ገብርኄር /ለሕፃናት/

መጋቢት 14/2004 ዓ.ም.

በቴዎድሮስ እሸቱ

 

ደህ12ና ሰነበታችሁ ልጆች? እንዴት ናችሁ? በጾሙ እየበረታችሁ ነው አይደል? ጎበዞች፡፡ ዛሬ ስድስተኛው ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ሳምንት ገብርኄር ይባላል፡፡ ገብርኄር ማለት ልጆች መልካም አገልጋይ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን ክርስቶስ ስለመልካም አገልጋይ ያስተማረው ትምህርት ይነገራል፡፡ ይህን የተመለከተ ምስጋናም ይቀርባል፡፡

 

አንድ ባለጸጋ አገልጋዮቹን ያስጠራቸውና ለአንኛው 5 መክሊት ለሁለተኛው 2 መክሊት ለሦስተኛው ደግሞ 1 መክሊት ወርቅ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያም እኔ እስክመጣ በዚህ ወርቅ በመነገድ ተጠቀሙ ብሏቸው ወደሩቅ ሀገር ይሔዳል፡፡ ልጆች መክሊት የወርቅ መለኪያ /መስፈሪያ/ ነው፡፡

ይህም ባለጸጋ ከሔደበት ሀገረ ብዙ ከቆየ በኋላ ወደ ሀገሩ ይመለስና ወርቅ የሰጣቸውን ሰዎች በመጥራት ስለንግዳቸው1212 ይጠይቃቸዋል፡፡ አምስት የተሰጠው አገልጋይ ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ አለው፡፡ ጌታውም አንተ መልካም አገልጋይ ነህ ወርቁን ከነትርፉ ውሰድ ወደጌታህም ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተሰጠውም ሌላ ሁለት መክሊት እንዳተረፈ ተናገረ ጌታው እሱንም አንተም መልካም አገልጋይ ነህ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሀለሁ ወደጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ በመጨረሻም አንድ መክሊት የተሰጠው አገልጋይ መጣ እንዲህም አለ “ጌታዬ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ ያልበተንከውን የምትሰበስብ ክፉ ጌታ መሆንህን አውቃለሁ ስለዚህ ሌቦች እንዳይሠርቁኝ አታላዮች እንዳይቀሙኝ ብዬ መክሊትህን ቀብሬ እስክትመጣ አስቀምጨዋለሁ አሁንም እንካ ይኸው አንድ መክሊትህ” ብሎ ሰጠው፡፡ ጌታውም “አንተ ክፉ አገልጋይ መቼ ነው እኔ ያልዘራሁትን ያጨድኩት፣ ያልበተንኩትን የሰበሰብኩት አሁን ወርቁን ተቀበሉትና ለባለ አምስት መክሊቱ ስጡት እሱን ደግሞ ወደ ዘለዓለም ሃዘንና መከራ ወዳለብት ወደጭለማው አውጥታችሁ ጣሉት” አላቸው፡፡ አገልጋዮችም ይህንን ክፉ አገልጋይ ወደ ጭለማው አውጥተው ጣሉት፡፡

 

ልጆች እንግዲህ በዚህ ሳምንት የሚነገረው ታሪክ ይህ ነው፡፡ እናንተ ክፉ አገልጋይ እንዳትባሉ ተግታችሁ ሥሩ በሃይማኖት ጠንክሩ እሺ! መልካም ደህና ሰንብቱ፡፡