“ደስታ ከጻድቃን ጋር ትኖራለች” (ምሳሌ ፲፥፳፰)
ቀሲስ ኃይሉ ብርሃኑ
ግንቦት ፲፫፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
በዚህ ርእስ ሥር የምንመለከተው “ደስታ ምንድን ነው? ጻድቃን እንዴት ደስታን አገኙና እኛስ ደስታን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ነው።
ደስታ ምንድን ነው?
በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ደስታ ማለት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ራሱ እግዚአብሔር ደስታችን የሆነ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” እንዳለ፡፡ (ፊልጵ.፬፥፬)
ሁል ጊዜ በጌታ መደሰት ማለት እግዚአብሔር በአጠቃላይ በሕይወታችን ለሚደርግልንና ላደረገለን ሁሉ በጽኑ እምነት መደሰት ማለት ሲሆን ሳይታወኩ በደስታም በሐዘንም የሚደሰቱት ደስታ ማለት ነው። “እኔም በደስታዬ ለዘለዓለም አልታወክም አልሁ” እንዳለ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት፡፡ (መዝ.፴፥፮)
እውነተኛ አማናዊ ደስታ ግን በጌታ የሆነ የማያቆረጥ የማይጠፋ ደስታ ነው።
በዚህ ባለንበት ዘመን ደስታችንን አርቀን፣ በሰማይ ላይ ሰቅለን፣ ለማውረድ እንደጨረቃ ተንጠራርተን የማንነካው ሆኖብናል። ከግል ሕይወታችንም ባለፈ በዙሪያችን የምንሰማው የዘረኝነት፣ የጦርነት፣ የስደት፣ የረኃብ… ወዘተ ወሬ፥ ኀዘንን እንጂ ደስታን የሚያሰሙ አይደሉም። መንኖ ጥሪትን፣ ከገዳም መግባትን፣ ከሰው መለየትን ገንዘብ ካደረጉ ቅዱሳን በቀር ደስታ ያለው የለም፡፡ በርእሳችን ላይ ጠቢቡ “ደስታ ከጻድቃን ጋር ትኖራለች” ብሎ የነገረን ለዚህ ነው። (ምሳሌ ፲፥፳፰)
ጻድቅና ጻድቃን ማለት ምን ማለት ነው?
ጻድቅ ማለት እውነተኛ ማለት ነው። በመሆኑም ጻድቅ እግዚአብሔር ነው። ይህንን በተመለከተ በመጽሐፈ ዕዝራ “አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ ፥ አንተ ጻድቅ ነህ” ይላል። (ዕዝ ፱፥፲፭) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሚያርፍበት ዕድሜ እንደ ደረሰ፥ባወቀ ጊዜ፥ መልካሙን ገድል እንደተጋደለ፥ ሩጫውን እንደፈጸመ፥ ሃይማኖቱንም እንደጠበቀ ከተናገረ በኋላ፦ “እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም” ብሏል። (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፮-፰)
ከሐዋርያው ንግግር የምንረዳው አካሄዳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ያደረጉ፥ ሃይማኖት ይዘው፥ ምግባር ሠርተው የተገኙ ሰዎች ጻድቃን እንደሚባሉ ነው። እነዚህም በነገር ሁሉ እውነተኞች ሆነው የተገኙ ናቸው። ወደ ርእሳችን እንመለስና “ደስታ ከጻድቃን ጋር ትኖራለች”*ስንል የክርስቲያን ደስታ ምድራዊ ደስታ፣ ወይም ተድላ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር በማመን የሚገኝ ደስታ ነው ማለታችን ነው። “የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ” እንደተባለው በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ያለውን የእውነትን ነጻነት የማወቅ ደስታ ነው፡፡ (ሮሜ ፲፭፥፲፫) “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” አላቸው” እንዲል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፴፪)
ደስታ ከክርስቶስ መከራ በምንካፈልበት ልክ የሚሰጥ ነው። “ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ኀሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።” (፩ኛ ጴጥ.፬፥፲፫)
ጻድቃን ከእግዚአብሔር ጋር በምድር የኖሩበት በሰማይ የሚኖሩበትን ደስታ ያገኙት ትእዛዙን በመፈጸማቸው ነው። “እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ” እንደተባለው ማለት ነው። (ዮሐ.፲፭፥፱-፲፩)
የክርስቲያኖችን ደስታን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
፩. ምድራዊ ደስታ፦ ምድራዊ ደስታ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ በምድር ላይ ብቻ የሚቀር እና
፪. ወደ ሰማያዊ ደስታ የሚያሻግር ቀጠይነት ያለው ደስታ ተብሎ ለሁለት ሊከፈል ይችላል። ይኸውም በምድር ላይ የሚቀር ደስታ በተሰጠን መክሊት፣ በተሰጠን ጸጋ በሀብታችን፣ በዕውቀታችን፣ በገንዘባችን፣በውበታችን… ወዘተ አማካኝነት በሚገኙ ዓለማዊ ደስታ የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ሳንቀርብና ንሰሐ ሳንገባ በጊዚያዊ ደስታ በመደሰት፣ ዘመናችን ፍጻሜ ሆኖ ሥጋና ነፍሳችን ተለያይቶ ስናልፍ ያለው ምድራዊ ደስታ ፍጻሜ ያለው ደስታ፣ በምድር የሚቀር እንለዋለን። ነገር ግን በተሰጠን ጸጋ/መክሊት ወጥተን ወርደን ብናተርፍበት “ወደ ጌታ ደስታ ግባ” የሚለውን ቃል በመስማት ወደ ዘለዓለማዊ የሚሻገር ደስታን እናገኛለን።
መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ “ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።” (ማቴ.፳፭፥፳፩) ፍጻሜ ወደ ሌላው ደስታ መግባት የሚቻለው እንደ ጻድቃን በዓለም ሳሉ መስቀሉን ተሸክሞ ክርስቶስን በመከተል መከራ መስቀለን በመታገሥ ይሆናል። “ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” እንዲል።፡ (ማር.፰፥፴፬)
በአጠቃላይ እነዚህ ሁለተኛውን ደስታ የያዙት ሥራቸው ይከተላቸዋል የተባሉ ጻድቃን “ደስታ ከጻድቃን ጋር ትኖራለች” የተባለላቸው ናቸው። እኛም ከእነዚህ ለመደመር የእነርሱን ፍኖት መከተል አለብን። ይልቁን በዚህ በበዓለ ኅምሳ በሕይወተ ነፍስ የዘለዓለም ሕይወት የምንኖርባት የመንግሥተ ሰማያት ኑሮ ምሳሌ በሆነች ወቅት ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን ሥራ ልንሠራበት ይገባል። ያን ጊዜ እኛም ከጻድቃን ቅዱሳን ጋር ሥራችን ይከተለናል። “ከሰማይም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል” ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።” (ራእ. ፲፬፥፲፫)
በምድርም በሰማይ ዘለዓለማዊ ደስታ የያዘች እመቤታችን ብቻ ናት። “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ኀሤት ታደርጋለች፤” (ሉቃ.፩፥፵፯) ይህ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር የሚገኝ ደስታ ነው። ይህም የማይለይ ደስታ፣ ዘለዓለማዊ ደስታ ይባላል።
በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም አጋንንት ተገዙልን ብለው ለተደሰቱት ፸፪ ሰዎች ጌታ እንዲህ አላቸው። “ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” (ሉቃ.፲፥፳) ትክክለኛው ደስታ በሰማይ መዝገብ ስማችን ስለተጻፈ መደሰት ነው።
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ጻድቅ “በአንተ ደስ ይለኛል፥ ኀሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ።” (መዝ. ፱፥፪) ከእግዚአብሔር ያገኘውን የማይቀማ ደስታ በማግኘቱ ቅዱስ ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር በመኖሩ ያገኘው ደስታ ስለሆነ “ለስምህ እዘምራለው” ብሎ እውነተኛ ደስታ እንዴት እንደሆነ ይነግረናል። “ደስ ያለው ቢኖር ይዘምር” እንደተባለው በደስታ በማመስገን ከእግዚአብሔር ጋር መኖርና የማንቀማ ደስታ ማግኘት እንችላለን። (ያዕቆብ ፭፥፲፫)
በዚህ ዓለም ያለ ደስታ ሁሉ ተለዋዋጭ ነው፡፡ መውደቅ መነሣት፣ ማዘን መደሰት ያለ ነው፡፡ ገንዘብ ያገኘ ይደሰታል፤ ሲያጣ ያዝናል፤ ምድራዊ ኑሮ ተለዋዋጭ ነው፤ ጊዜም ይመላለሳል፤ ይመሻል፤ ይነጋል፤ ምድር ላይ ቋሚ ነገር የለም።
ደስታ ግን ለእግዚአብሔር ለተገዙት እንደ ሕጉ ለሚኖሩት ግን አብራ ትኖራለችና በዓለም ሳለን ዓለምን በመናቅ እውነተኛ የእግዚአብሔርን ደስታ ይዘን እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!