“ይትሌዓል መንበሩ!” ቅዱስ ያሬድ

ኀዳር ፲፩፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

አሸናፊና ኃያል፣ ሁሉን ቻይ የሆነ የእግዚአብሔርን ገናንነትና እርሱን የሚመስል አምላክ እንደሌለ የሚያመለክት የስሙ ትርጓሜ “መኑ ከመ አምላክ፤ እንደ አምላክ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” የሆነ፣ የመላእክት ሁሉ አለቃ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በኅዳር ፲፪ የተሸሞበት ቀን “እግዚኡ ረሰዮ ለውእቱ ሚካኤል እምኵሎሙ መላእክት ይትሌዓል መንበሩ፤ ጌታው ሚካኤልን ከመላእክት ሁሉ መንበሩን ከፍ ከፍ አደረገው” እየተባለ ይከበራል፡፡

የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ አለቃ የሆነው መልእኩ ሚካኤል መላእክትን ሁሉ የሚያዝ ነው፡፡ መላእክት ደግሞ አለቃቸውን ያከብራሉ፤ ይታዘዛሉ፤ ከትእዛዙም አይወጡም፡፡ ሳጥናኤል በትዕቢቱ ከክብሩ ተዋርዶ ወደ ምድር ሲጣል አምላክ ቅዱስ ሚካኤልን በእርሱ ፈንታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ሾሞታል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይ ጭምርም ሾመው፡፡ … ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ፤ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፤ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ”  እንዲል፡፡ (ኢያ.፭፥፲፫)

ሠራዊተ መላእክት የሚያከብሩትንና የሚታዘዙለትን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እኛም እንደ ነቢዩ ኢያሱ እናከብረዋለን፤ እንታዘዘዋለን፡፡ መላእክትን ማክበርና መታዘዝ እንደሚገባ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክህን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፤ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት፤ አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፣ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፣ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፣ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ፣ መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና…፡፡” (ዘጸ.፳፫፥፳-፳፪)

በበዓሉ መታሰቢያ በኅዳር ፲፪ ቀን የክብር ባለቤት በሆነ በእግዚአብሔር ፈቃድ ክንፎቹን ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ኃጥአንንም ወደ አዲሲቱ ምድር ያወጣቸዋል፤ ይኸውም የመላእክት አለቃ የሚካኤል ሠራዊት ይሆናሉ፡፡ ይቅርታ የተደረገላቸውና ምሕረት አግኝተው በአንድ ጊዜ በክንፉ ያወጣቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በየዓመቱ በኅዳር ፲፪ ቀን እንዲህ እያደረገ እልፍ ነፍሳትን ያወጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ወገኖች የሆኑትን ሁሉ እንደ ሥራቸው ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አብ መጋረጃ ውስጥ ይገባል፤ በዚህች ዕለት ምድራዊትና ሰማያዊት ስለሆነች ምሕረቱም ከመንበሩ በታች ይሰግዳል፡፡ ስለውኃ ምንጮች፣ ስለ ወይን ቦታዎች፣ ስለ ምድር ፍሬዎች በምድርም ላይ ስለሚኖሩ ስለ ሰው ልጆች ነፍስ ሁሉ፣ ስለ እንስሳትም፣ ስለ ሰማይ ወፎችም፣ ስለ ባሕር ዓሣዎችም፣ በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ ሁሉ የምሕረት ባለቤት ከሆነ ከአብ ዙፋን በታች ሁልጊዜ በማመስገን ይሰግዳል፤ ልመናውንም እስኪሰማውና የምሕረትንም ቃል እስኪያስተላልፍለት ድረስ ከእግረ መንበሩ ሥር አይነሣም፡፡

ለዚህ ዓለም ምሕረትን የሚለምኑ ቅዱሳን መላእክትም በየዓመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን በእግዚአብሔር የዙፋኑ ዐውደ ምሕረት ዙሪያ ተሰብስበው ስለ ሰውና ስለ እንስሳትም ሁሉ ምሕረትን የሚለምን ቅዱስ ሚካኤል ከአብ መጋረጃ ውስጥ በወጣ ጊዜ ቸርና መሐሪ አብ ለቅዱስ ሚካኤል የሰጠው ልብሱን እነዚያ መላእክት ይመለከታሉ፤ ይቅርታን የማግኘት ምልክታቸው ነውና፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት በምድር ላይ ምሕረት እንደተደረገ ሰውንም እንስሳትንም ይቅር እንዳለ በዚህ ዓለምም የሚሆነውን ሁሉ አይተው ቅዱስ ሚካኤል በለበሰው ልብስ አምሳል ያውቁታል፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር እንደሚለው ይህ እጅግ የከበረ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል “ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋራ በመሆን ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ የሚያጽናናቸውና የዘወትር ጠባቂአቸው ሆኖ የሚራዳቸው እርሱ ነው፡፡” የብዙዎቹንም ቅዱሳን ገድል ስንመለከት የዘወትር ጠባቂያቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡

መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገውም ተአምር ይህ ነው፡- የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኰንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገልጦ ወደ ባለጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ነገር ግን ወደ ቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክበር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችን ጠርቶ አጠገባቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንድሰነጥቅ አዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ ፫፻ (ሦስት መቶ) የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፤ “ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ፤ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፤ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አጀጋጀላችሁ” አላቸው፡፡

እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፡፡ የከበረ ገናናው መልአክም “ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፤ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም” አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፡፡ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡

የመላእክት ሁሉ አለቃ የቅዱስ ሚካኤል ጥበቃው፣ ጸሎቱ፣ አማላጅነቱና ተራዳኢነቱ አይለየን፤ ከበዓሉ ረድኤት በረከት ይክፈለን፤ አሜን!

(ምንጭ፡ድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር)