የ፭ኛው አገር ዓቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አጭር ዳሰሳ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሳምንት የአንድነት ጉባኤውን ያካሒዳል፡፡
በያዝነው ዓመትም ከሰኔ ፲-፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለሦስት ቀናት በቆየው ጉባኤ የየአህጉረ ስብከቶች ሰ/ት/ቤቶች ሪፖርቶችና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በቆየው በዚህ የሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ የአንድነት ጉባኤ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች፣ እንደዚሁም የወጣቶች የአገልግሎት ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው፣ በ፳፻፰ ዓ.ም የአገልግሎት ዘመን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተዳስሰዋል፡፡
ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የአሕዛብንና የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ በሚመለከት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በተገኙበት ለጉባኤው የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡
በጉባኤው መዝጊያ ዕለትም የ፳፻፱ ዓ.ም ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ተካሒዷል፡፡
በውይይቱም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የዕድሜ ገደብና የሥራ አስፈጻሚዎች የአገልግሎት ዘመን መሻሻል አለበት ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የ፳፻፱ ዓ.ም ዓመታዊ የተግባር ዕቅድ በጉባኤው ውይይት ከተደረገበት በኋላ ዕቅዱ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡
የ፳፻፱ ዓ.ም የመሪ ዕቅዱ ግቦች፡- ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤት አገልግሎትን ለማስፋትና ለማጠናከር መዘገጀቷን ማሳወቅ፣ በዓላማው ዙሪያ ሕዝቡን በስፋት ማነሣሣትና ለተግባር ማንቀሳቀስ፤ ቢጽ ሐሳውያንን የመከላከል ዘመቻ፤ እንደዚሁም የሰ/ት/ቤቶችን ሥርዓተ ትምህርት የማስቀጠልና የመከለስ ጥናት ሲኾኑ፣ በመሪ ዕቅዱ በመጀመሪያ አንድ ዓመት ከመንፈቅም፡- የሰንበት ት/ቤቶችን የዝማሬ ሥርዓት እና የሰንበት ት/ቤቶችን አንድነት መዋቅር ማጠናከር የሚሉ ነጥቦች ተካተዋል፡፡
በጉባኤው መዝጊያ ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዕ አቡነ ማትያስ ካልዕ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የተገኙ ሲኾን፣ በዕለቱ ቅዱስ ፓትርያርኩ ‹‹አንትሙሰ ንበሩ በኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤›› /ሉቃ.፳፬፥፵፱/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ትምህርት በሰጡበት ወቅትም ‹‹ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እስኪወርድላቸው ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ እንዲቆዩ ታዝዘዋል፡፡ እኛም እግዚአብሔር ማስተዋሉን፣ ጥበቡንና ጸጋውን እንዲያድለን በቤተ ክርስቲያን መቆየት ይገባናል፤›› ብለዋል፡፡
እንደዚሁም ‹‹ወጣቱ ትውልድ ትኩስ ስለኾነ ኹሉም ነገር የሚጎዳ አይመስለውም፡፡ ክፉዉን ከበጎው ለመለየት የሚቻለን መንፈስ ቅዱስ ሲያድርብን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚያድርብን ደግሞ ሐቀኝነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ እምነት፣ አንድነት ሲኖረን ነው፡፡ ጊዜውም መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበት ወቅት ነውና ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ማደሪያነት ማዘጋጀት ይገባናል፤›› ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ‹‹ይህ ዓለም በብዙ ጣጣዎች የተሞላ ነውና በአገልግሎታችሁ ላይ ልዩ ልዩ ፈተና ሊመጣባችሁ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ፀላዔ ሠናያት ሰይጣንን ፃእ መንፈስ ርኵስ ማለት ያስፈልጋል፤›› ካሉ በኋላ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለቤተ ክርስቲያን ሞገስ፣ ድምቀትና ተጨማሪ ሀብት መኾናቸውን ጠቅሰው ‹‹የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ስትሉ የምታነሡትን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
በመጨረሻም ‹‹ይህንን ሰላማዊ ጉባኤ በሰላም በማካሔዳችሁ ለደስታችን ወሰን የለውም፡፡ በዛሬው ዕለት በዚህ ጉባኤ ተገኝቼ ቡራኬ በመስጠቴ ደስታ ይሰማኛል፤›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ መ/ር ዕንቈባሕርይ ተከሥተ የመዝጊያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ለጉባኤው መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትንና በጉባኤው የተገኙ የየሰንበት ት/ቤት ተወካዮችን ካመሰገኑ በኋላ ለየሀገረ ስብከቱ ሰ/ት/ቤት መምሪያዎች ፴፬ የመዝሙር ሲዲዎች በነጻ እንዲሠራጩ መደረጉን ገልጸው ‹‹ከእንግዲህ የመናፍቃንን ዘፈንና ቀረርቶ የምንሰማበት ጊዜ አይኖርም፡፡ ከዚህ በኋላ ኹላችንም ወደ ድጓው፣ ጾመ ድጓው ነው የምንሔደው!›› የሚል ቁጭት አዘል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ረፋድ ላይ በቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ቡራኬ የተከፈተው ይህ የአንድነት ጉባኤ ባለ ፲፭ ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫውን በፓትርያርኩ ፊት ካቀረበ በኋላ በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከምሽቱ ፲፩ ተፈጽሟል፡፡
በጋራ የአቋም መግለጫውም፡- የተሐድሶ መናፍቃን የእምነት መግለጫ፣ የሰ/ት/ቤቶች በየቦታው መቋቋም፣ የአባላት የአገልግሎት ዘመን መሻሻል፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች እንግልትና ስም የማጥፋት ዘመቻ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ዐበይት ነጥቦች ተካተውበታል፡፡ የጉባኤውን ሙሉ የጋራ አቋም መግለጫ ተራ ቍጥሮችን፣ አንዳንድ ቃላትንና ፊደላትን አስተካክለን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የአገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፭ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የወጣ የጋራ አቋም መግለጫ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃለ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የወሊሶ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደቡባዊ ዞን የማይጨው፤ የምሥራቅ ትግራይ አዲግራትና መቐለ ዙሪያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ፤ የጉራጌ ስልጤ፣ ከምባታና ሐድያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤
የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ሓፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላችሁ የክብር እንግዶች፤
እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤን ወክለን በ፭ኛው አገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የተሳተፍን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ ከሰኔ ፲-፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ላለፉት ሦስት ቀናት በማደራጃ መምሪያው ዓመታዊ የአገልግሎት ዘገባ፣ በ፳፭ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍል የሥራ ክንውን ሪፖርት፤ እንደዚሁም የሰንበት ት/ቤቶች አባላት በኾኑ ባለሙያዎች በቀረቡ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡
የመምሪያው ዘገባም ኾነ ከ፳፭ አህጉረ ስብከት የመጡ ተወካዮች ያቀረቡት ሪፖርት ሰንበት ት/ቤቶች እጅግ በርካታ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙና የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማፋጠን እየተጉ መኾናቸውን አስገንዝቧል፡፡
ኾኖም ግን በየአህጉረ ስብከቱ ያሉ መናፍቃን እና አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖዎች፣ በየአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች እየደረሱ ያሉ የአስተዳደር በደሎች፣ የበጀት እና የመምህራን እጥረት፣ የመሰብሰቢያና የመማሪያ ቦታ አለመኖር፣ የአንዳንድ አህጉረ ስብከት ስፋት እና ለትራንስፖርት አመቺ አለመኾን አገልግሎቱን እየተፈታተኑ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ኾነው ተመዘግበዋል፡፡
በመጨረሻም በሪፖርቱም ኾነ በጥናታዊ ጽሐፎቹ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየት በተደረገው የጋራ ውይይት በቀጣይነት ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ የምንሠራቸውን እና የምንስማማባቸውን የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አውጥተናል፤
፩.የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የ፭ ዓመት ዕቅድ ማለትም ከ፳፻፮-፳፻፲ ዓ.ም ድረስ የታቀደውን መሪ ዕቅድ በቀሩት ጊዜያትም ለመፈጸምና ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፡፡
፪.የሰ/ት/ቤቶች አጠቃላይ መሪ ዕቅድ የኹሉም አጥቢያ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዕቅድ አካል እንዲኾን እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችም የሰ/ት/ቤቶችን መሪ ዕቅድ ከዕቅዳቸው ጋር በማገናዘብ በዕቅድ እንዲካተቱ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን፤
፫.መልክዓ ምድርን መሠረት ያደረገ የሰንበት ት/ቤቶች ትስስር በማጠናከር ሰንበት ት/ቤቶች ባልተቋቋሙባቸው አጥቢያዎች እንዲቋቋሙ፣ በተቋቋሙባቸው ደግሞ የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጥባቸው ለማድረግ እንሠራለን፡፡
፬.በአገር አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴና መጠነ ሰፊ ጥፋትን አስመልክቶ በመረጃ ክፍል የተሰበሰቡና የተደራጁ ማስረጃዎችን ለቅዱስነትዎና ለቅዱስ ሲኖዶስ እንድናቀርብ እንዲፈቀድልን በአንድነት እንጠይቃለን፡፡
፭.በ፳፻፬ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙ ፲፮ ግለሰቦችና ፰ ማኅበራት ያስተላለፏቸው የምንፍቅና ትምህርቶችና መጻሕፍት በሊቃውንት ጉባኤ መልስ እንዲሰጣቸው የታዘዘ ቢኾንም ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ምላሽ ባለመሰጠቱ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ የሚል የክህደት መግለጫ እስከ ማውጣት ደርሰዋል፡፡ ስለኾነም ለእነዚህ አካላት አስቸኳይ ምላሽ ይሰጥልን ዘንድ በአንድነት እንጠይቃለን፡፡
፮.በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያኒቷ ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ ለማስቆም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፡፡
፯.ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ሰ/ት/ቤቶች የቀረበው የፕሮቴስንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ መረጃ ውሳኔ እንዲሰጠው፤ ውሳኔው ተግባራዊ ይሆን ዘንድም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቷ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፡፡
፰.በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች በተሳሳተ አመክንዮ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አባላት ላይ እየደረሰ ያለው እስር፣ እንግልት እና ወከባ እንዲቆምልን በአንጽዖት እንጠይቃለን፡፡
፱.ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት የፍትሕ አካላትም ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር የሰንበት ት/ቤት አባላትን ከማሰር እና ከማንገላታት እንዲታቀቡ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል መመሪያ እንሰጥልን እንጠይቃለን፡፡
፲.በቃለ ዓዋዲው እና በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም በወጣው ውስጠ ደንብ ላይ የተጠቀሰው የሰ/ት/ቤቶች የዕድሜ ገደብ እንዲነሣልን በድጋሜ እንጠይቃለን፡፡
፲፩.ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ እስከ አጥቢያ ሰ/ት/ቤቶች የሚደርስ የፋይናንስ ትስስር እና አያያዝ ሥርዓት በመምሪያው በኩል ተጠንቶ እንዲጸድቅልን እንጠይቃለን፡፡
፲፪.በዘመናችን ሚዲያ በወጣቱ እና በሕፃናት አስተዳደግ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ስለሚገኝ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተምህሮ ለምእመናን በስፋት ማዳረስ እንዲቻል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ እና የሚተዳደር፣ ቤተ ክርስቲያኒቷንም የሚወክል የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ሥርጭት በመጀመሩ ከመምሪያው ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በጋራ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
፲፫.ተወካዮቻቸውን ያልላኩ አህጉረ ስብከት ተለይተው በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን፡፡
፲፬.በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ልማታዊ ጉዳዮች ከአባቶቻችን ጋር በመኾን ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያናችን ዕድገት እና ልዕልና የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
፲፭.የቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ምሩቃን ጋር ተባብረን የምንሠራ መኾናችንን እንገልጻለን፡፡
ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም፡፡