ግዝረቱ ለእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ
ጥር ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪት ሕግ የሆነውን ግዝረት የፈጸመበት ዕለት ጥር ስድስት ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ክርስቶስ በሥጋ ግዝረትን ተቀበለ፣ ለአባቶች የተሰጠውን ቃልኪዳን ይፈጽም ዘንድ›› ብሎ መስክሯል፡፡ (ሮሜ ፲፭፥፰)
በዚያን ጊዜ ጌታችን ወደ ቤተ ግዝረት እንዳልገባና እንዳልተገረዘ የሚመስላቸው ብዙዎችም ነበሩ፡፡ እነርሱ እንዳሰቡት ሁኖ ቢሆን ኑሮ አይሁድ ታላቅ ምክንያትን ያገኙ ነበር፡፡ ጌታችን ግን የግዝረትን ሕግ ፈጸመ፤ ለእኛ በግዝረት ፈንታ የክርስትና ጥምቀትን ሰጠን፤ የፋሲካውንም ቂጣ በላ፤ በእርሱም ፈንታ ሥጋውንና ደሙን ሰጠን።
የከበረ ወንጌል ‹‹ስምንተኛው ቀን በተፈጸመ ጊዜ ሕፃኑን ሊገዝሩት ወሰዱት፣ ሳትፀንሰው መልአኩ እንዳወጣለት ስሙን ኢየሱስ አሉት›› እንዳለ ንጽሕት ድንግል እመቤታችን ማርያም ጻድቅ አረጋዊ ዮሴፍን ‹‹እንደ ሕጉ ልጄን እንዲገርዘውና ስሙን እንድንሰይመው ብልህና አዋቂ የሆነ ገራዥ ሰው አምጣልኝ›› አለችው፡፡ አረጋዊ ዮሴፍም ሄዶ የሚገርዝ ባለሙያ አመጣ፡፡ ያ ባለሙያም ሕፃኑን ልጅ ጌታችንን በእናቱ ክንድ ባየው ጊዜ ‹‹እንዲገርዘው ሕፃኑን በጥንቃቄ ያዙት›› አላቸው፡፡ ሕፃን ጌታ ኢየሱስም ‹‹ባለሙያ ገራዥ ሆይ! ደሜ ሳይፈስ ትገርዘኝ ዘንድ ትችላለህን? በዚያች ዕለት ካልሆነ በቀር ደሜ አይፈስምና ጎኔን በጦር ሲወጉኝ ያንጊዜ ውኃና ደም ይፈሳል ለአዳምና ለሚያምኑ ልጆቹ መድኃኒት ይሆናልና›› አለው፡፡ ጌታችንም ይህንን የተናገረውን ገራዡ በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ዕቃውንም ሰብስቦ ተነሥቶ ከሕፃኑ እግር በታች ሰገደ፡፡ ያንጊዜም ምላጮቹ በእጆቹ ላይ ቀልጠው እንደውኃ ሆኑ፡፡ ባለሙያውም ክብርት እመቤታችንን ‹‹ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ ይህ ልጅሽ ስለእርሱ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የሕያው አምላክ ልጅ ነው›› አላት፡፡
ሕፃኑም መልሶ ለዚያ ባለሙያ ‹‹እኔ ነኝ፣ ትገዝረኛለህን ወይስ ተውክ? ወይስ የአባቶቼ አባቶች እንዳደረጉ እኔ ላድርግ?›› አለው፡፡ ባለሙያውም ‹‹የአባቶችህ አባቶች እነማን ናቸው? አለው፡፡ ሕፃን ጌታችንም ‹‹አብርሃም፣ ይስሃቅ፣ ያዕቆብ የሕዝቡ ሁሉ አባቶች የሆኑ ናቸው፤ ለእነርሱም ይህ ግዝረት አስቀድሞ ከአባቴ ዘንድ ተሰጣቸው›› አለው፡፡ ባለሙያውም ‹‹እኔ ከአንተ ጋር እናገር ዘንድ አልችልም በአንተ ሕልውና መንፈስ ቅዱስ አለና›› አለው፡፡ ያንጊዜም ሕፃን ጌታችን ዐይኖቹን ወደሰማይ አቅንቶ ‹‹አባት ሆይ ለአብርሃም፣ ለይስሃቅ፣ ለያዕቆብ አስቀድሞ ግዝረትን የሰጠሃቸው ያችን ግዝረት ዛሬ ለእኔ ስጠኝ›› አለ፡፡ ያንጊዜ ያለሰው እጅ በሕፃኑ ሥጋ ላይ ግዝረት ተገለጠች፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድንግልናዋ ሳይለወጥ ከማኅፀኗ እንደ መውጣቱ የጌታችን ግዝረቱም የማይመረመር ሆነ፡፡ እንዲሁ በተዘጋ ቤት መግባቱና መውጣቱ እንደማይመረመር እንዲሁ እንደፈቀደ ከረቀቀ ጥበቡ ችሎታውን በመገረዝ ከሥጋው ምንም ምን ሳይቆረጥ ገለጠ፡፡ አዳምንና ልጆቹን ያድናቸው ዘንድ በፈቃዱ ከጎኑ በመስቀል ላይ የሚፈሰው ደምና ውኃ ካልሆነ በቀር ብዙም ሆነ ጥቂት ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ በፈቃዱ ሕጉ እንዲፈጸም አስቀድሞ አዘዘ እንጂ፡፡ ያም ባለሙያ ገራዥ ይህንን ተአምር ባየና የሕፃኑንም ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ሦስት ጊዜ ሰገደና ‹‹በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ የእስራኤል ንጉሥ ነህ›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ከጌታችን ከተአምራቱ ያየውንና የሰማውን እየተናገረ እየመሰከረ ወደቦታው ሄደ፡፡
ለሕፃኑ ጌታችን ከቸር አባቱ ጋራ ማኅየዊ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ክብር ምስጋና ስግደትም ይሁን፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፤ በቸርነቱ ይማረን::
ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር