ደብረ ዘይት፡- ዳግም ምጽአት
መጋቢት፤ ፳፻፲፮ ዓ.ም.
ዘመነ ሥጋዌ የጌታችን መገለጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትንበት፣ ይህም ከሰማያት ወርዶ እኛን ለማዳን ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው በመሆን ዓለምን ያዳነበት ነው፡፡ እርሱ እንደ ሰው ተወልዶ፣ እንደ ሕፃናት በጨርቅ ተጠቅልሎ፣ ጡት ጠብቶ፣ በየጥቂቱ አድጎ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በእግር ተመላልሶ፣ እንደ ሰው ተርቦና ተጠምቶ፣ ኀዘን መከራን ተቀብሎ በፍጹም ፍቅሩ አድኖናል፡፡
ፈውሰ ነፍስ በሆኑት ትምህርቶቹ ዓለምን አጣፍቶ፣ አዳኝ በሆኑት እጆቹ ልምሾዎችን፣ ድዊዎችንና አንካሶችን አድኖ፣ ጎባጣን አቅንቶ፣ የዕውራንን ዓይን አብርቷል፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑንም በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቀ መለኮት እጅ ተጠምቆ አስመስክራል፡፡ ብርሃነ መለኮቱ በታየበት በደብረ ታቦር ተራራም አምላክነቱን ገልጧል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፫-፲፯፣፲፯፥፩-፰)
ይህን ሁሉ ያደረገው ሰዎች አምላክነቱን አውቀን፣ ከሰማየ ሰማያት የወረደውና መከራን ተቀብሎ በመስቀል ላይ የሞተው ለእኛ ድኅነት መሆኑን እንዲሁም ድንቅ ሥራውን የፈጸመበት ይህን ጥበቡን ተረድቶና፣ የእጁን ሥራ፣ የቃሉን ተእምራት ያመነውን ሁሉም እንደሚድነን ሲያበስረን ነው፡፡ በተጓዳኝም በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ዳግም ምጽአቱና ምልክቶቹ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በዝርዝር በደቀ መዛምርቱ በኩል አሳውቆናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ (ማር.፲፫፥፫-፴፯)
“በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በምኵራብም ትገረፋላችሁ፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።
ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ፤ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።
በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።
በዚያን ጊዜም ማንም እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል፤ ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።ሰ ማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።
ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፤ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮህ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና፤ ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።”
ወንድሞች ሆይ! ጊዜ ዋጋው የላቀ በመሆኑና የጌታችንንም የፍርድ ቀን የሚያውቅ አለመኖሩን በቅዱስ ወንጌል ስለተነገረን በበጎነት፣ በቅንነትና በእምነት ጽናት ሆነን በጸሎት እንዲሁም በጾም፣ በትጋትና በክርስቲያናዊ ምግባር በመታነጽ በሃይማኖት ልንኖር ይገባናል፡፡ ዘወትርም ለሕጉ በመገዛትና ትእዛዙን በመፈጸም እስከ መጨረሻው ጸንተን “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና” ልንባል ያስፈልጋል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፬‐፴፮)
ዕድል ፈንታችን መንግሥተ ሰማያት መውረስ ይሆን ዘንድም በምድራዊ ሕይወታችን መከራ ሥቃይ ተቀብለንና ለነፍሳችን መሥዋዕት መክፈል ይገባል እንጂ “እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና” ከመባል ይሠውረን፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፵፩‐፵፫)
የአምላካችን ቸርነትና ረድኤት አይለየን፤ አሜን!