ግሩማን ፍጥረታት
መምህር ቢትወደድ ወርቁ
የካቲት ፰፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ከአዳም ትውልድ ሰባተኛ የሆነው ነቢዩ ሄኖክ ያልተመረመሩ እጅግ አስደናቂ (ግሩማን) ፍጥረታትና አዕዋፍ ስለመኖራቸው ጨምሮ ሲጽፍ “ከዚያም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሄድኹ፤ በዚያም ታላላቅ አውሬዎችን አየሁ፤ አንዱ ከሌላው ልዩ ነው፤ የወፎቹም ፊታቸው ይለያያል፤ መልካቸው ቃላቸውም አንዱ ከሌላው ይለዋወጣል” ይላል፡፡ (ሄኖክ ፰፥፳፱)
እግዚአብሔር አምላካችን ከፈጠራቸው ግሩማን ፍጥረታት መካከል ብሔሞትና ሌዋታን ይገኙበታል፤ ስለ እነርሱም በሊቃውንቱ ብዙ የተባለ ቢሆንም በዚህ ክፍል የቋንቋው ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ያሉትን እናውሳ፡፡ ሊቁ ብሔሞት በቁሙ “የየብስ አንበሪ፣ ከባሕር ተፈጥሮ በየብስ የሚኖር፣ አራዊት የሚፈሩትና የሚገዙለት፣ ከአራዊት ሁሉ የሚበልጥ፣ መጨረሻ ግዙፍ የእንስሳት ራስ፣ የአራዊት ንጉሥ፣ በኩራቸው፣ ቀዳማያቸው፣ በተፈጥሮ የሌዋታን ወንድም ባሏ መሰልዋ ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፪፻፶፯)
የብሉይ መጻሕፍት ደግሞ “ዝሆን ነው” በማለት ጠቅሰዋል፡፡ በመጽሐፈ ሄኖክ “ከዚያ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሄድሁ፤ በዚያም ቦታ ታላላቅ አውሬዎችን አየሁ፤ አንዱ ካንዱም ልውጥ ነው፤ የወፎችም ፊታቸው ይለዋወጣል፤ በእነዚህ አውሬዎችም አጠገብ በምድር ዳርቻ ሰማዩ በላዩ ያረፈበት አድማስን የተከፈቱ ደጃፎችንም አየሁ” ያለውንም ጠቅሰው ያብራራሉ፡፡ (ሄኖክ ፰፥፰)
ሊቁ ሌዋታንንም እንዲህ ገልጸዋታል፤ “የባሕር አውሬ፣ እንስሳ፣ ዘንዶ፣ ታላቅ ዓሣ፣ እንስት ዐንበሪ፣ ምድርን እንደ ዝናር እንደ ጋን ሰንበር ወይም እንደ ቀለበት እንደ አንባር ዙራ ተጠምጥማ ዐቅፋ የያዘች ናት፡፡” (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፭፻፷፩)
ግሩማን ፍጥረታቱም “በዚያች ቀንም ሁለቱ አንበሪዎች ይለያያሉ፤ ሌዋታን የምትባለው አንስታይ አንበሪ ከውኃዎች ምንጮች በላይ በባሕሩ ጥልቅ ትኖር ዘንድ ትለያለች፤ የማይታየውን ምድረ በዳ በደረቱ የሚይዝ ስሙ ብሔሞት የሚባለው ተባዕት አንበሪም ይለያል፤ የቦታውም ስም ጻድቃንና የተመረጡት በሚኖሩበት የመናፍስት ጌታ ለፈጠራቸው ሰዎች መጀመሪያቸው ከሆነው ከአዳም ሰባተኛ የሆነ አያቴ በተወሰደበት በገነት ምሥራቅ ያለ ዴንዳይን ይባላል፡፡” (ሄኖክ ፲፮፥፲፪-፲፬)
ስለነዚህ እጅግ አስደናቂ ፍጥረታት አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በኢዮብ መጽሐፍም ሲናገር “የሠራሁትን አውሬ እስኪ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል፤ እነሆ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው፤ ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤ የወርቹ ጅማት የተጎነጎነ ነው፤ አጥንቱ እንደናስ አገዳ ነው፤ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አውራ ነው፤ ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው፤ የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ ምግብን ያበቅልለታል፤ ጥላ ካለው ዛፍ በታች በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል፤ ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፤ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከቡታል፤ እነሆ ወንዙ ቢጎርፍ አይደነግጥም፤ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል፤ ዐይኖቹ እያዩ ይያዛልን? አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን?” ይላል፡፡ (ኢዮብ ፵፥፲፭)
ግሩማን ከሚባሉት አራዊት ጥንድ መንጋጋ ስላለው፣ ጥርሱ ስል ስለሆነውና ቆዳውም ስለጠነከረው፣ ከአፉም እሳት ስለሚወጣውና ሰይፍና ጦር ስለማያሸንፉትም አስፈሪ አውሬ ሲገልጥለት “ስለ አካላቱና ስለ ብርቱ ኃይሉ፣ ስለ መልካም ሰውነቱ ዝም አልልም፤ የውጭ ልብሱን ማን ይገፋል? በጥንድ መንጋጋው ውስጥ ማን ይገባል? የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው? በጥርሶቹ ዙሪያ ግርማ አለ፤ ቅርፊቶቹ ጠንካራ ስለሆኑ እርሱ ትእቢተኛ ነው፡፡ በጠባብ ማተሚያ እንደ ታተሙ ናቸው፤ እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም፤ እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፡፡ እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል፤ እንጥሻው ብልጭታ ያወጣል፤ ዐይኖቹም እንደ ወገግታ ናቸው፤ ከአፉ ፋናዎች ይወጣሉ፤ የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል፤ እንደ ፈላ ደስትና እንደሚቃጠል ሸምበቆ ከአፍንጫው ጢስ ይወጣል፤ እስትንፋሱ ከሰልን ታቃጥላለች፤ ነበልባልም ከአፉ ይወጣል፤ በአንገቱ ኃይል ታድራለች፤ ግርና በፊቱ ይዘፍናል፤ የሥጋውም ቅርፊት የተጣበቀ ነው፤ እስከማይንቀሳቀሱም ድረስ በእርሱ ላይ ጸንተዋል፤ ልቡ እንደ ድንጋይ የደነደነ ነው፤ እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጸና ነው፤ በተነሣ ጊዜ ኃያላን ይፈራሉ፤ ከድንጋጤም የተነሣ ያብዳሉ፤ ሰይፍና ጦር ፍላፃና መውጊያም ቢያገኙት አያሸንፉትም፤ ብረትን እንደ ገለባ፣ ናስንም እንደ ነቀዘ እንጨት ይቆጥራቸዋል፤ ፍላፃ ሊያብርረው አይችልም፤ የወንጭፍም ድንጋዮች እንደ ገለባ ይሆኑለታል፤ በሎታውን እንደ ገለባ ይቆጥረዋል፤ ሰላጢኑም ሲሰበቅ ይስቃል፤ ታቹ እንደ ስለታም ገል ነው፤ እንደ መዳመጫም በጭቃ ላይ ያልፋል፤ ቀላዩን እንደ ድስት ያፈላዋል፤ ባሕሩንም እንደ ሽቱ ምንቸት ያደርገዋል” ብሎታል፡፡ (ኢዮብ ፵፩፥፬-፳፬)
በመጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤልም እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ስለነዚህ ግሩማን ፍጥረታት ተጽፏል፡፡ “ያን ጊዜ የፈጠርካቸውን ሁለቱን እንስሳት ጠበቅህ፤ ያንዱን ስሙን ብሔሞት አልከው፤ የሁለተኛውንም ስሙን ሌዋታን አልከው፤ በየራሳቸው ለየሃቸው፤ የናጌብ ውኃ ያለበት ያ ሰባተኛው እጅ ሊወስናቸው አይችልምና አራቱ ተራሮች ባሉበት በዚያ እርሱ በውስጡ ይኖር ዘንድ ለብሔሞት ከስድስቱ እጅ አንዱን እጅ ሰጠኸው፤ ለሌዋታንም የባሕሩን ሰባተኛ እጅ ሰጠኸው፡፡” (ዕዝራ ሱቱ. ፬፥፵፱-፶፪)
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቅዱሳን ነቢያቱ አንደበት ስለነዚህ ግሩማን ፍጥረታት እንዲህ መናገሩ የእርሱ ሥራ እንደማይመረመርና አማኞችም ይህን አውቀው የልበ አምላክ የክቡር ዳዊትን ቃል ይዘው “እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፡- ሥራህ ግሩም ነው” እያሉ ሊያመሰግኑት እንደሚገባ የሚያሳየን ነገር ነው፡፡ (መዝ.፷፭፥፫) ዳግመኛም ስለ ፍጥረታት ስናስብና ስንማር የእግዚአብሔርን ቸርነት እንድናስብ ያደርገናል፡፡
ግሩማን ፍጥረታት አምላካችን እግዚአብሔር ካጎናጸፋቸው ጉልበት ቅልጥፍናና ኃይለኝነት አንጻር እንደሌሎች እንስሳት ቢገለጡና ከሰው ልጆች መኖሪያ የቀረቡ ቢሆኑ ኖሮ የሰውን ልጅ በምን መጠን ሊጎዱ እንደሚችሉ እናስተውል! እርሱ ግን ቸር ነውና እነዚህን ፍጥረታት ከሰው የራቁና የተሰወሩ አደረጋቸው፡፡ ስለእነዚህ ፍጥረታት እግዚአብሔር በገለጠው መጠን ብቻ ይታወቃል፡፡ ብሔሞትና ሌዋታን እንደ መቀነት፣ ምድር ደግሞ እንደ ወገብ ሆና በዙሪያዋ ተጠምጥመው ይኖራሉ፤ ቅዱሳንም በቅድስና የብቃት መዓርግ ላይ ሲደርሱ ይመለከቷቸዋል፡፡ (መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት ገጽ ፵፩)
የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት አይለየን፤ አሜን፡፡
ይቆየን!
ምንጭ፡- መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት፣ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ፊስአልጎስ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ፡- ፳፻፱ ዓ ም። መጽሐፈ ሥነፍጥረት ክፍል ፫ ለከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ተማሪዎች የተዘጋጀ ፡- ዲያቆን ከፍያለው ታደሰ ፲፱፻፺፫ዓ ም