ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተ ክርስቲያን – የመጀመርያ ክፍል
በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹‹ወኮነት ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተ ክርስቲያን እስመ አስተጋብአት እም ብሉይ ወሐዲስ፤ ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነች፤ ከብሉይና ከሐዲስ ሰብስባለችና፡፡›› ምክንያቱም ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ሙሴና ኤልያስን፤ ከሐዲስ ኪዳን ሐዋርያት ጴጥሮስን ያዕቆብን፣ ዮሐንስን ከመምህራቸው ከክርስቶስ ጋር ሰብስባለችና፡፡ ደግሞም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በነቢያትና ሐዋርያት መሠረትነት ነውና፡፡ ‹‹እስመ ተሐነጽክሙ ዲበ መሠረተ ነቢያት ወሐዋርያት እንዘ ክርስቶስ ርዕሰ ማዕዘንተ ሕንጻ፤ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ደንጋይ ክርስቶስ ነው፤›› እንዲል (ኤፌ. ፪፥፳)፡፡
በዓለ ደብረ ታቦር
እንደሚታወቀው በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ በዓለ ደብረ ታቦር ነው፡፡ በዓሉ ከዐበይት በዓላት የተመደበበት ምክንያትም በደብረ ታቦር የተገለጸው ምሥጢር ድንቅ በመኾኑ ነው፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ አንድ አንድ ጊዜ ለዅሉም፤ አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ በከፊል ምሥጢራትን ገልጾላቸዋል፡፡ ከእነዚህ ምሥጢራትም የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፤ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን በቤተ አልዓዛርና በቤተ ኢያኢሮስ፤ ምሥጢረ ቍርባንን እንደዚሁ በአልዓዛር ቤት፤ ነገረ ምጽአትን በደብረ ዘይት ገልጿል (ማቴ. ፱፥፳፫፤ ፳፮፥፳፮፤ ዮሐ. ፲፩፥፵፫)፡፡
ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት ምሥጢራት መካከል ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንና ምሥጢረ ቊርባንን ዅሉም ደቀ መዛሙርት ያዩ ሲኾን ነገረ ምጽአትን ግን በከፊል ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ አራተኛ እንድርያስን ጨምረው ተረድተዋል፡፡ የደብረ ታቦርን ምሥጢር ከዚህ ልዩ የሚያደርገው ከሐዋርያት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ብቻ መገኘታቸው፤ ከነቢያት ደግሞ ሙሴና ኤልያስ መጨመራቸው ነው፡፡ ከጌታችን ዘጠኝ በዓላት አንዳንዶቹ በተፈጸመው ድርጊት የተሰየሙ ሲኾን ከፊሎቹ ድርጊቱ በተፈጸመባቸው ቦታዎች ተሰይመዋል፡፡ በድርጊቱ የተሰየሙት ፅንሰት፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገት ሲኾኑ ሁለቱ ሆሣዕና እና ጰራቅሊጦስ ደግሞ ድርጊትንና ስምን አስተባብረው የያዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ዅሉ ተለይቶ ደብረ ታቦር ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ ተሰይሟል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዅሉም ምሥጢራት ነገረ ምጽአቱንና ምሥጢረ መንግሥቱን በተራራ ላይ ገልጿል፡፡ ነገረ ምጽአትን በደብረ ዘይት የገለጸበትን ምክንያት ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ለዅሉም ጊዜ አለው›› እንዳለው ለጊዜው ትተነው ወደ ደብረ ታቦር እንመለስ፤ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት፤ ነቢያት ሊያዩት የተመኙትን ያዩበት ነቢያትና ሐዋርያት በአንድነት የተገናኙበት፤ ተገናኝተውም እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የመሰከሩበት፤ እግዚአብሔር ወልድ በክበበ ትስብእትና በግርማ መለኮት የተገለጠበት፤ እግዚአብሔር አብ በደመና ‹‹የምወደው፣ ለተዋሕዶ የመረጥኩት በእርሱ ህልው ኾኜ የምመለክበት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤›› ብሎ የመሰከረበት፤ መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ የወረደበት፤ እግዚአብሔር አንድነቱን፣ ሦስትነቱን የገለጠበት እነ ቅዱስ ጴጥሮስ ለመኖር የተመኙት ደብረ ታቦር ነው፡፡ በዓሉ የጌታችን ሲኾን በስሙ ደብረ ታቦር ተብሏል፡፡ ይህ በዓል ያን ጊዜ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ወደ ተራራው ሲወጣ፣ በተራራው ራስ ላይ ምሥጢሩን ሲገልጥላቸው፣ አእምሮአቸውን ሲከፍትላቸው፣ ከግርማው የተነሣ ፈርተው ሲወድቁና ሲያነሣቸው በዐይነ ሕሊናችን የምንመለከትበት በዓል ነው፡፡
ጌታችን ወደ ደብረ ታቦር የወጣው መቼ ነው?
ወንጌላዊያኑ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን ለመግለጥ ወደ ደብረ ታቦር የወጣው ደቀ መዛሙርቱን በቂሣርያ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?›› ብሎ በጠየቃቸው በሰባተኛው ቀን እንደ ኾነ ጽፈዋል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ በስምንተኛው ቀን ነው ይላል፡፡ (ማቴ. ፲፯፥፩-፰፤ ማር. ፱፥፪-፰፤ ሉቃ. ፱፥፳፰)፡፡ ነገሩ እንዴት ነው? ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማቴዎስ በጠቀሰው በሰባተኛው ቀን መኾኑን በትርጓሜያቸው አስቀምጠዋል፡፡ ታዲያ ስለ ምን ስምንት አለ? የሚለውን ሲያትቱ (ሲያብራሩ) ስምንት ያለው ሰባት ሲል ነው ብለው ተርጕመውታል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሳምንት የሚባለው ሰባት ቀን ነው፡፡
ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ዕለተ ሰንበት ሲናገር ‹‹ኦ ቅድስት ንዒ ኀቤነ ለለሰሙኑ ከመ ንትፈሣሕ ብኪ ለዓለመ ዓለም፤ ቅድስት ሆይ፣ በየሳምንቱ ወደኛ ነዪ፤ ለዘለዓለሙ በአንቺ ደስ ይለን ዘንድ፤›› በማለት መናገሩ ሰሙን ማለት ሳምንት እንደ ኾነ ያጠይቃል፡፡ ሳምንት ማለት ደግሞ ሰባት ቀን ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ሉቃስ በስምንተኛው ቀን ያለው በሳምንቱ (በሰባተኛው ቀን) ሲል ነው፡፡ በሌላ መልኩ ማቴዎስ በሰባተኛው ቀን ሲል ሉቃስ በስምንተኛው ቀን ማለቱ የወጡበትንና የተመለሱበትን ቈጥሮ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ መጽሐፍ የጎደለውን ሞልቶ፣ የሞላውን አትርፎ መናገር ልማዱ ነው፡፡ ይህንም በሚከተሉት ኃይለ ቃላት መረዳት እንችላለን፤
- ሰሎሞን ‹‹ወነበርኩ ውስተ ከርሠ እምየ ዐሠርተ አውራኃ ርጉዐ በደም፤ በእናቴ ማኅፀን በደም ረግቼ ዐሥር ወር ነበርኹ፤›› ብሏል (ጥበ. ፯፥፪)፡፡ የእናቶች እርግዝና ጊዜ ዘጠኝ ወር ኾኖ ሳለ ጠቢቡ ዐሥር ወር ተቀመጥሁ አለ፡፡ ይህን ያኽል ረጅም ቀን የመጨመር ልማድ ያለው መጽሐፍ ‹‹በስምንተኛው ቀን›› ቢል ብዙ የሚደንቅ፣ የሚጣረስም አይደለም፡፡ የሚጣረሰው ወይም የሚጋጨው የእኛ አእምሮ ነው፤ የዕውቀት ማነስ ስላለብን፡፡
- ‹‹ወበጽሐ ወርኃ ለኤልሳቤጥ፤ የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ወራት ደረሰ›› (ሉቃ. ፩፥፶፯) ሲል ቀን አልጠቀሰም፡፡ ሰው የሚወለድበት ቀኑ የታወቀ ስለ ኾነ ነው፡፡
- ስለ እመቤታችን ሲናገር ‹‹በዚያ ሳሉም የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤ የበኵር ልጅዋንም ወለደች›› ብሏል (ሉቃ. ፪፥፮)፡፡ ከአንድ በላይ የኾኑ ወሮች ‹‹ወራት›› ይባላሉ፡፡
ይህ ዅሉ የመጻሕፍት ቃል መጽሐፍ ሲያሻው ጠቅልሎ፣ ሲፈልግ ዘርዝሮ፣ አስፈላጊ ሲኾን ደግሞ በአኀዝ ወስኖ፣ ደግሞም አጕድሎ፣ እንደዚሁም ሞልቶ ሊናገር እንደሚችል ያስረዳናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማርያም ማኅፀን ያደረው ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲኾን መጽሐፍ ‹‹ተፀውረ በከርሣ ፱ተ አውራኃ፤ ዘጠኝ ወር በማኅፀኗ አደረ›› በማለት አምስት ቀን አጕድሎ ሲናገር እናገኘዋለን፡፡ ከዚህ አንጻር ሉቃስም አንድ ቀን ጨምሮ ተናግሯል፡፡ መጨመርም ማጕደል የመጻሕፍት ልማድ ነውና፡፡
ለዚህ ምሥጢር ደብረ ታቦር ለምን ተመረጠ?
፩ኛ ምሳሌነት ስላለው
የታቦር ተራራ፣ የቤተ ክርስቲያን፤ የወንጌል እና የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ አንደኛውን ምሳሌ ከላይ የተመለከትን ሲኾን ሁለተኛው ምሳሌ አበው በትርጓሜአቸው እንዲህ አብራርተውታል፤ ተራራ ሲወጡት አድካሚ ነው፤ ከወጡት በኋላ ግን ዅሉንም ቁልጭ አድርጎ ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፤ ወንጌልም ሲማሯት፤ ሲያስተምሯት ታደክማለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኀጢአትን፤ እውነትንና ሐሰትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለችና፡፡ በሌላ መልኩ ከተራራ ላይ ያለ ሰው ጠላቱን በቀላሉ በአፈር በጠጠር ድል መንሳት፣ ፍትወታት እኩያትን ማሸነፍ ይችላል፡፡ ከተራራ ላይ መሰወር እንደማይቻል በወንጌል ያመነ ሰውም ተሰውሮ አይቀርም፤ በመልካም ሥራው ለዅሉም ይገለጣል፡፡ በሦስተኛውም ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ከነቢያት ሁለቱ ከሐዋርያት ሦስቱ በተራራው ላይ መገኘታቸው መንግሥተ ሰማያት ነቢያትም ሐዋርያትም በአንድነት የሚወርሷት መኾኗን ያስረዳል፡፡ ከደናግላን ኤልያስና ዮሐንስ፣ ከመዓስባን (በሕግ ጋብቻ ኖረው ሚስቶቻቸው የሞቱባቸው ወይም ትዳራቸውን የተዉ) ሙሴና ጴጥሮስ በተራራው ላይ መገኘታቸውም መንግሥተ ሰማያት ደናግላንም መዓስባንም መልካም ሥራ ሠርተው በአንድነት የሚወርሷት እንደ ኾነች ይገልጻል፡፡
ይቆየን