‹‹ድኀነት››
የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት ያጣውን የተፈጥሮ ጸጋ ክብር በአዲስ ተፈጥሮ እንደገና ለመታደል መብቃቱን ለመግለጽ የሚነገር ልዑል ቃል ‹‹ድኀነት›› ነው፡፡ ድኀነት የሚለው ቃል አዳም በክርስቶስ የታደለውን የሕይወተ ሥጋና ሕይወት ነፍስ፣ በረከተ ሥጋና በረከተ ነፍስ ጸጋ ወይም በሌላ አነጋገር የሞተ ሥጋና የሞተ ነፍስ ድቀት የደረሰበት አዳም በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘው ትንሣኤውና ሕይወት የሚገለጽበት ሕያው ቃል ነው፡፡ ይህ ምሥጢር በብዙ ዓይነት ገጸ ንባብ የተገለጠው የተላያየ ትርጉም ስላለው አይደለም፡፡ ሁሉም ዓይነት ገጸ ንባብ ሲተረጉምና ሲመሠጠር የሚያስተላልፈው መልእክት አንድ ነው፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ ወደ ጥንተ ተፈጥሮ ደረጃ መመለስ፣ ከብልየት መታደስ፣ በአዲስ ሕይወት የተፈጥሮ ጸጋን መልበስ እና የመሳሰሉትን ናቸው፡፡ (ሉቃ. ፪፥፲፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፪፤ የሐ. ፳፥፴-፩፤ ፲፩፥፳፭-፳፰)
የሰው ልጅ በፈጣሪው አርአያና አምሳል የተፈጠረ፣ ሕያዊት፣ ለባዊት፣ ነባቢት፣ ነፍስ ያላቸው፣ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሑ ልቡና የተሰጠው /መቅድመ ወንጌል/፣ መንፈሰ አእምሬ፣ መንፈሰ ለብዎ፣ መንፈስ ጥበብ፣ መንፈሰ ምክር፣ መንፈሰ ኃይል፣ መንፈሰ ረድኤት፣ መንፈሰ ፈሪሃ እግዚአብሔር ጸጋን በስፋት የታደለ ታላቅ ፍጡር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ተፈጥሮ ‹‹አታድርግ›› ከሚል አምላካዊ ሕግና ትእዛዝ ጋር ኑሮውን የጀመረ ፍጡር የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ዓይነት ኑሮውን የጀመረው ልጅ ከጊዜ በኋላ እንዳኖሩት አልተገኘም፡፡ (ኢሳ፤ ፲፩፥፩)
ቀደም ብሎ የተገለጸው ዓይነት ተፈጥሮና ኑሮ የነበረው የሰው ልጅ ‹‹አታድርግ›› የተባለውን በማድረጉና በክፉ ምኞት የዲያብሎስን ዓይነት ስሕተት ስለተሳሳተ የዲያብሎስን ዓይነት አወዳደቅ ወደቀ፤ በዚህ ስሕተቱና ድቀቱም በኅሊና፣ በሥጋ እና በነፍስ ሞተ፡፡
የሰው ልጅ ስለፈጸመው ጥንተ አብሶ ከዲያብሎስ ያላነሰ በደል በመፈጸም የዲያብሎስን ዓይነት አወዳደቅ ቢወድቅም እንደ ዲያብሎስ ዕሩቅ ውዱቅ ሆኖ አልቀረም፡፡ በተፈጥሮ የታደለውን ጸጋ ክብር እንደተገፈፈና የዲያብሎስን አወዳደቅ እንደወደቀ አልቀረም፤ አውቆ በድፍረት፣ ሳያሳውቅ በስሕተት በሠራው ኃጢአት ክፉኛ ስለተጸጸተ በቃል ኪዳን የተደገፈ ተስፋ ድኀነት ተሰጠው፡፡ ይህም የድኀነት ተስፋ ‹‹ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ኖኅ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ኪዳ ሕይወት፣ ኪዳነ ምሕረት፣ ኪዳነ በረከት ማለት ነው፡፡ (የሐዋ. ፫፥፲፱-፳፭፤ ገላ. ፬፥፬፤ዘፍ. ፱፥፰)
ከድቀተ አዳም አስከ ክርስቶስ ድረስ ያለው ዘመን የተስፋ ዘመን ክርስትና ራሱ የትንሣኤ ሙታንና የመንግሥተ ሰማያት ተስፈኞች ዘመን እንደመሆኑ መጠን በእርግጥ የተስፋ ዘመን ሊባል ይችላል፡ ሆኖም የሐዲስ ኪዳን ሕዝብ የመንግሥተ ሰማያት ተስፈኛ ለመሆን የበቃው በክርስቶስ በተፈጸመው የድኀነተ ዓለም ተግባር ስለሆነ ዘመነ ተስፋ የሚለው ቃል ትክክለኛ መጠሪያ ሊሆን የሚችለው ከአዳም እስከ ክርስቶስ ለነበረው ዘመን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደራሲ ‹‹ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፣ ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል›› ሲል የተናገረው ቃል የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሐቅ ነው፡፡ ለዚህም የምስክርነት ቃል ምንጩ ቅዱስ መጽሐፍ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ (የሐዋ. ፫፥፲፱፤ ገላ. ፬፥፬;)
ዛሬ በዓለም ዙሪያ ሰላም የጠፋው፤ ችግር፣ መከራ፣ ቸነፈርና ስቃይ የበዛው መልካሙ እረኛችንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላጣን ነው፤ ወደ እርሱም ለመቅረብ የልባችን ደንዳናነት እና በትዕቢት መታወር እንደ ብረት ሰንሰለት አጥረውናል፡፡ ሥጋዊ ምቾትን ብቻ እያሰብን የምንኖር ሰዎች እንደ ኮሮና ዓይነት መድኃኒት የለሽ ወረርሽኝ ሲከሰት መፍትሔ ብለን የምናስበው በዘመናዊ የሕክምና መፈወስን ሆኗል፡፡ ነገር ግን ይህን በሽታ ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕክምና አገልግሎትም ሆነ ባለሞያዎች ባለመገኘታቸው ብዙ ሺዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለማስቆም መመሪያዎቹ እየተተገበሩና ጥንቃቄ እየተወሰደ ቢሆንም የመገናኛ ብዙኃኖች አሁንም ድረስ የበሽተኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ይህም እኛ የያዝነው አካሄድም ሆነ እየተጓዝንበት ያለው መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ያሳያል፤ ድኀነትን ሥጋንና ድኀነተ ነፍስን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና፡፡
የድኀነተ ዓለም ተግባር የፈጸመው ሕማሙንና ሞቱን የኃጢአት መደምሰሻ የዲያብሎስና የሞት ድል መንሻ የመንግሥተ ሰማያትና የዘለዓለማዊ ሕይወት መውረሻ በማድረግ ነው፡፡ እግዚአብሔር የድኀነት አምላክ ተብሎ የሚጠራው በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በፈጸመው የድኀነተ ዓለም ተግባር ብቻ አይደለም፡፡ በኪዳነ ናኅ እንደተገለጠው ከዚያም በፊት ለሰው ልጅ ኑሮ ደኅንነት ይፈጽመው በነበረ የትድግና ተግባር የደኀነት አምላክ መሆኑን ለሰው ልጅ በተግባር ገልጿል፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን የፈቀደው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ሕይወትነት፤ ሞተ ሥጋ በትንሣኤው ሥጋ፣ ሞተ ነፍስ በሕይወተ ነፍስ ተደምስሷል፡፡ የዚህ ድኅነት ባለቤት ለመሆን የሚቻለውም በትምህርት ድኀነተ ለሰው ልጅ ሊታደል የሚችልበትን ምሥጢር በመፈጸም ነው፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ኢሳ.፳፮፥፲፤ ፩ቆሮ.፲፭፥፲፭፤ ዮሐ.፲፪፥፴፪፤ ዕብ. ፲፪፥፲፰-፳፭)
በዚህም እኛ በክርስቶስ ክርስቲያን የምንሆን የዕለተ ዐርብ ፍጡሮቹ በድኀነት ጎዳና እንድንራምድ ወደ አምላክችን መመለስ አለብን፤ እርሱ ለበጎቹ እንደ መልካም እረኛ ነውና፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ የበጎች እረኛ እኔ ነኝ›› እንዲል.፤ በጨለማና በሞት ጥላ ወስጥ ለምንኖር ለእኛም ብርሃኑን ይገልጥል ዘንድ እግሮቻችንን ወደ ሰላም መንገድ አቅንቶልናል፡፡የሰላሙንም መንገድ እንጓዝ ዘንድ እንደ እርሱ ሁሌም መስቀሉን ልንሸከም ይገባል፡፡ (ዮሐ. ፲፥፮፤ አንቀጸ ብርሃን ፲፩)