የ ቆሙ መቃብሮች
መጋቢት 16 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ር ስምዓኮነ መላክ
ሰዎች ሲሞቱ ወይም ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሲለይ በክብር የሚያርፍበት ቦታ መቃብር ይባላል፡፡ መቃብር የሚላው ቃል የጎደጎደ ምድር ተብሎ ይተረጎማል፡፡ መዝ.14፥4፣ ኢሳ.22፥16 ሲዖልንም መቃብር ሲል ይገኛል፡፡ መትሕተ ታሕቲት ናትና፡፡
በማን ጊዜ እንደተጀመረ ባይታወቅም የሚቀበሩት በርስትነት በያዙት ቦታ ነበር ዘፍ.13፡፡ ያ ልማድ ሆኖልን ዛሬም በአዲስ ኪዳን የምንኖር ክርስቲያኖች እንደ አባቶቻችን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንቀበራለን፡፡ ስለምን ቢሉ ሥጋውን ደሙን የበላንበትና የጠጣንበት ብቸኛዋ ርስታችን በምድር ቤተ ክርስቲያናችን ናትና ነው፡፡
የቀደመው ርስት በዋጋ ይገዛ ነበር የዛሬዋ የምእመናን ርስት ቤተ ክርስቲያን ዋጋዋ የክርስቶስ ደም ነውና ደሙ በነጠበበት ቦታ ብቻ ስትሠራ ትኖራለች የምእመናን መቃብር በጌታ ደም የተገዛ እንጂ በሰቅል በተመዘነ ወርቅ የተገዛ አይደለም፡፡ ይህም የጌታ ደም ከሁሉ በላይ የከበረ እንደሆነ የምእመናንም መቃብር የከበረ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ለዛሬው ግን መቃብርን ያነሣነው ከአቤል ሞት ጀምሮ እስከ ጌታ ዳግም ምፅአት የማያቋርጥ ታሪክ ያለውን ጀግና ባለ ታሪክ መቃብርን ታሪኩን ለትውልድ ልናስተዋውቅለት ሳይሆን መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለቆሙ መቃብሮች የተናገረውን ቃል ማስታወስ ስለሚገባ ነው፡፡
መድኀኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት በጀመረ በመጨረሻው ዓመት በመቅደስ ተገኝቶ ለሕዝቡና ለደቀመዛሙርቱ ተናገረ፡- “ታላቅ ሸክም ማሰር ሰለሚችሉት መሸከም ግን ስለማይወዱት ስለ ጻፎችና ፈሪሳውያን ነበር የተናገረው፡፡
ለብዙዎች ብዙውን ኀጢአታቸውን በፍቅር የሸፈነው ጌታ ስለ ወንጀለኞች ሲጠየቅ ዝም የሚለው አምላክ ዮሐ.8፥11፣ ሉቃ.7፥47 በቤተ መቅደሱ አደባባይ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል የእነዚህን ታላላቅ የኦሪት አገልጋዮች በደል መዘርዘር ጀመረ፡፡ ተመክሮ ያልተመለሰን ሰው በአደባባይ ሊወቅሱት ይገባልና ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረው “ቢሰማህ ብቻውን አድርገህ ብቻህን ሆነህ ምከረው ባይሰማህ ካንተ ጋር ሁለት ሆናችሁ ምከረው….. እነርሱንም ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት” ማቴ.18፥15-17 ብሎ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይም የማይገባ ነገርን አድርገዋልና መገሰጽ ስለሚገባቸው በታላቅ ቃል ገሰጻቸው 1ቆሮ.5፥5 በመጽሐፍ ቃልህ እውነት ነው ተብሎ የተነገረለት መምህር ነውና ዮሐ.17፥17 እነርሱን ከውስጥ እስከ ውጭ ሊገልጹ በሚችሉ የተግሣፅ ቃላት ገሰፃቸው፡፡
በዘመኑ የነበሩ መምህራን አባቶቻቸው በሠሩት ኀጢአት የተጸጸቱ ለመመሰል አባቶቻቸው የገደሏቸው የነቢያትን መቃብር በኖራ እየለሰኑ ይሠሩና ያሠሩ ነበርና ያንኑ የሠሩትን ልስን መቃብር እየተመለከተ “የተለሰነ መቃብር የምትመስሉ” ሲል ተናገራቸው ይህ መቃብር ቢከፍቱት ለአፍንጫ የሚከረፋ ለዐይንም የሚከፋ ነገር አይታጣበትም፡፡ ሥጋው ተልከስክሶ አጥንቱ ተከስክሶ፣ እዡ ፈሶ ሲታይ ከውጭ የተለሰነ ውበቱን ያጠፋዋል፡፡ አብረውት እንዳይኖሩ ያስገድዳል በዚህ ረጅም ዕድሜው እንደላዩ ሁሉ ውስጡ አምሮ አያውቅም፡፡
ዘመኑን ሁሉ ሕይወት በሌላቸው ነገሮች የተሞላ ሆኖ ይኖራል እንጂ፡፡ ከዕለታት ባንዱ ስንኳን ንጹህ ነገር ክርስቶስን ቢያገኝ በሥጋ የሞተው በመንፈስ ግን ሕያው የሆነው ጌታ በትንሣኤ አሸንፎት ይዞ ማስቀረትም አይቻለው ብሎ ባዶውን ቀርቶ ይሄው እስከዛሬ ያለ ክርስቶስ ይኖራል፡፡ በእውነት ክርስቶስ በመቃብር መስሎ የተናገረበት ነገሩ ምን ይመስላችኋል? ለጊዜው የሚያመለክተው በዚያ ዘመን እስከ ክርስቶስ ወደ መቃብር መውረድ ድረስ በሰው ልጆች ላይ ሙስና መቃብር በሥጋቸው ወደ ሲዖል መውረድ በነፍሳቸው የግድ የነበረባቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡
በዘመኑ ባለ ጊዜ ሆኖ ሞት ውጦ መቃብር ተረግጦ የማስቀረት ኀይል ነበረውና፡፡ ያንን የሚገልጽ ሲሆን ፍጻሜው ግን ከውጭ ለሰው መልካም መስለው ስለሚታዩት ከውስጥ ግን ለእግዚአብሔር የሚመች በጎ ተግባር የሌላቸው ሰዎች እንዲገሰጹበት የተጻፈ ነው፡፡
ከውጭ ሲያዩአቸው ይጸልያሉ ይጾማሉ በጾምና በጸሎት ብዛት በገድልና በትሩፋት ጠውልገው ይታያሉ ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው ይምላሉ ሐሰቱን እውነት ያስመስላሉ በልባቸው የሌላውን የእግዚአብሔር ቃል አንሥተው ሲናገሩ በቂሳርያ ከተመሰገነው ጴጥሮስ ይበልጣሉ ዝምነታን በማያውቀው አንደበታቸውም ደግመውና ደጋግመው ስሙን ሲጠሩ ከጳውሎስ በላይ ሰባኪ ይመስላሉ ከውስጣቸው ግን እንዲህ አይደሉም፡፡ አመጽንና ሽንገላን ተሞልተዋል፡፡ በክፉ ምኞታቸውና አስቀያሚ በሆነው መሸታቸው የገዛ ነፍሳቸውን ገለው የገዛ ሥጋቸውን መቃብር አድርገው ቀብረዋል፡፡
በወይንና በአረቂ አልሰከሩም እንጂ በኀጢአት ሰክረው ወድቀዋል፡፡ ከመብልና ከመጠጥ እንጂ ክፉ ተግባራቸውን ከመተው የማይከለክሉ ይልቁንም በሞተ ሥራ የተሞሉ የቆሙ መቃብሮች ሆነዋል ስለዚህም መቃብር ውስጥ ያሉ ሙታንን ስንኳን የማይጠላ ጌታ ለተለሰኑ መቃብሮችም በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆሞ አሳምረው የለሰኑአቸው ልስን መቃብሮችን አሻግሮ እየተመለከተ ሁሉም ወደ መዳን የሚደርሱበትን ሕያው መልእክቱን አስተላለፉ፡፡
ወንድሜ ሆይ! አንተስ እንዳምን ነህ? ከውስጥህስ ምን ይገኛል? እግዚአበሔር አንተን ክርስቲያን አድርጎ ሐዋርያት ከሰበሰቧት አንዲት ማኅበር አባል ሲያደርግህ ምን ዓይነት ዓላማ እንደነበረው ታውቃለህ? ጨለማውን ዓለም ካንተ በሚወጣው የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ሊሞላው፣ ሕይወት አልጫ ለሆነችባቸው ማጣጫ ሊያደርግህ ማቴ.5፥12-13 በአሕዛብ መካከል ስሙን አሸክሞ ሊልክህ ሐዋ.9፥5 ዓላማ ስላለው ነው፡፡
የታመሙትንና በአጋንንት ተይዘው የሚሰቃዩትንም የሚፈውሳቸው ለምጻሞችን የሚያነጻቸው የረከሱትን የሚቀድሳቸው አንተን መሣሪያ አድርጎ እንደሆነ ታውቃለህ? አንተ ግን ለዚህ ዓላማ የተጠራህ መሆንህን የረሳህ ትመስላለህ፡፡ በአለባበስህና በከንፈርህ ብቻ እግዚአብሔርን ታመልካለህ ቀን ቆጥረህ ደማቅ በሆኑ የዓመትና የወር በዓላት ብቻ ለእግዚአብሔር ትዘምራለህ በሌላው ቀን ግን ትጠፋለህ ቃሉን ታውቃለህ እንደ ቃሉ መኖር ግን ተስኖሃል ከውጭ እንጂ ከውስጥ የሚታይ ነገር የሌለህ መጥፎ ሰው ሆነሃል፡፡ በክፉ መሻትህ እየወጋህ ሕያዊት ነፍስህን ገለህ የቆመ መቃብር ሆነሃታል፡፡
የማይታይ የተሰወረ የማይገለጥ የተከደነ አለ ይመስልሀልን? ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ቆይታ በኋላ ተከድኖ ይኖር የነበረ መቃብር መገለጡን በጌታ ደም ድብቅ ምሥጢሩን ከረጅም ዓመታት በኋላ ማጣቱን እንዳትረሳ ማቴ.27፥57 አንተ ሆይ! ሳይነግሩት የሰውን ማንነቱን የሚያውቅ ጌታ አንተንስ ቢገልጥህ? ዮሐ.2፥25 ከላይ የተለሰነ ኖራህን ቢያነሳብህስ? የቆመው መቃብርነትህ በጌታ ቃል የሞተውን ሳይሆን ሕያው የሆነ አልዓዛርን የሚያስገኝ ይመስልሃል? ብታምን የልቡናህን ትንሣኤ ዛሬ ታየ ዛሬም የተለሰነው መቃብር በር ላይ ቆሞ ይጣራል በውስጥህ ያሉት ሙታን አካሎችህ ዛሬ ድምጹን የሚሰሙበት ጊዜ ደርሷል እርሱም አሁን ነው ዮሐ.5፥25፡፡
የሚያሳዝነው ነገር ተዘግቶ ተለስኖ መቀመጡ ነው እንጂ የተከፈተ መቃብርማ ለብዙዎች የሚያስገርም ምስጢር ተገኝቶበታል እኮ! ሉቃ.24፥12 መላእክቱ የከበቡት የጌታ ደቀ መዛሙርት የጎበኙት ያ ቅዱስ መቃብር ባዶም ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ትንሣኤውን የሰበከ እርሱ ነበር፡፡
ወንድሜ ሆይ! የቆመ መቃብር ብትሆንም ለእግዚአብሔር ቃል የተከፈተ ልብ ካለህ እውነት እልሃለሁ ስላንተ ወዳንተ ወደመቃብሩ መላእክቱን ያዝልሀል ለደቀ መዛሙርቱ ሳይቀር የሚደንቅ ጥበብን ይገልጥብሃል ለጌታችን ቃል የተከፈተ ልብህ ዝቅ ብለው ቢያዩትስ የጌታ ልብስ ብቻ እንጂ ሌላ ምን ይገኝበታል፡፡ ከእውቀት፣ ከጥበብህ ከቅድስና የተለየሁ ባዶ ሰው ነኝ ብለህ ብታምን እንኳን እግዚአብሔር ባዶነትህን ለምስክርነት ይሻዋልና ከላይህ ላይ ያለ ልስንህን አስወግደው፡፡
አለበለዚያ የክፉዎች አጋንንት ማደሪያ መሆንህን አትርሳው፡፡ ማቴ.8፥28 ከዚያ በፊት ግን አሁን ዕድል አለህ፡፡ እንደውጪ ሁሉ ውስጠኛውንም የመቃብር ክፍል ማጽዳት ትችላለህ፡፡ አንተ እኮ! ዕድለኛ ነህ፡፡ የአባትህ ድምጹ እስከመቃብር ድረስ ዘልቆ ይሰማል ቅዱስ የሆነው ደሙ በመቃብር ያሉትን ሳይቀር መቃብራቸውን ከፍቶ ይቀድሳል እንዳትረሳ! ይሄ ዕድል ላንተም ተሰጥቶሃል፡፡ ደግሞም አንድ ነገር አለ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባው ቃል ኪዳን አለ መቃብሩን ከፍቶ ለሞቱ አጥንቶች ሕይወትን ሰጥቶ የሚያኖርበት ጊዜ አለ ይሄ ቃል ኪዳን ላንተም የተገባ ቃል ኪዳን ነውና አትፍራ ምን አልባትም ይሄ ቃል ኪዳን ላንተም የተገባ ተስፋ አትቁረጥ፡፡
በዙሪያህ ሆነው ከመቃብሩ ደጃፍ ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል የሚሉም ይኖራሉ ድንጋዩ ታላቅ ቢሆንም ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር መላኩን ልኮ አንተ ባልጠበቅከው ሰዓት ሊያነሣው እንደሚችል አትጠራጠር፡፡ መቃብር ብዙ ኀያላንን ይዞ ማስቀረቱ የተገለጠ ነው፡፡ እነ ዳዊት እነሶምሶን፣ ዮፍታሔ፣ ጌዴዎን ሌሎችም ኀያላን መቃብር ያድራሉ ደራሲዎቹ የደረሱላቸው ተራኪዎቹ የተረኩላቸው ዜመኞቹም ያዜሙላቸው ጀግኖች ሁሉም ከመቃብር አላመለጡም ምድራዊ ፍጥረት ሥጋዊ ደማዊ ሰውነት ሁሉም የመቃብር ምርኮኞች ሆነዋል፡፡
አንተ ሆይ! ባንተም ውስጥ ስንት ኀያላን የእግዚአብሔር ቃላት ተቀብረው ቀርተዋል መሰለህ? እነ አባ ጳውሊ ከዓለም ወጥተው የኮበለሉባቸው እነ አባ እንጦንስ ሥርዓተ መላእክትን የተላመዱባቸው ይሄ ግዙፍ ዓለም የተከናወነባቸው እነዚያ ሰባሪ ቃላቶች አንተ ዘንድ ሲደርሱ ግን ሳይሠሩ ቀብረህ አስቀርተሃቸዋል፡፡
እውነት እልሃለሁ አዲስ ሆነህ የምትሠራው በቅዱስ ቃሉ ነውና ቃሉን ጠብቅ ብታምንም ባትምንም በክፋት ብትሆን ሳትወድ በግድ “መቃብር ሆይ ይዞ ማስቀረትህ ወዴት አለ?” ሆሴ.13፥14፣ 1ቆሮ15፥55 ተብለህ መጣልህ አይቀርምና ይህ የፈጣሪህ ድምጽ ወዳንተ ባደረበት ቅጽበት ወዲህ በፈቃድህ ንስሓ ግባ ይሄ ጊዜ ለሌላ ለምንም የተመደበ አይደለም የንስሓ ብቻ ነው፡፡
“እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ ወደ እስራኤል ምድርም አገባችኋለሁ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” ሕዝ.37፥12-13፡፡