆንሽ እኔም እፈልግሻለውና በሕይወቴ ኑሪልኝ!

መላእክት በዙሪያሽ ረበው የሚታዮብሽ፣ በቀኝና በግራ የሚከቡሽ ቤዛዊተ ዓለም መድኃኒታችን ነሽ፡፡ በአምላክ ቀኝ የምትቆሚው እናታችን ክብርሽ ከሁሉም ይለያል፡፡ የሕይወት ፍሬ ከአንቺ የተወለደብሽ ቅድስት ድንግል ማርያም የነፍሳችን ፈውስ ነሽ!

አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ከአንቺ ተወልዶ ‹‹ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፤ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው›› በማለት የደረሰልሽ ቅዱሱ የሶርያው ሰው ኤፍሬም ምስጋናሽን ገልጾ ባይጨርሰው ‹‹ስለ እርሷ ድንቅ ሆኖ የሚነገረውን ይህን ምሥጢር ማወቅ የሚቻለው ምን ልቡና ነው? መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማት የሚቻለው ምን ጆሮ ነው?›› በማለት አደነቀሽ፤ አመሰገነሽ፡፡

የሕይወቴ ጣፋጯ ፍሬ እኔም እመሰግንሻለሁ!

ምንጭ፡- መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘሠሉስና ዘዓርብ፣ የኀሙስ ውዳሴ ማርያም፣ ነገረ ማርያም፣ መጽሐፈ ቅዱስ (መጽሐፈ ሐዲስ)