ጋብቻና ጾታ
ክፍል ሦስት
ዲያቆን ዘሚካኤል ቸርነት
ጥር ፲፫፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ፈቃድ ለሐሳብ መነሻ ነው፤ አንድ ሰው አንድን ጉዳይ ማሰብ የሚጀምረው ከፈቃዱ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ሐሳብና ፈቃድ በአገባባዊ ፍቺአቸው ተለዋዋጭና ተመሳሳይ የሚተካካ ትርጒም ይኖራቸዋል፡፡ ጋብቻም በጥሬ ትርጉሙ ኪዳን ማለት በመሆኑ በሁለት አካላት መካከል የሚፈጸም ውል ስምምነት ነው፡፡ አንድን ጎጆ ለመምራት በፈቃድ ላይ የሚመሠረት ውል (ኪዳን) ነውና፤ የጋብቻ ኪዳን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን መጨረሻው ደግሞ ይህ ዓለም ሳይሆን ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት ናት፡፡
የጋብቻ ኪዳን በሁለት አካላት (ባልና ሚስት) መካከል የሚደረግ ውል ስምምነት ነው፤ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ውል ሲሆን መሥራቹና ጸጋን የሚያድለው እግዚአብሔር ነው፡፡ በዓለም ላይ የምንመለከተው ጋብቻ የወንድና የሴት ውሕደት ብቻ ሲሆን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይጨመራል፡፡ ተጋቢዎቹና እግዚአብሔር በኪዳን ተመሳሳይ ፈቃድ ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ መውጣት መውረድ ስላለበት ይህም ፈቃዱ አብሮ ይወርዳል፤ አብሮ ይወጣል፤ እንደሚገጥመው የሕይወት መሰናክልና ከፍታ አንድ ጊዜ መጥፎ አንድ ጊዜ መልካም ይሆናል፤ የሥጋ ድካም አለበትና የጸባይ መለዋወጥ ይኖረዋል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚለዋወጥ ሐሳብም ፈቃድም አይኖርም፤ የእግዚአብሔር የሆነውና እርሱ እግዚአብሔርም መልካም፣ በጎ፣ ጥሩ ልዩ ነውና፡፡
አምላካችን እግዚአብሔርን ባልተረዳነው ቁጥር በሕይወታችን፣ በትዳራችን ላይ የሚገጥሙን ነገሮች የእግዚአብሔርን መልካምነት እንድንጠራጠር ያደርጉናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁል ጊዜም ሁሉንም ነገር የሚያደርገው ለራሳችን ጥቅም ነው፡፡ አንድ ሰው የሰዶምና ገሞራ ታሪክን አንብቦ “እንዴት እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ያጠፋል?” ብሎ ሊያስብ ይችላል፤ ነገር ግን ታሞ የማይድን፣ አልፎም ተርፎም ለሌላው የሰውነታችን ክፍል በሽታውን የሚያዛምት አካል ካለ እርሱን በሐኪም ትእዛዝ ብንቆረጥ ሐኪሙን መጥፎ ልንለው ይቅርና አካሌን ቆረጠው፤ አጎደለኝ አንለውም፡፡ ይልቁንም አከመኝ እንለዋለን እንጂ፡፡ ለአንድ ሐኪም የዚህን ያህል ምክንያታዊ ከሆንን ለእግዚአብሔርማ እንደ ቅዱሳን መላእክቱ በገባንም ባልገባንም ጉዳይ ሁሉ ለመልካም እንደሆነ በማመን የበለጠ ምክንያታዊ መሆን ይገባናል፡፡
ኦርቶዶክሳዊ የጋብቻ ሕይወት በወንድና ሴት መካከል ያለውን ሕይወት፣ ኪዳን የመጠበቅ ሕይወት ነው፡፡ ይህም ፈቃድ እንደ ቅድስት ሥላሴ ያለ ፈቃድ አንድ ነው፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ፈቃድ አላቸው፤ እንደምንል ሁሉና ወንድ ሴት በጋብቻ ላይ አንድ ፈቃድ አላቸው ማለት ነው፤ ይህም ፈቃድ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንግሥተ ሰማያትን ሊያወርስ እነርሱ ደግሞ እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ በፈቃድ በሚገቡት ኪዳን አንድ ይሆናሉ፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንም ምሥጢረ ተክሊል አንዱ የሆነበት ምክንያት በኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ስላለ ነው፡፡ የሁለቱ አካላት አንድ መሆን እንዴት እንደሆነ አናውቅም፤ አድራጊው የሰው ልጅ የማይመራመረው ቅዱስ እግዚአብሔር ስለሆነ ምሥጢር ተባለ፡፡ በጋብቻ ውስጥ የእግዚአብሔር ፈቃድና ሐሳብ መኖሩን ሊያጠይቀን በቃና ዘገሊላ ቅዱስ እግዚአብሔር ተገኝቶ በፈቃዱና በእናቱ ልመና ውኃውን ወደ ወይን መለወጡን ተመልክተናል፡፡ (ዮሐ. ፪)
በዚህ የጋብቻ ኪዳን ውስጥ ወንድና ሴትን የሚያመለክተው የሥራ (የግብር) ድርሻን ነው፡፡ በሥነ ፍጥረት ግን ሰው ሰው ነው፡፡ በወንድና በሴት መካከል የሥራ ድርሻ ልዩነት እንጂ የሰውነት ጸባይ ልዩነት የለም፤ ስለዚህ በጋብቻ ኪዳን ውስጥ ወንድና ሴትን አንዱ ይበልጣል፤ አንዱ ያንሳል አንልም፤ ስለምን ብንል በነገረ መለኮት አስተምሮ አካላዊ የሆነው ወንድነትና ሴትነት ከጾታ በእጅጉ ስለሚለያይ ነው፤ ጾታ ሲሆን የሥራ ድርሻ ሲያመለክት በአካላዊ ጸባዩ ወንድ በአዳም አንቀጽ ካህን ሆኖ በምሳሌው ክርስቶስን ይወክላል፡፡
አዳም ለምን በካህን እንመስለዋለን? ብንል (ዘፍ. ፩፥፳፮-፳፯) ይገዛ ዘንድ ገነትን ይጠብቃት፣ ይንከባከባት ዘንድ፣ ለእንስሳትና አራዊት ስምን ያወጣም ዘንድ እግዚአብሔር ሥልጣን፣ ሰጥቶታልና ነው፡፡ ለእንስሳት የሚያወጣው ስምም የእግዚአብሔርን ስምና ክብር የሚገልጥ ነበር፤ የእግዚአብሔርን ስም የሚገልጥ ደግሞ ካህን ይባላል፡፡ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት በመሆኑ የወንድ ምሳሌው ይሆናል፡፡ ሴትን ስንመለከት በአንቀጸ ሔዋን የሕያዋን (ሕይወት ያላቸው ሰዎች ሁሉ) እናት ሆና እናገኛታለን፤ ይህም ሕይወትን በሚሰጥ በመንፈስ ቅዱስ እና በጥምቀት በምትወልደን ቤተ ክርስቲያን ትመሰላለች፡፡ ስለምን ቢሉ ሕይወትን የምትሰጥ ሴት (ሔዋን) ሞትን ለልጆቿ ብትሰጥም በዳግማዊት ሔዋን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወትን ማግኘት ችለናልና፡፡
ለምድር ልጅን የምትወልድ (የምታስገኝ) ሴት ናት፤ ሕይወትን በማስገኘት በጥምቀት በመውለድ ቤተ ክርስቲያንን ትመስላለች፡፡ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል መበላለጥ እንደሌለ ሁሉ በወንድና በሴት መካከል መበላለጥ የለም፡፡ በዚህም የነገር መለኮት ትምህርት ወንድ በእግዚአብሔር ወልድ ተመስሎ ሴት በቤተ ክርስቲያን ተመስላ ባልና ሚስትን እንደ ራስና አካል አድርጋ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ራስ አካልን እንዲንከባከብ፣ አካል ደግሞ የራስ ረዳት እንዲሆን ሐዋርያው እንዲህ በማለት አስተማረን፤ “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ራስም ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፫)
“ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል፤ ይከባከበውማል።” ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ። በሚሉ ኃይለ ቃላት (ኤፌ.፭፥፳፭-፴፫) ወንድ ምን ያህል ሚስቱን መውደድ እንዳለበት በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል፡፡
ይቆየን!