ይቅርታ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መጋቢት ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በፈቃደ እግዚአብሔር የጀመርነው የዐቢይ ጾም ሁዳዴ (ጾመ ክርስቶስ) ስድስተኛውን ጨርሰን ስምንተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ላይ እንገኛለን፡፡ በአቅማችሁ በመጾም በጸሎት በርቱ!
ቤተ ክርስቲያንም ሄዳችሁ መንፈሳዊ ትምህርትን መማር አትዘንጉ! ዘመናዊ ትምህርታችሁንም ቢሆን በርትታችሁ ተማሩ! የሁለተኛው መንፈቀ ዓመት እየተገባደደ ነው! በርትታችሁ አጥኑ! ያልገባችሁን ጠይቁ! አብዛኛውን ጊዜያችሁን በትምህርታችሁ ላይ ትኩረት አደርጉ!፤ መልካም! በዛሬው ክፍለ ጊዜ “ይቅርታ” በሚል ርእስ እንማራለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይቅርታ ማለት የበደለን ሰው መልሶ አለመበደል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የሰደበን ሰው መልሶ አለመሳደብ፣ ክፉ ያደረገብንን ሰው እኛም እንደ እርሱ ክፉ አለማድርግ፣ በይቅርታ ማለፍ ይህ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አንዱ ነው፡፡ የበደለን ሰው ይቅር ማለት መታደል ነው፡፡
ልጆች! በማንኛውም ነገር ሁሉ ይቅር ባይ ከሆንን ሰዎችን በይቅርታ ስናልፍ እግዚአብሔር እኛንም ይቅር ይለናል፤ ይባርከናልም፤ “አባታችን ሆይ” እያልን በምንጸልየው ጸሎት ላይ ‹‹…እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል…ይቅር በለን…›› የሚል ኃይለ ቃል አለበት፡፡ (ማቴ.፮፥፲፪)
ታዲያ ልጆች! በዚህ ጸሎት ላይ እንደተጠቀሰው እና እኛም ዘወትር እንደምንጸልየው የይቅርታ ሰዎች መሆን አለብን፤ በቤት ውስጥ ካሉ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን አልያም ሰፈር ውስጥ ካሉ ወይም በትምህርት ቤት ከምናውቃቸው ጓደኞቻችን ጋር በአንዳንድ ነገር ልንጣላ (ላንግባባ) እንችላለን፤ ጥልና ግጭትም የሚያስነሡ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ! እኛ ከሆንን በደለኞች ይቅርታን መጠየቅ አለብን፤ ወይም እኛ ተበድለን (አስቀይመውን) ከሆነ ይቅርታን ማድረግ አለብን፤ ቂም መያዝ አይገባም፤ እነርሱ እንዳደረጉብን እኛም መጥፎ ነገር ማድረግ የለብንም፤ በይቅርታ ማለፍ አለብን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታ ማድረግ እንዳለብን አስተምሮናል፤ በመስቀል ላይ የተሰቀለልንም እኛን ይቅር ብሎን ነው፤ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ መከራ ለሚያደርሱበት ይቅርታን አድርጎላቸዋል፡፡ የምናምነው የክርስትና እምነት መሠረቱ የእርሱ ይቅርታ ነው፤ እኛም ሰዎችን ይቅርታ ብንልና መልካም ምግባር ቢኖረን እግዚአብሔር ያከብረናል፡፡ ሰዎችንም ወደ መልካም ምግባር እንዲመጡ ምክንያት መሆን እንችላለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በመጽሐፍ ቅዱስ ተበድለው ይቅርታን ያደረጉ፣ በዚህም ምግባራቸው ክብርን ያገኙ፣ ለክፉ ሰዎችም ከክፋታቸው መመለስ ምክንያት የሆኑ ብዙ አባቶቻችንና እናቶቻችን አሉ፤ ለአብነት እንዲሆነን የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ እንመልከት፡፡
ንጉሠ እስራኤል ቅዱስ ዳዊት
ዳዊት ማለት ‹‹ኅሩይ›› ማለት ነው። አንድም ‹‹ልበ አምላክ›› ማለት ነው። (ሐዋ.፲፫፥፳፪) አባቱ “ዕሤይ” እናቱ “ሁብሊ” ይባላሉ። ቅዱሱም ተወልዶ ጉልበቱ ከጸና በኋላ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ አድጓል። በወቅቱ የነበረው ንጉሥ ሳኦል ከጌታ ፈቃድ በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ቅብዐ መንግሥት እንዲቀባው አደረገ። (፩ኛ ሳሙ.፲፮፥፩-፲፫)
ከዚህ በኋላ በረድኤተ እግዚአብሔር ጎልያድን በአንድ ጠጠር ገደለ። በንሡ ሳኦልም ቅንዐት አድሮበት አንድ ቀን ሊገድለው ሦስት ሺህ ሠራዊት ይዞ ተከተለው፡፡ ከሠራዊቱ ተለይቶ ብቻውን በነበረ ጊዜ ዳዊት ካለበት ዋሻ ውስጥ ገባ። ጨለማ ነበርና ሰው መኖሩን አላወቀም።
አቢሳ የተባለ የዳዊት ጓደኛ “ጠላትህን አሳልፎ ሰጥቶሀልና ልግደለውን?” አለው። ዳዊትም “ተው በእግዚአብሔር መሢሕ ላይ እጅህን አታንሣ” በማለት አይሆንም አለው። እርሱ የልብሱን ዘርፍ በሰይፉ ቀዶ ያዘ። ሲወጣ ተከትሎ ወጥቶ “ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር እነሆ ዛሬ አሳልፎ ሰጥቶኝ ነበር። ነገር ግን የልብስህን ዘርፍ ከመቅደዴ በቀር ምንም ምን እንዳላደረግሁህ አንተ ታውቃለህ” ብሎ ቅዳጁን አሳየው። ሳኦልም ድምጹን ከፍ አድርጎ በማልቀስ ‹‹ልጄ ዳዊት ሆይ! እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፈንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ። ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ። አሁንም እነሆ! አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ አውቃለሁ›› አለው፡፡ (፩ኛሳሙ.ም ፳፬)፡፡ ከዚህም በኋላ ዳዊት በነገሠ ጊዜ ለልጆቹ እንዲራራላቸው ሳኦል ቃል አስገባው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? አይገርምም? ሊገድለው መጥቶ ይቅርታ አደረገለት! ከሳኦል የጠበቀው የእግዚአብሔር ምሕረትና ጥበቃው ነበርና ቂም አልያዘም፡፡ ምን ጊዜም ማሰብ ማስታወስ ያለብን የሰዎችን ክፉ ሥራ ሳይሆን እነርሱ ክፉ ሲያደርጉብን ከክፉ የጠበቀንን የእግዚአብሔርን ፍቅርና ምሕረት ነው፡፡ ያ ታዲያ ልባችን ቂም ከመቋጠር (ከመያዝ)፣ ክፉ ነገር ከማሰብ ያነጻልናል፡፡ ልባችን ንጹሕ ከሆነ የይቅርታ የፍቅር ሰዎች እንሆናለን፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹አቤቱ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ…›› በማለት እንደጸለየው ልባችን ከቂም በቀል ርቆ የይቅርታ ሰዎች እንድንሆን እኛም እንጸልይ! (መዝ.፶፥፲)
ነቢይ ኤልሳዕ
ኤልሳዕ የሚባል ነቢይ ነበር፤ አንድ ቀን ሦርያ የምትባልን አገር የሚመራው ንጉሥ ይዘውት እንዲመጡ ነቢዩ ኤልሳዕ ወዳበት ሥፍራ ላካቸው፤ ወታደሮቹም ነቢዩ ኤልሳዕ የሚያድረበትን ዋሻ ዙሪያውን ከበው ሊይዙት ሲጠብቁ ተመሪው (ደቀ መዝሙሩ) ግያዝ ጠዋት በሩን ከፍቶ ሲወጣ አያቸውና ደንገጦ ሮጦ ገብቶ ለነቢዩ ኤልሳዕ ነገረው፡፡ ነቢዩም እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ይበልጣሉ፤ አትፍራ” አለውና “እባክህ አምላኬ ለዚህ ብላቴና ዓይነ ልቡናውን አብራለት” ብሎ ተማጸነ፡፡
ቅዱሳን መላእክት ደግሞ ነቢዩ ኤልሳዕና ግያዝን እየጠበቋቸው ነበር፤ በጸሎት እንዳያስተውሎ ካደረጋቸው በኋላ ወደውጭ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ ወታደሮቹም “ኤልሳዕን” አሉት፤ “ኑ ላሳያችሁ” ብሎ ራሱ እየመራቸው ወደ እስራኤሉ ንጉሥ ወሰዳቸው (ማርኮ)፡፡
ንጉሡ ግን ልግደላቸው ብሎ ተነሣ፤ ነቢዩ ኤልሣዕ መልሶ “አይ እንዳትነካቸው፤ እንጀራ አብልተህ፣ ውኃ አተጥጠህ በሰላም ወደ አገራቸው ሸኛቸው” አለው፤ ሊገድሉት (ሊይዙት) የመጡትን ጠላቶቹን ይቅርታ አድርጎ በሰላም ወደ አገራቸው ሸኛቸው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ክፉውን በክፉ ሰይሆን በመልካም መመለስ አለብን፤ ሁል ጊዜ እኛ መልካም ከሆንን ከማንኛውም ክፉ ነገር እንዲጠብቁን ቅዱሳን መላእክትን አምላካችን እግዚአብሔር ይልክልናል፡፡
‹‹..ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና…›› እንደተባለው ይቅርታ ማድረግ ክብሩ ለራስ ነውና የይቅርታ ሰዎች እንሁን፡፡ (ማቴ.፮፥፲፬) ይቅር ባይ ሆነን ለክብር እንበቃ ዘንድ ማስተዋሉን ይስጠን!
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በትምህርታችሁ በርትታችሁ ትማሩ ዘንድ ይገባል! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ! ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!